የኤርትራው ፕሬዝዳንት ቻይና ናቸው

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር ቤጂንግ ውስጥ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ፕሬዝዳንት ጂፒንግ፣ ቻይና ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት “ስትራቴጂካዊ” እና “ረጅም ጊዜ የሚቆይ” ግንኙነት አድርጋ እንደምታየው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገልጠውላቸዋል።

በኢነርጂ፣ በመሠረተ ልማትና ግብርና መስኮች ከኤርትራ ጋር ትብብሯን ለማጎልበትና የኤርትራን ኢንዱስትሪ እና ግብርና ለማዘመን እንደምትሠራ የገለጡት ጂፒንግ፣ ኤርትራ ለምትከተለው ከውጭ ተጽዕኖ ነጻ የኾነ የውጭ ፖሊሲና ለሉዓላዊነቷና ክብሯ ለምትሰጠው ዋጋ ፕሬዝዳንት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ትናንት ቤጂንግ የገቡት፣ በቻይናና አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ነው።