የኦሮሞ ብሄረተኞች ከማንም በላይ ኦሮሞዉን እየጎዱት ነው #ግርማካሳ


ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ለጨፌው(የኦሮሞ ክልል መንግስት ምክር ቤት) የተናገሩት ነገር ነበር። “ኦሮሞ አቃፊ ነው፣ ዘር አይለይም፤ ለምንድን ነው ታዲያ ሌሎች የሚፈሩንና የሚጠሉን? ያንን በሌሎች ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ማስተካከል አለብን” ነበር ያሉት። በተወሰነ ደረጃ እነ ዶ/ር አብይ በኦሮሞዉና በሌሎች ማህበረሰባት መካከል፣ የሕወሃትና የኦነግ ፖለቲካ የፈጠረውን የሃያ ሰባት አመታት አለመተማመን ለማስቀረት ችለው ነበር።  በጣም አመርቂ፣ ተስፋ ሰጪ ስራዎችን ሰርተዋል።

ሆኖም ግን ለኦሮሞ ጥቅም እንቆማለን የሚሉት ጽንፈኛ ሃይሎች፣ እነ ዶር አብይ የገነቡትን በአሁኑ ወቅት እያፈረሱት ነው። ጽንፈኞች እያደረጉት ባለው በጣም አሳፋሪን አሳዛኝ ግፎችና ሰቆቃዎች፣ አብዛኛው ማህበረሰብ በኦሮሞ ላይ ያለው አመለካከት እንዲቆሽሽ እያደረገ ነው። እነዚህ ጽንፈኞች በጽንፈኛ ፖለቲካቸው ከማንም በላይ እየጎዱ ያሉት፣ ራሱ የኦሮሞ ማህበረሰብን ነው። በዚህ በጽንፈኛ ፖለቲካ ምክንያት አሁን የኦሮሞ ክልል የሚባለው አካባቢ በእጅጉ እየታመሰ ነው ያለው። እዚህ ጋር እነ ዶ/ር አብይ ስል፣  በኦህዴድ ያሉ ጥቂት የለዉጥ ሃይሎችን ማለቴ ነው። ጽንፈኞች ስል ደግሞ የጃዋር ቄሮዎችን፣ ኦነጎችንና በዋናነት አብዛኞቹ ኦህዴዶች/ኦዴፓዎች ማለቴ ነው።

እነ ዶ/ር አብይም ሕግን ማስከበር ባለመቻላቸው፣ ጽንፈኝነትና አክራሪነት የተላበሱ ሃይላት በነጻነት አገር ውስጥ ገበተው የመንግስት ድጋፍ ተደረጎላቸው እንዲቀንሳቀሱ በመፍቀዳቸውም ነው ችግሩ የተባባሰው።

ይሄ ስንጽፍ ብዙዎች ጸረ-ኦሮሞ ይሉናል። ግን ከኦሮሞ ብሄረተኞች ይልቅ ለኦሮሞ ማህበረሰብ የሚጠቅመን ሀሳቦች ያስቀመጥን እኛ ነን።  ከዚህ በታች ያለውን ፣ በተለይም የኦሮሞ ልጆች በርጋታ እንዲያነቡ እጠይቃለሁ። እኛን መረጃ ሳይኖራችሁ ጸረ-ኦሮሞ ማለት አቁመው፣ እኛ ለኦሮሞ ማህበረሰብ ምን ያህል እንደነ ጃዋርና በቀለ ገርባ ካሉት በተሻለ ሁኔታ ለሕዝቡ የሚጠቅም ሕሳብ እንዳለን ይረዱ ነበር።

————————————–

– እነርሱ ኦሮሞው ከአማርኛ ጋር ተጣልቶ፣ የመሻሻል እድሉ ጠቦ እንዲኖር ነው የሚፈልጉት።ትልቁ ቀጣሪ በሆነው በፌዴራል መንግስት፣ በአማራው፣ በደቡብ፣ በቤኔሻንጉል፣በጋምቤላ ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች … ሥራ እንዳያገኝ። እኛ ኦሮሞው የአገሪቷን ዋና ቋንቋ አማርኛ ተምሮ፣ መጻፍና ማንበብ ችሎ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ያለ ምንም የቋንቋ ተጽኖ እንዲሰራ ነው የምንፈልገው።

– እነርሱ አፋን ኦሮሞ እንደማንነት መገለጫ ነው የሚያዩት። ከዚህም የተነሳ አማርኛ በመናገራቸው ኦሮሞነታቸውን ያጡ ይመስላቸዋል። ይሄንን  እኛ ቋንቋ የማንነት መገለጫ ሳይሆን መግባቢያ ነው ባዮች ነን። አሁን አላውቅም እንጅ፣ በፊት ግን በሐረር ያሉ ኦሮምኛም፣ አማርኛም አንዳንዶቹ አደርኛና ሶማሌኛም ይናገሩ ነበር። በወልቃይት ትግሪኛ፣ አማርኛ አንዳንድ ቦታም ዐረብኛ ይናገራሉ። ቋንቋ የማንነት መገለጫ ተደረጎ መወሰድ ሲጀመር ግን፣ ትግሪኛ የተናገረ ትግሬ ነው ሲባል ግን ችግር ተፈጠረ።

– እነርሱ ልጆቻቸውን ደህና ት/ቤት እያስተማሩ ነው፣ ለርካሽና የኋላ ቀር የፖለቲካ አይዲዮሎጂያቸው ብለው፣ አማርኛ እንዲጠላ በማድረግ በድሃው ኦሮሞ ልጅ ሕይወት ነው የሚጫወቱት ። እኛ ልጆቻችን ጥሩ የወደፊት እድል እንዲገጥማቸው እንደምንፈልገው የኦሮሞም ልጅ ብሩህ ሕይወት እንዲኖረው ነው የምንፈልገው። ስራ አጥቶ እንዲጎሳቆል አንፈልግም።

– እነርሱ በዘረኛና ጠባብ ፖሊሲዎቻቸው በኦሮሞው ማኅበረሰብና በሌላው መካከል መቃቃርና ልዩነት እንዲፈጠር ይሰራሉ። ከዚህ የተነሳ ኦሮሞው በብዛት በሚኖርባቸው ከአዲስ አበባ ራቅ ባሉ አክባቢዎች የንግድ፣ የቱሪዝም የመሳሰሉ እንቅስቅሴዎች በስፋት ሊስፋፋ አልቻለም። እስቲ አስቡት አሁን ማንነው የዓኖሌ ሐውልት ያለበት አካባቢ ሳይፈራ የሚሄደው? ሕዝቡ ደግና እንግዳ ተቀባይ ሆኖ፣ በሌላው አይምሮ ውስጥ ግን ከኦሮሞው ጋር በጭራሽ የማይገናኝ አስተሳሰብ እንዲገባ፣ እንዲፈራ ከመደረጉ የተነሳ፣ እንደ አዋሳ፣ ባህር ዳር ያሉ አሶሳ ሳትቀር ሲሻሻሉ እንደ ነቅምቴ፣ መቱ … ያሉ ግን ወድቀዋል። እኛ ዘረኞች የዘረገቱ የመፈራራት ግንብ ፈርሶ ኦሮሞው በባህሉ እንግዳ ተቀባይ ሌላው የሚያቅፍና እንድ እራሱ አድርጎ የሚቀበል (በጉዲፍቻ ባህል እንዳየነው) መሆኑን፣ ኦሮሞው ሌላው ጠላቱ ሳይሆን፣ ከሌላው ጋር የተዋለደና የተዛመደ መሆኑን እያስረዳን፣ ሁሉም ዜጎች ወደ ባህር ዳርና ወደ አዋሳ ሲሄዱ ነጻነት እንደሚሰማቸው ወደ ሁሉም የኦሮሚያ ግዛቶች ለመሄድም ነጻነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው የምንሰራው። እነ ነቀምት፣ እነ አሰላ እነ መቱ በንግድ በቱሪዝም እንዲያድጉ፣ እንዲሻሻሉ ነው የምንፈልገው።

– እነርሱ አፋን ኦሮሞ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ተወስኖ፣ ኦሮሞው ከሌላው ጋር እንዳይገባባና እንዳይነጋገር፣ እንዲለያይ ነው የሚሰሩት። እኛ አፋን ኦሮሞ ከኦሮሚያም አልፎም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲነገር፣ ከኦሮሚያ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደ ሰብጀክት እንዲሰጥ ነው የምንፈልገው። ከዚህም የተነሳ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ኦሮሞ አማርኛን በደንብ አውቀው አዲስ አበባ ሲመጡ በነጻነት ከከተሜው ጋር እንዲግባቡ፣ የአዲስ አበባ ልጆችም ወደ ገጠር ሲሄዱ በአፋን ኦሮሞ ከገበሬው ጋር እንዲግባቡ ነው የምንፈልገው።

– እነርሱ ኦሮሞውን በጠባብነት ጆንያ አሳንሰው ነው የሚያዩት። መገንጠልን፣ ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ ቁርሾች ነው የሚያስተምሩት። እኛ የኦሮሞውን ግንድነት፣ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማቅናት ዙሪያ የኦሮሞውን ጉልህ ሚና ነው የምንናገረው።

– እነርሱ አገር አስገንጣይ፣ የውጭ ወራሪዎች ተባባሪዎችን፣ ዘረኞች ነው እንደ ሞዴላቸው የሚያዩት፤ እንደ ዋቆ ጉቶ ያሉትን። እኛ እንደ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አብዲሳ አጋ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ አባመላ ፊታወራሪ ሃብቴ ዲንግዴን፣ ጀነራል ደምሴ ብልቱ፣ አቡነ ጴጥሮስ (አባ መገርሳ) … ያሉትን፣ አገር ያቀኑ የሕዝብ ኩራት የሆኑ የኦሮሞ ጀግኖችን ነው የምንዘክረው።

– እነርሱ የኢትዮጵያው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሃብትና ቅርጽስ የሆነው የግዕዝ (ሳባ) ፊደል በመጸየፍ፣ ፍረንጆችን እንደ ጌታ የማየት የባሪያነትና የበታችነት መንፈስ ስለተናወጣቸው፣ ከአፋን ኦሮሞ ሆነ ከኦሮምሞ ጋር ምንም ያልተገናኘ የላቲን ፊደል በሕዝቡ ላይ የዘረጉ ናቸው። እኛ የቀደምት የኦሮሞ ልሂቃን፣ እንደ አናሲሞስ ያሉ፣ የተጠቀሙበት የኦሮሞውን ኩራት የሆነው ኢትዮጵያዊ ፊደል እንጠቅም ባይ ነን።

– እነርሱ ኦሮሞውን በማጣላትና በመነጠል ለውጥ ይመጣል ባዮች ናቸው። እኛ ኦሮሞው ትግሉን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በማቀናጀት በኢትዮዮጵያዊነት ጥላ ስር ቢያደርግ፣ ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ ቢያያዝ ተዓምር መስራት ይችላል ባዮች ነን።