ኢትዮጵያ የኮሮና መመርመሪያ ቴስት ኪት ማምረት ጀመረች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኢትዮጵያ ቢጂአይ ባዮ ቴክኖሎጂ ከተባለው ግዙፍ የቻይና ኩባንያ በመተባበር ባቋቋመችው ፋብሪካ የኮሮና መመርመሪያ ቴስት ኪት ማምረት ጀመረች።

Image may contain: one or more people, people standing and outdoor

መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ የተከፈተው እና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፖርክ የተገነባው ፋብሪካ በአመት 10 ሚሊዮን የመመርመሪያ ኪቶችን የማምረት አቅም እንዳለው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ በሰጡበት ወቅት በፋብሪካው የተመረተውን ቴስት ኪት በእጃቸው ይዘው ታይተዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ መመርመሪያውን እያሳዩ “እዚህ ጋ እንደምታዩት በኢትዮጵያ የተመረተ ነው የሚለው” ሲሉ ተደምጠዋል።”የመጀመሪያው የቴስት ኪት በኢትዮጵያ ተመርቷል። በቢጂአይ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር ነው ይኸ ፋብሪካ የተቋቋመው። አሁን በአመት ከ10 ሚሊዮን በላይ [ቴስት ኪት የማምረት] አቅም አለው። ለእኛም ለተቀረው የአፍሪካ አገርም ምርቱን ለመላክ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል” ብለዋል።”በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤተ ሙከራ ተቋቁሞ እዚያው ምርመራ ይደረጋል።

በከተማችንም ተጨማሪ ቤተ ሙከራዎች ይቋቋማሉ” ሲሉም አክለዋል። ዐቢይ የጤና ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አርከበ እቁባይ (ዶ/ር) ጨምሮ ፋብሪካው በኢትዮጵያ እንዲቋቋም ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል ያሏቸውን አመስግነዋል።ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ቴስት ኪት ማምረቻውን የከፈተው የቻይና ኩባንያ እስካለፈው ግንቦት ወር ድረስ ብቻ 35 ሚሊዮን የኮሮና መመርመሪያዎችን ለ180 አገሮች መሸጡን እና 58 ቤተ ሙከራዎች መገንባቱን የሬውተርስ ዘገባ ይጠቁማል።

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን ከማመሱ በፊት ባለፈው ጥቅምት 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ከቢጂአይ በተሰጠው መሳሪያ የዘረመል ቤተ ሙከራ ለማቋቋም ማቀዱን አስታውቆ ነበር። መቀመጫውን በቻይናዋ ሸንዘን ከተማ ያደረገው ቢጂአይ ግሩፕ በዓለም ትልቁ የዘረመል ጥናት ኩባንያ ነው። የኩባንያው ድረ ገጽ እንደሚጠቁመው ለሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች የዘረመል ትንተና መሳሪያዎች እና ግብዓቶች ያቀርባል። ከ 1,000 በላይ ሰራተኞች በ39 አገሮች አሉት።ኩባንያው ከ21 አመታት በፊት ቤጂንግ ጄኖሚክስ ኢንስቲትዩት በሚል ሥያሜ በአራት ሳይንቲስቶች ሲቋቋም ዋንኛ ዓላማው የሰው ልጅን ዘረመል ለማጥናት በሚደረገው ምርምር ቻይናን መቀላቀል ነበር። ላለፉት አራት አመታት 20 ሚሊዮን የእጽዋት እና የእንስሳት ዘረመል የተከማቸበትን የቻይና ብሔራዊ የዘረመል ባንክ የሚያስተዳድረው ይኸው ኩባንያ ነው።

የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባው ፋብሪካ የኮሮና ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ሲውል የወባ እና የሳንባ ነቀርሳ መመርመሪያዎችን ወደ ማምረት እንደሚሸጋገር አስታውቋል።ኢትዮጵያ እስከ ትናንት መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ አንድ ሚሊዮን 130 ሺሕ 850 የኮሮና ምርመራዎች እንዳደረገች የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ ይጠቁማል። በአገሪቱ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር 63 ሺሕ 888 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 38 ሺሕ 397ቱ አሁንም ተሕዋሲው አለባቸው። ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እስካሁን 996 ሰዎች በኢትዮጵያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ትናንት ይፋ በሆነው መግለጫ መሠረት 345 ሰዎች በጠና ታመዋል።