ነጋዴ በኦሮምኛ ካልሸጠ አትግዙ – አቶ በቀለ ገርባ

አቶ በቀለ ገርባ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበርና በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ናቸው። ትውልዳቸው በወለጋ ሲሆናሁ አሁን ነዋሪነታቸው በአዳማ/ናዝሬት ነው። አቶ በቀለ ፣ ከኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ ጋር በቅርበት የሚሰሩ የለማ ቲም ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በለማ ቲም ደስተኛ አለመሆናቸውን ብዙ ጊዜ ሲናገሩ የሚደመጡ ናቸው።

ልክ እንደ አቶ በቀለ የወለጋ ተወላጅ የሆኑና ኦሮምኛን አቀላጥፈው የሚናገሩ ዶ.ር አብርሃም አለሙ ፣ የአቶ በቀለ የኦሮምኛ ንግግር እንደሚከተለው ተርጉመው አቅርበዉልናል።

——————————-
ስለ ኦሮሞ ቋንቋና ባህል እድገት – በኦሮሞ ባህል ማእከል የተካሄደ የፓነል ውይይት
አዲስ አበባ፣ 08/07/2011

የኦሮሞን ቋንቋና ባህል አዲስ አበባ ውስጥ ማሳደግን ዐቢይ ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው የኦሮሞ ቋንቋና ባህል ቦርድ፣ ምሁራንና የማህበረሰቡን ልዩ ልዩ አካላት ያሳተፈ የፓነል ውይይት በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማእከል በ 08/07/2011 አካሂዷል፡፡ …..
በውይይቱ ላይ ንግግር ያቀረቡት የፖለቲካ መሪና የቋንቋ ባለሙያ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ “የኦሮሞ ቋንቋ ጉዳይ፣ የኦሮሞ ማንነት ጉዳይ ነው፤” አሉ፡፡

ቋንቋ የሌለው ህዝብ (ማህበረሰብ) የለም፡፡ አንድ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ አለ፣ እከሌ የሚባል ማህበረሰብ ነው ተብሎ ከሚታወቅበትም ነገር አንዱ ትልቁ ቋንቋው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ያን ማህበረሰብ እንዳይኖር ሲፈልጉ፣ አስቀድመው ቋንቋውን ይገሉታል፤ ቋንቋውን ይገሉታል፡፡ እንዲህ ነው የሚሉት፤ መፈክራቸውም እንዲህ ነው፤ “ቋንቋውን ግደል፤ ከዚያም ቀጥለህ ሰውዬውን ግደል፤” ይላሉ፡፡ በዚህ ምክኛት የራስን ቋንቋ መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ የራስን ማንነት መጠበቅ ማለት እንደሆነ ይታወቃል ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ምንድን ነው የሚያስፈልገን ስለሚለው አሁን ወደ አእምሮዬ ሊመጡ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ ማንሳት እወዳለሁ፡፡

እንግዲህ ይህ ቋንቋ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ተነስቶ ወደፊት እንዲቀጥል ለማድረግ፣ ብዙ ሰዎች ዋጋ ከፍለውበታል፤ ተሰውተውበታል፡፡ ዛሬ በዓለማችን ላይ ብዙ ቋንቋዎች አሉ፤ ከስድስት ሺህ በላይ፣ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ቋንቋዎች ናቸው ያሉት፡፡ ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ወደ እሚቀጥለው ምእተ-ዓመት (ክፍለ ዘመን) የሚሸጋገሩት ቢበዙ ቢበዙ ከሶስት ሺህ አይበልጡም፡፡ ቀሪዎቹ ሶስት ሺዎች ከወዲሁ የሚጠፉ ናቸው ማለት ነው፡፡ በዓለማችን ላይ የቋንቋ ሳይንስ እንደሚገልጸው፣ ከዚህ በኋላ የሚፈጠሩ አዳዲስ ቋንቋዎች አይኖሩም፡፡ ሆኖም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ቋንቋ ከዚህ ዓለም ላይ ይሞታል፤ ይጠፋል፡፡ የመጨረሻው ያንን ቋንቋ የሚናገረው ሰው፣ የንን ቋንቋ የሚናገረው አዛውንት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ፣ ቋንቋውም አብሮት ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ቋንቋ የሚፈጠርበት ሁኔታ፣ … እንግዲህ የተለያዩ ሃሳቦች ናቸው ያሉት፡፡ እኛ የምንወስደው ግን፣ ያው አንድ ቋንቋ ነው እየበዛ እየበዛ ማህበረሰቡ ወደ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ከመበታተኑ የተነሳ ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚለወጠው፡፡ የኩሾች ቋንቋ ድሮ አንድ ነበር፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ በጊዜያት መካከል፣ የተወሰነው ቡድን ከብቶቹን እየነዳ በዚህ አቅጥጫ ሲሄድ፣ ሌላው ደግሞ በሌላው መንገድ ሲሄድ፣ አንዱ በግራ፣ ሌላው በቀኝ ሲሄድ፣ በዚህም ምክንያት መገናኘት ሳይችሉ ሲቀሩና የአንድን ቋንቋ ልዩ ልዩ አካባቢያዊ አነጋገሮች (ቀበሊኛ) እየተነጋገሩ እየሄዱ፣ በዚያው ቀስ በቀስ የተለያዩ ቋንቋዎችን ወደ መነጋገር ይሄዳሉ፡፡ ጥንት እኛ ኦሮሞዎች ከሶማሌዎች፣ ከአፋሮችና ከሲዳማዎች ጋር አንድ ቋንቋ ነበር የምንናገረው፤ የኩሽ ቋንቋ፡፡ እየበዛንና ወደ ልዩ ልዩ አቅጣጫዎች እየተበታተንን መሄድ ስንጀምር፣ ቋንቋችን እየሰፋ፣ እየተዋለደ ሄደ ማለት ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ግን እዚህ ዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት እድል አይህኖርም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የቋንቋ መወለድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም አንድ ቋንቋ ወደ አንድ ዓይነትነት እያደገ ይሄዳል እንጂ ወደ መለያየት እያደገ ስለማይሄድ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ አለ፤ ሚዲያ አለ፤ የቋንቋን መደበኛነት የሚሰራ አለ፤ ሬዲዮ አለ፤ ቴሌቪዥን አለ፤ ጽሁፍ አለ፤ ትምህርት አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደ አንድ ቋንቋነት ነው የሚያመጡት፡፡

ለምሳሌ ከሃያ ሰባት ዓመታት ወይም ከሰሰላሳ ዓመታት በፊት፣ የነበረውን የኦሮሞ ቋንቋ ብንወስድ፣ እኛ ሁላችንም ዛሬ እንደምንነጋገርው ያለ መደበኛነትን የጠበቀ አልነበረም፤ ማእከላዊነቱን የጠበቀ ቋንቋ አልነበረም፡፡ ምስራቅ ሀረርጌ ውስጥ የሚነገረው፣ ምእራብ ወለጋ ውስጥ ከሚነገረው በመጠኑ የሚለያይ ነበር፡፡ መግባባት እንኳን የማይቻልበት ደረጃ ውስጥ እስከመግባትም ይደረስ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ቋንቋው ወደ አንድነት ደረጃ ደርሷል፡፡ በመሆኑም ካሁን በኋላ የተለያየ ቋንቋ ወደመሆን ደረጃ የሚደርስበት አጋጣሚ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ቋንቋ እንደ አንድ ቋንቋ ይቀጥላል፡፡ ይህን ማለት ምን ማለት ነው፣ እዚህ ዓለም ላይ ያሉት ቋንቋዎች ካሁን በኋላ አይባዙም፤ በቁጥር እያነሱ ነው የሚሄዱት፡፡ ሲያንሱ ደግሞ ለምንድን ነው የሚያንሱት ብለን ብንጠይቅ፣ ሰዎች የራሳቸውን ቋንቋ እየተው የሌላውን ቋንቋ ስለሚወስዱ ነው ሁሉም፡፡ ልክ ለምሳሌ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮሞ፣ ከምባታ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ እና ሌሎችም ቋንቋቸውን እየተዉ የሌላውን አንድ ቋንቋ እየወሰዱ እንደሚሄዱት፣ እንደዚሁ እየሆነ ነው የሚቀጥለው፡፡ ሰው የራሱን ቋንቋ እየተወ፣ እየተወ ነው የሚሄደው፡፡ ገበያውን እያየ ነ የሚሄደው፡፡ ትምህርት የማይሰጥበት ከሆነ፣ ስራ የማይሰራበት ከሆነ (የስራ ቋንቋ ካልሆነ)፣ ስራ ላይ የማይውል ከሆነ፣ ዛሬ ካለበት ደረጃ ነገ ደግሞ ከፍ ባለ ደረጃ የማይጠቀምበት ከሆነ፣ ዛሬ በጠቀምበት ስፍራ ነገ የማይጠቀምበት ከሆነ፣ ያ ቋንቋ ከእለት ወደ እለት እየሞተ ነው የሚሄደው፡፡ እያነሰ ነው የሚሄደው፤ ተናጋሪዎቹ እያነሱ ነው የሚሄዱት ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የኦሮሞ ቋንቋም እንደዚሁ በርትቶ ወደፊት በዓለማችን ላይ ከሚኖሩት፣ ወደሚቀጥለው ምእተ-ዓመት ወደሚተላለፉት ሶስት ሺህ የሚጠጉ ቋንቋዎች አንዱ እንዲሆን፣ ትልቅ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ይህ ቋንቋ እንዳይጠፋብን፣ እንዳይሞትብን፤ ከሚሞቱት ቋቋዎች አንዱ እንዳይሆንብን፡፡ ቋንቋችንን መጠበቅ፣ መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡ ትናንሽ ቋንቋዎች ትምህርት የማይሰጥባቸው ከሆነ፣ የስራ ቋንቋ የማይሆኑ ከሆነ፣ የሚቀጥለው ትውልድ ካሁኑ የማይቀበላቸው ከሆነ፣ ልጆቻቸው ቤት ውስጥ የማይነጋገሩባቸው ከሆነ፣ እነዚያ ቋንቋዎች መጥፋታቸው የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ልጆቻችንን ቋንቋችንን ማስተማር ግዴታችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ልጆቻችንን ማስተማር ግዴታ የሚሆንብን፤ ይ ቋንቋ እንዳይጠፋ የምንፈልግ ከሆነ፡፡ ማንነታችን ቀጣይ እንዲሆን የምንፈልግ ከሆነ፤ እንደ አንድ ህዝብ እንድንቀጥል የምንፈልግ ከሆነ፡፡ ህዝባችንን በመግደል ውስጥ በመጀመሪያ ከሚደረጉ ነገሮች አንዱ ለጆቻችን ቋንቋቸውን እንዳያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ቋንቋቸውን እንዲያውቁ የምናደርጋቸው ከሆነ፣ ቋንቋውን አስቀጥለናል ማለት ነው፡፡ ቋንቋው ወደሚቀጠለው ምእተ-ዓመት እንዲሸጋገር እያስቀጠልነው ነው ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ባለበት ደረጃ፣ ለምሳሌ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የሚነገር ከሆነ፣ ወይም በዚህች የአዲስ አበባ ወሰን ዙሪያ የሚነገር ከሆነ፣ ነገ ደግሞ የማይነገር ከሆነ፣ የሚነገርበት ቦታ እየጠበበ የሚሄድ ከሆነ፣ ቋንቋው ወደመጥፋት እየሄደ ነው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአቃቂ አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት፣ ወይም ከሶስት ወይም ከአስር ዓመት፣ አስራአምስት ዓመት በፊት፣ ኦሮሞ ነበር የሚኖረው፤ እነሱው ነበሩ የሚናገሩት፡፡ ስለዚህ ቋንቋው በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ዛሬስ፣ ይሄን ቋንቋ የሚናገር ሰው የለም፤ እዚያ አካባቢ የለም፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ትናንት በሚነገርበት ቦታ ላይ ዛሬ እየተነገረ አይደለም፡፡ ትናንት ከነበረበት ደረጃ ወደ ታች ዝቅ እያለ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ቋንቋ የተወሰነ እርምጃ ወደ ሞት እየሄደ ነው ማለት ነው፤ ወደ ሞት እየተራመደ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ ምሳሌ ደግሞ ዛሬ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥበት ከሆነ፣ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከሆነ ትምህርት የሚሰጥበት፣ ቢያንስ ቢያንስ ከስድስተኛ ክፍል ወደ ታች ሊወርድ አይገባውም፡፡ ሰባተኛ ክፍልን ወደምንማርበት ደረጃ ከተሸጋገረ ግን ቋንቋውን አራምደነዋል ማለት ነው፤ ወሰኑን አሰፋንለት ማለት ነው፡፡ ስምንተኛ ክፍልን የምንማርበት ከሆነ ደግሞ ትንሽ ጨመር አደረኝለት ማለት ነው፡፡ ዘጠነኛን የምንማርበት ከሆነ ደግሞ እድገቱን ጨመርንለት ማለት ነው፡፡ ትናንትና የማሰጠውን አገልግሎት እንዲሰጥ ስናደርገው፣ ቋንቋውን አሳደኘው ማለት ነው፡፡ ያን ቋንቋ እያጠነከርነው ሄድን ማለት ነው፡፡ እየተንከባከብነው ሄድን ማለት ነው፤ እንዲሰነብት የድርሻችንን እያደረኝ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለምሳሌ እንደ አንድ ግለሰብ፣ በግልም ሆነ በቡድን ስለ ቋንቋ ትምህርት ስናነሳው የነበረ ጉዳይ አለ፡፡ የኦሮሞ ቋንቋ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርት ይሰጥበት ከነበረበት ወደ ስድስተኛ ክፍል ዝቅ የሚደረግ ከሆነ፣ ትናንትና አገልግሎት ሲሰጥ ከነበረበት ደረጃ ወደ ታች ዝቅ ብሏል ማለት ነው፡፡ ይሄ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ይሄ ፖለቲካ ሳይሆን የቋንቋ ሳይንስ ነው፡፡ ትናንትና የሚሰጠውን አገልግሎት የማይሰጥ ከሆነ ቁልቁል ወዷል ማለት ነው፡፡ ትናንት አገልግሎት ሲሰጥ ከነበረበት ቦታ ዛሬ የማይሰጥ ከሆነ እየሞተ ነው ማለት ነው፡፡ የሄ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ዛሬ እስከ ስምንተኛ ክፍል የምንማርበት ቢሆን፣ ነገ ደግሞ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ነው የምንማርበት ቢሆን፣ ቋንቋችንን እያጠነከርነው ሄድን ማለት ነው፡፡ ጉልበት እየሰጠነው ሄድን ማለት ነው፤ ቫይታሊቲ፣ ኤትኖሊንግዊስቲክ ቫይታሊት ይሉታል እንዲህ ዓይነቱን የቋንቋ ጥንካሬ፡፡ ቋንቋን የሚያጠነክር መቅኒ መስጠት ማለት ነው፡፡ ….. ይህን የማናደርግ ከሆነ ግን ቋንቋችንን አቅም እየነሳነው፣ ጥንካሬውን እያጠፋነው፣ ወደ ሞት እየገፋነው እየሄድን ነው ማለት ነው፡፡ ዝም ብለን ተሰብስበን ቁጭ እያልን፣ “ቋንቋችን መሞት የለበትም፤ ምን እናድርግ ቋንቋችን እንዳይሞት እያልን ብንፎክር ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ አንደኛ ሳይንሱን ማወቅ አለብን፡፡ አውቀን ምን ከሆነ ነው የሚጠነክረው፣ ምንስ ከሆነ ነው የሚዳከመው? ስለዚህ በተለያዩ ተቋማት በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ለምሳሌ እዚህ ማስታወቂያ ላይ የሚጻፈው ጽሁፍ በአንድ ቋንቋ ብቻ መጻፉና በሁለት ቋንቋዎች መጻፉ ልዩነት አለው፡፡ በአንድ ቋንቋ ብቻ የሚጻፍ ከሆነ በዚያው ቋንቋ ብቻ ማንበብ፣ በዚያው መተርጎና መረዳት ግዴታችን ይሆናል፤ የፈለገውን ቢሆንም፡፡ በሁለት ወይም በሶስት ቋንቋ የምንጽፍ ከሆነ ምን ያድርግልኝ ብሎ ይህን ቋንቋ ወደ ማንበብ ይሄዳል? ለምን፣ ምን እዲያደርግለት፣ እድል ተሰጥቶታል ለምን ማንበብ ያስፈልገዋል በዚህ ቋንቋ? ባእዳን እንዴት ቋንቋቸውን እንደሚያሳድጉ እናውቃለን፡፡ እኛ ደግሞ በፍርሃትም ይሁን፣ ባለማውቅም ይሁን፣ አንዳንድ ጊዜ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በመጻፍ ቋንቋችንን ጉልበቱን፣ ችሎታውን፣ ጥንካሬውን እያሳጣነው እንሄዳለን፡፡ እኔ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነ ቦታ ሄጄ ነበር፣ እዚሁ ሀገር ውስጥ፡፡ መቀሌ ሄጄ ነበር፡፡ እዚያ ያየሁት፣ ለአንድ ቀን ብቻ ነው እዚያ የቆየሁት፣ በአንድ ቋንቋ ብቻ፣ በራሳቸው ቋንቋ ብቻ፣ ወይም ቢበዛ ደግሞ በሁለት ቋንቋ ነው የሚጽፉት፡፡ ወደ ኦሮሚያ ስንመጣ ግን በሶስት ቋንቋ ነው የሚጻፈው፡፡ ያውም የእኛ ቀጫጭን ቁቤዎች ሲሆኑ፣ የሌላውን ደግሞ በትላልቅ ፊደላት በሰፊው ይጻፋል፡፡ ይሄ ተጽእኖ አለው፤ የፊደሉ መጠን ብቻ በአእምሯችን ውስጥ የሚፈጥረው ነገር አለ፡፡ ሰው እራሱን ጥሎ፣ እራሱን ጠልቶ፣ እራሱን ወደ ታች ዝቅ አድርጎ፣ ሰው ማንነቱን ወደታች ጥሎ የሌላን ማንነት እራሱ ላይ አይገነባም፡፡ ፍርሃትም ከሆነ ማስወገድ ግድ ነው፡፡ እውቀትም ከሆነ ከላያችን ላይ ጠርገን መጣል ግዴታችን ይሆናል፡፡ እኛ እኛ ነን፤ ቋንቋችን እኛ ነው፤ እኛም ቋንቋችን ነን፡፡ ስለዚህ ቋንቋችንን ማጠንከር ባለብን ቦታዎ ሁሉ ማጠንከር አለብን ማለት ነው፡፡ አምልኮ ቤት ስንሄድ በቋንቋችን ማምለክ፤ በቋንቋችን መጸለይ፤ በቋንቋችን መቀደስ፤ በቋንቋችን የምናደርገውን ማድረግ፡፡ ይህን ወይም ያንን ሃይማኖት ተከተሉ ማለት አያስፈልግም፡፡ ግን ማድረግ የምንፈልገውን ሁሉ በቋንቋችን ነው ማድረግ ያለብን፡፡ በቋንቋችን ነው ማድረግ ያለብን፡፡ እግዝአብሄር ይህን ቋንቋ ሲሰጠን በዚሁ ቋንቋችን እንደሚሰማን የታወቀ ነው፡፡ በራሳችን ቋንቋ ጸልየን ከእግዝአብሄር ጋር ስንገናኝ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ የምናደርገውን ሁሉ ይህን በማወቅ ይሁን፡፡ የምንጽፈው፣ ልጆቻችንን፣ ደሞዛችንን እንኳን ተቀብለን ስንገባ፣ በአማርኛ “አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት” ከማለት፣ ቶኮ፣ ለማ፣ ሰዲ፣ አፉር (አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት…) ብለን መቁጠር መቻልን መልመድ አለብን፡፡ የምናደርገውን ሁሉ ከማንነታችን አኳያ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ የምንሰራውን ሁሉ፡፡ የምናየውን ሁሉ፣ የምንገዛውን ሁሉ፡፡

ዝም ብሎ ምንም ሳያደርጉ የራስን ቋንቋ ማሳደግ አይቻልም፤ እንካ ቋንቋህን አሳድግ የሚልህ የለም፡፡ ለምን? ምክንያቱም የኛ እያደገ ሲሄድ፣ ሌላው ደግሞ ከቁጥር እየጎደለ መሄዱ የድ ስለሆነ ነው፡፡ ቋንቋ እየተገፋፋ የሚሄድ በመሆኑ፡፡ አንድ ቋንቋ መጥፋት ሲጀምር፣ የቋንቋው ተናጋሪ ማህበረሰብ ባለ ሁለት ቋንቋ (ልሳነ-ክልኤ) bilingual እየሆነ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ አሁን ወደ ሶማሌና ኦሮሚያ ወሰን አካባቢ ብትሄዱ፣ ሁለት ቋንቋ ነው የሚናገሩት፤ ኦሮሚኛና ሶማሊኛ፡፡ ሆኖም ከጥቂት ግዜ በኋላ እንደዚህ መናገራቸውን አይቀጥሉበትም፤ ሀይል (ስልጣን) ወዳለው ይሄዳል ነገርዬው፤ ገንዘብ ወዳለው፣ ጉልበት ወዳለው፣ ስልጣን ወዳለው ይሄዳል፡፡ ወይ ይሄኛውን ወይም ያኛውን መናገር ይተዋሉ፡፡ ስለዚህ ልጆቻችን ቋንቋችንን መተው ወይም ልሳነ-ክልኤ መሆን ሲጀምሩ፣ ባለ ሁለት ቋንቋ መሆን ሲጀምሩ፣ አንደኛው ቋንቋ ችግር ውስጥ መግባት መጀመሩ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ስለዚህ ቋንቋችንን ለማጠናከር የሚያስፈልገው ሌላው ጉዳይ ኤኮኖሚ ነው፤ ኤኮኖሚያችን ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ጠንካራ ንግድ ያለኝ ብሆንና ኦሮሞ መሆኔን ካወቁ፣ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ እንዳደርግላቸው ሲፈልጉ፣ ብድር እንድሰጣቸው ሲፈልጉ፣ አንዳች ውለታ እንድውልላቸው ሲፈልጉ፣ አስቀድመው በኦሮምኛ ሰላምታ ያቀርቡልኛል፤ “አከም፣ ነጋ?” ብለው ሰላምታ ያቀርቡልኛል፡፡ ምክኛቱም የኔን ዝምድና ይፈልጋሉ፡፡ ይሄን ዝምድና የሚያመጡልኝ ወደውኝ አይደለም፤ ገንዘቤ ነው የሚያመጣልኝ፤ አቅሜ ነው የሚያመጣልኝ፡፡፡ አቅም ከሌለኝ ዘመድ አይኖረኝም፡፡ አቅም የሌለው ማህበረስብ ዘመድ የለውም፡፡ እንዲሁ ዝም ብለን መንገድ ላይ ስንጭህ ብንውል ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ የሆን ነገር በእጃችን ሲኖረን፣ የሆነ የሌላውን እጅ መጠምዘዝ የምንችልበት፣ የሆነ የራስን ቋንቋ የሚያጠነክሩበት፣ የሆነ የራስን ማንነት የሚያጠነክሩበት ነገር በእጅ ውስጥ ካለ ነው እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ አይሆንም፡፡ ወይ እውቀት ሊኖረኝ ይገባል፤ እውቀቴን ከኔ ለመውሰድ ሰዎች ወደኔ መጥተው በምፈልገው ቋንቋ ያናግሩኛል፡፡ ስለዚህ ኤኮኖሚም ወሳኝ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ኤኮኖሚ የአንድን ቋንቋ ደረጃ (ስቴተስ) የሚወስን ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሶስት ወይም ከአራት ዓመታት በፊትና አሁን ያለውን ብንወስድ፣ የኦሮሞን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ለውጥ አለ ወይስ የለም? “ለውጥ አለ” (የአድማጮች መልስ)፡፡ በየሄድንበት ሁሉ የኦሮሞን ቋንቋ ነው አይደል የምንሰማው አሁን? ለምን ይመስላችኋል? የቋንቋው ደረጃ (ስቴተስ) ስለተለወጠ ነው፡፡ ደረጃው ነው የተለወጠው፡፡ ደረጃው ደግሞ አንድም በስልጣን የሚመጣ ነው፤ በፖለቲካ ስልጣን፡፡ የፖለቲካ ስልጣን፡፡ አሁን ያሉት ይጥቀሙንም፣ አይጥቀሙንም፣ ምንም ይሁኑ ምን ኦሮሞ መሆናቸውን ብቻ ሰዎች ያውቃሉ፡፡ እናም “ሰዎቹ እንዲህ ናቸው፤” ይላሉ፡፡ አሁን ይህ ቋንቋ ይፈለጋል፤ ገብያ አለው፡፡ ነገ ከሌለን [ስልጣን] እዚህ ቦታ ላይ አይኖርም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በታክሲ ስትሄዱ፣ ወይም ሌላ መኪና ስትሳፈሩ፣ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ስትገቡ ከአንድ ቋንቋ በስተቀር የሚዘፈን የለም፡፡ ናዝሬት ብትሄዱ፣ ጎባ ብትሄዱ፣ ነቀምት ብትሄዱ፣ ሻሸመኔ ብትሄዱ፣ አዲስ አበባ ብትመጡ፣ አንድ ቋንቋ ብቻ ነው የሚዘፈነው ታክሲ ውስጥ፣ “ገገው፣ ገገው” ይላል፡፡ አሁን ያ ሁኔታ የለም፤ ብዛት የለውም፡፡ አቅም ነው፤ አቅም ስለተለወጠ ነው፡፡ አቅም ሲለወጥ ቋንቋችንም እየተለወጠ ይሄዳል፡፡ ስልጣን እያገኘ ይሄዳል፤ ጉልበት እያገኘ ይሄዳል፡፡ የፖለቲካ ስልጣን የምንፈልገው ለዚህ ነው፡፡ መጥፋት አንፈልግም፡፡ ቋንቋችን እንዲጠፋ አንፈልግም፡፡ ስለዚህ ስልጣን መያዝ የቋንቋችንን ደረጃ ይለውጣል፡፡ ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ላስረዳችሁ እንደሞከርኩት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ባካሄድኩት ጥናት የሚመስል ነገር እንደተረዳሁት፣ እናንተም ከህዝብ ቆጠራ ሰንድ ማግኘት እንደምትችሉት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የወላይታ ሰዎችና ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የትግራይ ሰዎች ቁጥር እኩል ነው፡፡ እኩል ነው፡፡ ሆኖም የወላይታ ዘፈን አጸሙም፡፡ ድምጻቸው አይሰማም፡፡ የሉም፡፡ የሌሎቹን ግን እንሰማለን፡፡ ይሄ ለምን/እንዴት ሊሆን ቻለ? ኤኮኖሚ ነው፤ የገንዘብ አቅም ነው ያለው፤ የፖለቲካ አቅም ነው ያለው፡፡ የኤኮኖሚ አቅም የሚኖረን ከሆነ ቋንቋችን ይጠነክራል፡፡ የፖለቲካ ጉልበት (ስልጣን) ካለን ቋንቋችን ይጠነክራል፡፡ ያለበለዚያ የኛ ቁጥር ይህን ያህል ነው፣ እኛ ይህን ያህል ሚሊዮን ነን፣ እንዲህ ሆነን፣ እንዲያ ሆነን ብንል ዋጋ የለውም፡፡ ማድረግ በሚገባን ነገር ላይ በርትተን መስራት ከሁላችን የሚጠበቅ ነው ማለት ነው፡፡

ሌላው ላነሳው የምፈልገው ነገር፣ የራስን ቋንቋ ከሚገድል ነገር መካከል ወይም የራስን ቋንቋ ጉልበት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከሌላ ማህበረስብ ጋር የሚደረግ ጋብቻ (ትዳር) ነው፡፡ ይኸውም ለምንድን ነው፣ የህዝብ ስብጥርን (ዴሞግራፊ)፣ አንድ ቋንቋ የሚጠነክረው ያን ቋንቋ የሚናከር ህዝብ ቁጥር ሲጨምር ነው፡፡ ያን ቋንቋ የሚናገረው ህዝብ ቁጥር ደግሞ የሚጨምረው ሁለት ነገሮች ከተሟሉ ነው፡፡ አንደኛ፦ የመራባቱ መጠን ከመሞቱ መጠን በላይ ሆኖ ከተገኘ ነው፤ ፈርቲሊቲው፣ የመራባቱ መጠን፣ የሚወለዱት ሰዎች ቁጥር ከሚሞቱት ሰዎች ቁትር በላይ ከሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባን ብንወስድ አሁን፣ አዲስ አበባን ብንወስድ፣ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሰዎች ቁጥር ወይስ ከአዲስ አበባ የሚወጡ ሰዎች ቁጥር ነው የሚበዛው? ወደዚህ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ይበልጣል ይመስለኛል፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡት ሰዎች ግን ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው ችግር፣ ወደዚህ የሚገቡት ሰዎች ሁሉ አንድ እንስራ ውስጥ ታጭቀው (ተቀቅለው) አንድን ቋንቋ ብቻ ወደ መናገር ወደ ታች ነበር የሚወርዱት፤ ሁሉም፡፡ ይሄ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ከሌላ ቦታ ወደዚህ የሚመጡት ሰዎች ሁሉ ቋንቋቸውን እየተዉ ነበር የሚሄዱት፡፡ አሁን ግን ወደ አዲስ አበባ ቢገቡ እንኳን ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ መጋባት ጀምረዋል፡፡  ወደዚህ ቢመጣ እንኳን ቋንቋውን መልቀቅ ትቷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ እየበዛ ሲሄድ፣ ያንን ቋንቋ የሚናገረው ህዝብ ብዛት እየጨመረ ሲሄድ፣ ቋንቋው እያደገ ይሄዳል፡፡ ቋንቋውን የሚናገረው ሰው ብዛት እያነሰ ሲሄድ ደግሞ ቋንቋው እየሞተ ነው የሚሄደው፡፡

በዚህ ውስጥ ከራስ ማህበረስ ውጭ (ከባእድ ጋር) የሚደረግ ጋብቻ የሚለውን ነጥብ ድጋሚ ላንሳ፡፡ አንድ ባልና ሚስት የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ነገር፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ነገር፣ ልጆች ሲወልዱ ልጆቻቸው ከሁለቱ የየትኛውን ቋንቋ ይናገሩ ይሆን? እንደ አዲስ አበባ ነዋሪ የትኛውን ቋንቋ ይሆን የሚወስዱት? የትኛውን ነው የሚወስዱት? ያንኑ ነው የሚወስዱት፤ ይሄ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አንደኛው አደጋ ከራስ ማህበረሰብ ውጭ የሚፈጸም ጋብቻ፣ ይህን የምናገረው የቋንቋ ሳይንስ ስለሆነ ነው እንጂ የጥላቻ ወይም መውደድ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም፤ ይሄ ቋንቋን ወደ ታች ከሚያወርዱ ጓዳዮች መካከል፣ አንድን ቋንቋ ከሚገድሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ምክኛቱም ከሚወለዱት ልጆች ላይ ቋንቋውን የሚያተባቸው በመሆኑ ነው፡፡ እናትና አባት አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ቢሆኑ፣ ልጆቻቸውም ያን ቋንቋ ወስደው ለማደግ ትልቅ እድል ይኖራቸዋል፡፡ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ከሆነ፣ አባትየው ኦሮሚኛ፣ እናት ደግሞ ሌላ ቋንቋ፣ ወይም እናት ኦሮሚኛ፣ አባት ደግሞ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ከሆነ፣ የሚወለደው ልጅ ኦሮሚኛን ወስዶ የማደግ እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ያውም ከውጭ የሚመጣው ተጽእኖ ሲጨመርበት ጭራሽ የባሰ ዝቅ እያደረገው ነው የሚሄደው፡፡ ይህ የራስን ቋንቋ ከሚገድሉ ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑ በሳይንሱ ውስጥ የሚታወቅ ነው ማለት ነው፡፡

የሚቀጥለው ጉዳይ፣ ኦሮሞ ስለ ቋንቋው ምንድን ነው የሚያስበው የሚለው ነው፡፡ እንዴት ነው የሚያስበው? ዋጋ የሌለው ቋንቋ እያለ ነው የሚያስበው፣ ወይስ ይሄ ቋንቋ እንደሌላው ማንኛውም ቋንቋ ትልቅ ነው ብሎ ነው የሚያስበው? ደረጃውን ትናንት እንዴት ነበር የምናየው፣ ዛረስ እንዴት ነው የምናየው? ትናንትና ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብለ በኦሮሚኛ መናገር ፈርተናል፡፡ ታክሲ ውስጥ በኦሮሚኛ ቋንቋ ስንናገር ሁሉም ዞር እያለ ያየን ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ ደረጃው ስለተለወጠ ነው፤ ስቴተሱ ነው የተለወጠው፡፡ ይህም በከፍተኛ ዋጋ የሆነ ነው፡፡ ይህ ከእጃችን እንዳይወጣ መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ቋንቋችን ወደሚቀጥለው ክፍለ ዘመን እንዲሻገር የምንፈልግ ከሆነ፣ ብዛታችንን፣ ዲሞግራፊያችንን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ በማንጠቅምባቸው ቦታዎች (ጉዳዮች) ውስጥ ሁሉ ሰብረን ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡ ነገ ዛሬ ከምንጠቀምበት ድንበር አሻግረን ልንጠቅምበት ያስፈልገናል፡፡ ሰባተኛ ክፍል ድረስ የምንጠቀምበት ከሆነ፣ እስከ ስምንተኛ መጠቀም፣ ስምንተኛ ክፍል ድረሰ ከሆነ እስከ ዘጠኝ ወደ መጠቀም ማሸጋገር፡፡ ወይም በአንድ የሙያ መስክ ብቻ የምንጠቀምበት ከሆንን፣ በሁለት፣ ሶስት፣ አራት የሙያ መስኮች ወደ መጠቀም ማሸጋገር፡፡ በእምነት ስፍራ መጠቀም፣ በስራ ቦታ መጠቀም፣ በንግድ ቦታ መጠቀም፡፡ የሆነ ነገር ለመገበያየት (ለመግዛት) ስንሂድ መጠቀም፣ የሆነ ነገር ስንሸጥ መጠቀም፡፡ በኦሮሚኛ መጠየቅ ነው፤ “ስንት ነው ይሄ ዋጋው?” ሻጩ አላውቅም ካላችሁ፣ እናንተም እንግዲው “በል ደህና ሰንብት፤ እኔም አልገዛም” ብሎ ትቶ መሄድ፡፡ ጸብ አያስፈልግም፤ ሌላ ምንም አያስፈልግም፡፡ ሄዳችሁ ጠይቁት፤ “ይሄ ዋጋው ስንት ነው? ከየት ነው የመጣው? የት ነው የሚሰራው? ከፍ ያለ መጠን አለ? አነስተኛ አለ?” ብላችሁ ጠይቁ፡፡ አላውቅም ካለ፣ “ደህና ሰንብት” ብሎ መሄድ፡፡ ሌላውም እንዲሁ ሄዶ ሲጠይቀው፣ “እንዲህ አርግልኝ፤ ያንን ስጠኝ” ብሎ ይጠቀውል፡፡ አሁንም አላውቅም ካለ፣ “ደህና ዋል፤” ብሎ ትቶ ሄዶ፣ ቋንቋውን ለሚናገረው መስጠት ነው፤ ማንነታችንን ለሚያሰፋው፣ ቋንቋችንን ለሚያሳድገው መስጠት፡፡ ይህንን በየቀኑ ሶስት አራት ሆነን ደጋግመን ስናደርገው፣ ሰውዬው ምን ያደርጋል? ወይ ቋንቋውን ይማራል፤ ወይም እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ከሆነ ደግሞ ይናገራል፤ ይሄ ሁለቱንም ማድረግ የማይችል ከሆነ ደግሞ ቋንቋውን የሚችል ሰው ይቀጥራል፡፡ ለአንድ ሰው የስራ መስክ ከፈታችሁ ወይስ አልከፈታችሁም? ዝም ብለ እየተነሳን ብንጮህ፣ ይህቺ ሰውዬ ቋንቋችንን አትናገርም፣ ምንምን እያልን፣ ቤቱን ማስዘጋት ነበር፣ ማናምን ከምንል፣ ምን እዚያ አደረሰን፣ ምንስ አስዘጋን፣ ገንዘባችን ኪሳችን ውስጥ ነው ያለው፣ መግዛት ከሚገባን ቦታ ሄደን አንገዛም? እሱ እራሱን ይዘጋው የለም እንዴ? ስለዚህ በብልሃት መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለ ቋንቋችን ጉዳይ፣ በጥንካሬ፣ በብልሃት፣ በእውቀት ተመርተን ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡ …

 

(የሙሉ ቪዲዮው ሊንክ ላማግኘት እዚህ ይጫኑ)