ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመት ምሕረት፤
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ አሜን!
+ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
+ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
+ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
+ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
+ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣
እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከ እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓስራ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወበዝንቱ ተዓውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው በእንቲኣሁ፤ ወዝንቱ ውእቱ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር፡- የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ዘንድ ተገለጠ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነው፤ (፩ዮሓ. ፬፥፱)
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው እኛ ምሥራቃውያን ክርስቲያኖች በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል፣ የጌታችን የኣምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ነው፤ በዓለ ልደት የእግዚአብሔር ሰላምና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የታወጀበት ዕለት ነው፤ በዚህ ዕለት የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅርና ሰላም ቃላዊ ወይም ተምኔታዊ ኣልነበረም፤ ወይም ደግሞ በርቀት በመልእክት የተላለፈ ኣልነበረም፤
ከዚህ ይልቅ ሰብእናችንን በመዋሐድ፣ በተግባር ሆኖ በመገኘት፣ እንዲሁም ለመሰጠት ዝግጁ በመሆን የተገለጠና የታየ ሰላምና ፍቅር ነው፤ እግዚአብሔር የኛን ሰላምና ፍቅር በእጅጉ የሚሻው መሆኑን ለመረዳት፣ የኛን ሰብአዊ ክዋኔ በምልአት ተዋሕዶ በመካከላችን ከመገኘት የተሻለ ሌላ ማረጋገጫ ሊኖር ኣይችልም፤ እኛ ሰዎች ለእግዚአብሔር ጠላቶቹ ተብለን በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጽን ነን:: እግዚአብሔር ጠላቶቹን የራሱ አካል አደረጋቸው ሲባል ከመስማት የበለጠ አስደናቂ ነገር በዚህ ዓለም ምን ሊኖር ይችላል?
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እግዚአብሔር ሰብኣዊነታችንን በምልአት ተዋሕዶ በዓለማችን እንዲገለጥ የሆነበት ዋና ምክንያት እሱ እንዳስረዳን እኛ በሕይወት እንድንኖር ነው፤ ይህንንም ያደረገው ከሁሉ በላይ የሆነ ሌላ ገፊ ኃይል ገፋፍቶት ሳይሆን ድንበር የለሽና ፍጹም ፍቅሩ አነሣሥቶት እንደሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንረዳለን፤ የእግዚአብሔር ፍቅር እኛ ከምናውቀው ፍቅር ሁሉ በላይ መሆኑንም በዚህ እናስተውላለን፤ ለጠላቶቹ ሕይወት ፍቅርና ሰላም ሲል እነሱን ከመሆን አልፎ እስከ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚዘልቅ ፍቅር እጅግ በጣም ታላቅ ነው፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !
እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ እኛ በሕይወት በሰላምና በፍቅር እንድንኖርለት ከሆነ የእኛ ግብረ መልስም ከዚህ የተለየ ሊሆን ኣይገባም፤ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ለማዳን እንጂ ለማጥፋት አልመጣም፤ የእኛም ሕይወት የሚጠበቀው ኣንዱ ሌላውን በማዳን እንጂ በማጥፋት እንዳልሆነ ጌታችን በቃልም በተግባርም በኣጽንዖት ነግሮናል፤ በዚህ አስተሳሰብና እምነት እንድንኖርም አዞናል፡፡
ታድያ በቃሉ ለመኖርና ለእሱ ለመታዘዝ ቃል የገባን እኛ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ እርግፍ ኣድርገን በመተው እርስ በእርስ ለመጠፋፋት መሽቀዳደም ምን ይሉታል? ይህስ ለማን ይበጃል?
የአንድ ሀገር ሕዝቦች ይመካከራሉ፣ ይቻቻላሉ፣ ይታገሣሉ፣ ጊዜ ሰጥተው ያስቡና መፍትሔ ያበጃሉ እንጂ ማን በማን ላይ ይነሣል? ይህ ለማንኛችንም አይበጀንምና ወደ ኣእምሮኣችን እንመለስ የሚል ጥሪ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክት ነው፤
በመጨረሻም፤
ይህንን የተቀደሰ በዓል ስለ ሃገራችን ዘላቂ ሰላም በመጸለይና በማሰብ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ እጥረት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን በመደገፍና በመርዳት ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ለሀገር ኣንድነትና ለሕዝብ ፍጹም ሰላም መስፈን ከልብ በመነሣሣት በዓሉን እንድናከብር አባታዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን!!
መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ