ኢሰመኮ፣ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መያዝ ከሚችለው የተጠርጣሪዎች ቁጥር በላይ በመያዙ ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጥሯል አለ። ኢሰመኮ፣ ማረሚያ ቤቱ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠርጣሪዎችን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ለይቶ አለመያዙ “አሳሳቢ” እንደሆነ ገልጧል። በማረሚያ ቤቱ የተወሠኑ ዞኖች ለተጠርጣሪዎች በቂ የመንቀሳቀሻ ቦታ እንደሌለና ተጠርጣሪዎች እንዲይዙት የሚፈቀድላቸው ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን 200 ብር ብቻ መሆኑ አስፈላጊ ሸቀጦችን ለመግዛት በቂ እንዳልሆነ የጠቀሠው ኢሰመኮ፣ ማረሚያ ቤቱ ላንድ ተጠርጣሪ የእለት ቀለብ የመደበው 35 ብርም ምግብ ለማቅረብ በቂ አይደለም ብሏል። ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ የተጠርጣሪዎችን መጨናነቅ ለመቀነስ፣ ፍርድ የተሠጣቸው እስረኞች በአፋጣኝ ወደ ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ቀደም ሲል የተላለፈው ውሳኔ በፍጥነት ይተግበር በማለት አሳስበዋል።