‹‹ገብረ ወልድ ተቀናጣ
ወደ ሰማይ ፎቅ አወጣ››
የሚለው ዘመን ተሻጋሪ መንቶ ግጥም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመርያው ባለ አምስት ፎቅ እንደሆነ ለሚነገርለት ሕንፃ የተገጠመ ነበር፡፡
ከአራዳ ጊዮርጊስ በታች ወደ ደቡብ አቅጣጫ ከመጀመርያው የፖስታ ቤት ሕንፃ ‹‹አራዳ ፖስታ ቤት›› ፊት ለፊት በዘመኑ ገዝፎ ይታይ የነበረው ሕንፃ በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ወልድ እንግዳ ወርቅ የተገነባ ነበር፡፡ በ1940ዎቹ መገባደጃ የተወጠነውና የተገነባው ፎቅ በፒያሳ መሀል ጎልቶ ይታይ እንደነበር ይወሳል፡፡
‹‹የማይጨው ዘመቻና የጉዞ ታሪክ›› (1941) የሚል መጽሐፍ ያዘጋጁት ምክትል ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ወልድ በ1928 ዓ.ም. የማይጨው ጦርነትን አስመልክቶ በዚያው ሥፍራ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት የተደረገውን ምክክር በቃለ ጉባዔ መያዛቸው ለመጽሐፉ ግብዓት እንደሆናቸው የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ስለ አገራዊው ጦርነት ‹‹የመጀመሪያው›› ቃለ ጉባዔ አዘጋጅ እንደሆኑም ይወሳላቸዋል፡፡
እኚህ የጽሕፈት ሚኒስቴር አውራ የነበሩት ጸሐፌ ትዕዛዝ በአዲስ አበባ የመጀመርያውን ፎቅ መገንባታቸውም ይጠቅስላቸዋል፡፡ መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ በ1953 ዓ.ም. በታኅሣሥ ወር በተደረገው የነጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተገደሉት ከፍተኛ ሹማምንት እሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡
እሳቸው በተገደሉ በስድስተኛው ዓመት ሕንፃቸውን የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ከቤተሰቦቻቸው ገዝቶ ይገለገልበት ነበር፡፡ ከሕንፃው መግቢያ ተለጥፎ የነበረው የእብነ በረድ ላይ ጽሑፍ ማኅበሩ በ1956 ተመሥርቶ በ1959 ዓ.ም. ሕንፃውን መግዛቱ ተመልክቷል፡፡
በዘውዳዊው ዘመን የመታሰቢያ ድርጅቱ ምድር ቤቱን ለአሜሪካ ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ አከራይቶት እስከ ደርግ መምጣት ድረስ በቤተ መጻሕፍትነት አገልግሏል፡፡ ደርግ ከወረሰው በኋላ ‹‹የካቲት ቤተ መጻሕፍት›› ተብሎ በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ሥር ይተዳደር እንደነበር ይወሳል፡፡
ይህ ታሪካዊና ነባር ሕንፃ መሰንበታቸውን በ‹‹ልማት›› ሰበብ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ የከተማዪቱ የፎቆች መነሻ የሆነው ባለበት ሆኖ በአካባቢው እየተገባደደ ካለው የዓድዋ ፕሮጀክት ጋር ማስተጋበር አይቻልም ኑሯል የሚል ጥያቄም አስተያየትም የሰነዘሩ የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡
የቅርሶችን እንታደግ ድምፅ
ከሁለት አሠርታት በፊት ጀምሮ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃዎች ለ‹‹ልማት›› ተብሎ እንዲፈርሱ መደረጉ የየአገሪቱ የቅርስ ጥበቃ አዋጅና ድንጋጌዎች ያለመከበራቸው ማሳያ ሆኖ አልፏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ‹‹በሚያስደነግጥ ፍጥነት ታሪካዊ ቅርሶቿን እያጣች›› በመሆኑ አፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ለማይንቀሳቀሱ ቅርሶችም የተለየ ፖሊስና የአፈጻጸም መተግበርያ መንግሥት ማውጣት እንዳለበትም ከኢትዮጵያ ሚሌኒየም ዋዜማ (2000 ዓ.ም.) ጀምሮ ሲጠቆም ማስገንዘቢያም ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርሶች በመንታ መንገድ ላይ እንደሚገኙ፣ ጎልቶ እየታየ ባለው የልማት አካል ውስጥ ቅርሶች ካልተካተቱ በአደጋ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም ብለው የቅርስና የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎችና ተሟጋቾች ከአሥር ለበለጡ ዓመታት በተደጋጋሚ ቢያስተጋቡም ተሰሚነታቸው እምብዛም ነበር፡፡ ማሳያው በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲፈርሱ መደረጋቸው ነው፡፡ ዘንድሮም ይኸው ፈረሳ ቀጥሏል፡፡
አንቲካ ከሆኑት መካከል ዋቢሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው በሉምባርዲያ ስም የሚታወቀው የ90 ዓመቱ የሼኽ አህመድ ሳሏህ ሕንፃ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየፈረሰ ነው፡፡ ይህ አዲስ አበባ በተመሠረተች በ49 ዓመቷ የቆመው ሕንፃ በቅርስነት የተመዘገበ እንኳ ቢሆንም ከመናድ አልታደገውም፡፡
ተፈጥሮአዊ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ ተገቢው ትኩረትና ክብካቤ አግኝተው ለቀጣዮቹ ትውልዶች እንዲተላለፉ፣ ኅብረተሰቡም ስለቅርሶች ግንዛቤ እንዲያገኝ በማሰብ ከሦስት አሠርታት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር (ኢቅባማ) ነው፡፡ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ ለማድረግ ካደረጋቸው ተግባራት መካከል የማስገንዘቢያ መድረኮችን በየጊዜው ማዘጋጀቱ ተጠቃሽ ነው፡፡
የሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) ብተት ምክንያት በማድረግ «አዲስ አበባ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ በሚሌኒየሙና ከሚሌኒየሙ ባሻገር» የተሰኘ ሲምፖዚየም አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በወቅቱ በሲምፖዚየሙ ከቀረቡት ወረቀቶች አንዱ በታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ የቀረበው ነው፡፡ ሪፖርተር ተገኝቶ እንደዘገበው፣ በቅርስነት ተመዝገበዋል የተባሉት ሳይቀሩ በ‹‹ልማት›› ሰበብ እንዲፈርሱ መደረጋቸው፣ ጭርሱን የአዲስ አበባ አንድ የታሪክ ምሰሶ የሆነው የለገሀር ባቡር ጣቢያ ነባር ሕንፃ እንዲፈርስ መታሰቡ፣ ለሲምፖዚየሙ መዘጋጀት አንዱ ምክንያት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ስለ አዲስ አበባ ታሪካዊ ቅርሶች ቤቶች ጥናታቸውን አቀረቡ፡፡
‹‹የለገሃር ሕንፃ ይፈርሳል የሚል ነገር ተነስቶ ስለ ነበር እሱ ላይ አተኮርን፡፡ በጊዜው አንገብጋቢም ነበር፤›› በሚሉት ፕሮፌሰር ባህሩ ማብራሪያ፣ ‹‹ጥናቴን ሳቀርብ በአጋጣሚ የለገሃሩ ሕንፃ በ1921 ዓ.ም. ሲመረቅ የሚያሳይ አንድ ፎቶ አግኝቼ ነበር፡፡ ዓመቱ አውሮፕላንም የመጣበት ጊዜ ስለነበር ከላይ ፎቶ አንስቷል፡፡ በፎቶው ሦስት ቦታዎች ቁልጭ ብለው የሚታዩት አንደኛው ግቢ [ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት]፣ ሁለተኛው ጊዮርጊስ፣ ሦስተኛው ባቡር ጣቢያ ነው፡፡ ግራፊክ የሆነ ሥዕል አዲስ አበባ በሦስት ዓምዶች መቆሟን ያሳያል፡፡››
ለገሃርን ማፍረስ ከሦስቱ የአዲስ አበባ ዓምዶች አንዱን ማፍረስ በመሆኑ እሱንና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶችን ለመታደግ እንዲያስችል በሲምፖዚየሙ የታሪካዊ ቅርስ ኮሚቴ በሳቸው ሰብሳቢነት በመቋቋሙ ብዙ መታገላቸውን የለገሃሩም ሕንፃ ከመፍረስ መዳኑን ያስታውሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ምሰሶዎች
አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ከአክሱምና ጎንደር ቀጥላ ሦስተኛዋ መናገሻ ከተማ ልትባል የምትችል ናት፡፡ የአክሱምና የጎንደር ታሪካዊነት ጎልቶ ሲታወቅ፣ የአዲስ አበባ ግን እምብዛም አልታወቀም የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ የአዲስ አበባን ታሪካዊ ፋይዳን በሦስት የዕድገት ምዕራፎች ከፍለው ያሳያሉ፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ፡ ከ1928 ዓ.ም. በፊት ወይም ቅድመ ጣሊያን ወረራ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ የጥንታዊ ሕንፃዎችና ታሪካዊ ቅርሶች መሠረት የሆነው የአፄ ምኒልክ ግቢ (ታላቁ ቤተ መንግሥት) የተገነባበት ነው፡፡ ሌላው ማዕከል ደግሞ ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ ሥርዓት የተደረገበትና መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰኘበት ነው፡፡ ወደ ንግድ ማዕከልነት በመለወጥም አራዳን ሲወልድ፣ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችና ሕንፃዎች የተሠራበት ነው፡፡
ሦስተኛው ማዕከል ለገሀር ሲሆን የባቡር ጣቢያው ሕንፃ መሠረት አዲስ አበባን ዱሮ ከነበረችበት ወደ ታች ስቦ የደቡብ አዲስ አበባን ዕድገት በሙሉ በርሱ ዙሪያ በማሽከርከር በዘመኑ ውብ ሕንፃዎች የሕንድና ዐረባዊ ሥነ ሕንፃን ስልትን የተከተሉም ተሠርተውበታል፡፡ ከሁሉም የበለጠ ውበት ያላቸው እነዚኞቹ ናቸው፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ፡ የጣሊያን አገዛዝ ዘመን (1928-1933) ነው፡፡ በዚህም አዲስ ዓይነት የኪነ ሕንፃ ባህል ከመመሥረቱም ባሻገር፣ አዳዲስ ማዕከላት ተፈጥረዋል፡፡ አራዳ ወደ ፒያሳ መለወጡና መርካቶን መትከሉ ነው፡፡ የጣሊያኖቹ የራሳቸው አሻራ አላቸው በጣም ውብ አይባሉም፡፡ ግን አንድ ምዕራፍን ያሳያሉ፡፡
ሦስተኛው ምዕራፍ፡ ከኢትዮጵያ የ1933 ዓ.ም. ድል በኋላ የሚመጣው ሦስተኛው ምዕራፍ የ1948 ዓ.ም. የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥትን (ያሁኑ ብሔራዊ) ጨምሮ በርካታ ሕንፃዎች የተገነቡበትና የታደሱበት ዓረፍተ ዘመን ነው፡፡
ከጣሊያን በኋላ በ1950ዎቹ ልዩ አርክቴክት የታየበት ነው፡፡ አፍሪካ አዳራሽ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ማዘጋጃ ቤት (እጇን የዘረጋች ሴት የሚመስል) እነዚህም ሌላ ምዕራፍ ናቸው የከተማውን ታሪክ በደንብ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
‹‹ይሁን እንጂ፣ ታሪካዊ ቤቶችና ሥፍራዎች ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ አግኝተዋል ለማለት በእጅጉ ያዳግታል፡፡ በተለይ የበለፀጉ አገሮች ቅርስንና ዕድገትን ያለምንም ችግር ለማቀናጀት መቻላቸውን ስናይ፣ እኛስ እንዲህ ለማድረግ ለምን ይሳነናል የሚለው ጥያቄ ዘወትር በአዕምሯችን የሚጉላላ ነው፡፡ እንኳን ረዥም ታሪክ ያላቸው የአውሮፓ ከተሞች ይቅርና፣ በቅርቡ የተፈጠሩት የአሜሪካ ከተሞች እንኳን ያቺኑ ያለቻቸውን ታሪክ ሲንከባከቡና ሲያሽሞነሙኑ፣ እኛ ግን ታሪክ እያለን ታሪክ የሌለን ሆነን የመቅረት አደጋ እያንዣበበብን ነው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ በተለይ ከጣሊያን በፊት የተገነቡት ቤቶች የተለየ ሥነ ሕንፃዊ ውበትን የተጎናፀፉ ሲሆኑ፣ ከቸልታ የተነሣ በየዓመቱ በፊታችን እየተሰወሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ የራስ ናደው፣ የሻቃ በልሁ፣ (ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም አጠገብ የነበረ) የደጃዝማች ብሩ ኃይለማርያም (ጣሊያን ትምህርት ቤት ጀርባ የነበረ) ያሉት ቤቶች ፈርሰው ደብዛቸው መጥፋታቸውን ያነሳሉ፡፡
‹‹ስለታሪካዊ ቅርስ ስናነሳ የደጃዝማች ቤት የምናስከብር ነው የሚመስላቸው፡፡ የደጃዝማች ቤት ስለሆነ ሳይሆን የአንድ ዘመን ኪነ ሕንፃ (አርክቴክቸር) ይወክላል፡፡ በኮንክሪትና በመስታወት ሕንፃ መሥራት ይቻላል እንደዚያ ዓይነት ቤቶች አይሠሩም፡፡ በቅርስነት ማቆየት ያስፈልጋል እያልን ነው ለማስረዳት የሞከርነው፡፡ ቁም ነገሩ ከባለቤቶቹ ሳይሆን ከቤቶቹ ነው፡፡›› የድሮዎቹ ውበቶች ሲጠበቁ ነው ሕይወትን የሚያጣፍጡት፡፡
ዘንድሮ ሠላሳኛ ዓመቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር፣ ሥራዎቹንና ቅርሶችን ጨምሮ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በተመለከተ ልዩ መጽሔት አውጥቷል፡፡ በዚያው መጽሔት ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ቅርሶች ሕጉም አልጠበቃቸውም ተሿሚዎቹም አልሠሩም ምን መደረግ አለበት?›› ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡
‹‹በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ሲፈርሱ ማየት በጣም የሚዘገንን ነው፡፡ ሚኒስቴሪያል የሆነ ቅርስን የሚመለከት የቅርስ ጥበቃ ካውንስል ካልተቋቋመና ካልተናበቡ ዕርምጃም መውሰድ ካልቻሉ በስተቀር ሕግ ማውጣትና ማስመዝገብ ብቻውን እንደማይበቃ አይተናል፡፡ በግል ወይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ደረጃ የሚቻለው ተሞክሯል፡፡ ጡንቻ ያለው ማስፈጸምም ማገድም፣ እንዳይፈርስ ማድረግ የሚችል ኃይል መቋቋም አለበት፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ እሱን እንዴት ማድረግ እንደምንችል አላውቅም፡፡
‹‹በሌሎች አገሮች ታሪካዊ የቅርስ ቤቶች በጣም የሚከበሩ እንደ ብርቅ የሚታዩ ፈጽመው የማይነኩ ናቸው፡፡ በተለይ የጀርመንን ምሳሌ ነው ያመጣሁት፡፡ የድሮ ከተሞች /ራትሐውስ ይሉታል፡፡ እምብርት የሆኑ የጥንት ማዕከሎች በደንብ ነው የሚጠበቁት የእግር መንገድ እንጂ መኪና አይገባባቸውም፡፡ ቤቶቹ ለተለያዩ አገልግሎቶች ቡና ቤት፣ ሲኒማ፣ ቡቲክ ሲውሉ የድሮ መልካቸው ሳይቀየር ነው፣ የፖርቶሪኮ ዋና ከተማ ሳንዋን ጥንታዊነቷን ይዛ በዩኔስኮም የቅርስ ቦታ ሆናለች፡፡ ስለዚህ እኛም የእነርሱን መንገድ መከተል አለብን፡፡ ብዙዎቹ ግን እየተደመሰሱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ግን አዲስ አበባ ሬስቶራንት፣ ፊንፊኔ አዳራሽ፣ ራስ ብሩን የመሳሰሉት መጠበቅ እንደሚቻል ምልክት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበርን ከመሠረቱት ባለሙያዎች አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ አንዱ ናቸው፡፡ ስለ አዲስ አበባ ከተማና ኪነ ሕንፃዊ ቅርሶች ከተመሠረተችበት ከ1879 አንሥቶ እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ የነበራትንና ያላትን ገጽታ የሚያሳይ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ‹‹Addis Ababa from 1886-1941, the City and Its Architectural Heritage›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2007 አሳትመዋል፡፡ ይህንኑ መጽሐፍ በማስፋፋት ‹‹The City and Its Architectural Heritage ADDIS ABABA La Ville et son Patrimoine architectural›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ በፎቶግራፎች ጭምር የታጀበ ግዙፍ መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ2019 ከፎቶ ባለሙያው ዴኒስ ጄራድ ጋር በመሆን አሳትመዋል፡፡
ስለ ቅርሶች በተለይም ስለ ኪነ ሕንፃ ሙያዊ ገለጻና ምክረ ሐሳብ በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ቅርስ፣ ልማትና ተግዳሮቱን በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች ካንፀባረቋቸውና ሪፖርተር ከዘገባቸው ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
‹‹በማደግ ላይ ያለን አገር ስንሆን ‹ዕድገት/ልማት› የሚለውን ቃል አዳዲስ ሕንፃ ከመሥራት፣ ‹አሮጌ› የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ከአሉታ ጋር ያያይዙታል፡፡ ያረጀ የሚል ስሜት ይሰጡታል፡፡ ከኋላ ቀርነት ጋር ያስተሳስሩና ያንን ባስወገድንና አዲስ በገነባን ቁጥር ልማት አመጣን የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ግን አንድ የማይገነዘቡት ነገር አለ፡፡ በዚህ በእኛ ሙያ በኪነ ሕንፃና በከተማ ልማት ላይ ያለን ሰዎች እንደምንለው፣ እያንዳንዱ ዘመን የራሱ የዕድገት ደረጃ የሚያስቀምጠው አሻራ አለው፡፡ ኋላ ቀር የምንላቸው የምንንቃቸው በዘመናቸው በጣም የተከበሩና የተደነቁ ሥራ ነበሩ፡፡
‹‹የድሮ ከተማ የታሪካችን ነፀብራቅ፣ ዕድገታችንና የመጣንበትን መንገድ በተጨባጭ የሚያሳየን ነው፡፡ ረቂቅ ብቻ ሳይሆን በጠጣሩ ኮንክሪት በሆነ መንገድ የሚነግር ነው፡፡ ይኸን የተረዱ አገሮች በከተማ ዕድገታቸው ላይ ያንፀባርቁታል፡፡ አዲሱንም ይሠራሉ፡፡ የድሮውንም ይጠብቃሉ፡፡ ከየት ወዴት እንደመጡ ይታያል፡፡ እነዚያን ሕንፃዎች ይገለገሉባቸዋል፡፡
‹‹እኛ ተከታታይ ከሆነው ዕድገታችንና ከታሪካችን ጋር አንዳንዴም የተጣላን ይመስለኛል፡፡ ቅርስ በውስጡ የያዘውን መልዕክትና ጥቅም ካለመረዳት ወደ አዲሱ የማድላት ነገር አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በመንግሥትም በኩል የሚሾም ማንኛውም ባለሥልጣን ወይም በቦታው ያለ የባህል ሚኒስቴርን ሊጨምር ይችላል፡፡ ደከም ባለ አቅም ላይ ነው የሚገኙት፡፡
‹‹በምጣኔ ሀብት አስተሳሰብ ከተወሰደ የቅርስ ይዘቶች ያላቸው ታሪካዊ ሕንፃዎች በከተማው ውስጥ የያዙትን ቦታ ብንገምት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች እንደ አገር እንደ ሕዝብ እንደ ሥልጣኔ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉን አይደሉም፡፡ ጥቅማቸውም እንዲያውም በዚያኛው ከምናገኘው የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ግንዛቤው ሲኖረን፡፡ አሁን ችግሩ ግንዛቤው ስለሌለ ላልማ፣ አዲስ ልሥራ ላስፋፋ የሚለው መሬቱን ብቻ እንጂ ከላዩ ያለው የቅርስ ሀብት፣ ትውፊት ሌላውም ነገር የመረዳቱ ነገር ገና ነው፡፡ የተረዳው ሰው አያደርገውም፣ ሁለቴ ያስባል መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ትልቁ ችግር ያን ቅርስ ካጠፋኸው መልሰህ አታገኝም፡፡ አዳዲስ ሕንፃዎችን ደጋግመን መሥራት እንችላለን፤ እነዚያ ቅርሶችን ግን አንዴ ከምድረ ገጽ ካጠፋናቸው ተመልሰው አይመጡም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ተግዳሮት ይፈጥራሉ፡፡
መሥራች አባል የሆኑለት የቅርስ ባለ አደራ ማኅበር ሦስት አሠርታትን ማስቆጠሩን ተከትሎ ከወራት በፊት ባስተላለፉት መልዕክት ለአገራዊ ቅርሶች የሕግ ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው በአፅንዖት ከመጠቆም አልተቆጠቡም፡፡
‹‹እንደ አንድ አገር፣ እንደ አንድ በማደግ ላይ ያለሁ፣ ሥልጡን ነኝ፣ ታሪክ አለኝ የሚል ሕዝብ ለነዚህ ቅርሶች ቦታ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ጠንካራና ቁርጠኛ የሆነ አቋም መውሰድም ይገባዋል፡፡ መንግሥትም የሕግ ከለላን በአስቸኳይ መፍጠር አለበት፡፡ የሕግ ከለላ የፈጠሩ አገሮች ቅርሳቸውን በመከላከላቸው በሠሩት ሥራ ዛሬ ይኮሩበታል፡፡ እኛ ይህንን ባለማድረጋችን ጊዜው እያለፈብን ነው፡፡ ሃያ፣ ሠላሳ ዓመት እያለፈ ሲሄድ የምናፍርበትን ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡
‹‹አንዳንዴ ቀድመህ ነቅተህ ወደፊት ምን ሊመጣ ይችላል የሚለውን ስትናገር ከባድ ነው፡፡ ቀድመን አውቀን ግንዛቤውን አግኝተን ብንሠራ ጥሩ ነው፡፡ የመንግሥት አካላትም የባህል ተቋማትም ሌሎችም የቅርስ ጥበቃን መደገፍ ይገባቸዋል፡፡ ይሄ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊነት ብቻ አይደለም፣ የሁላችንም እንጂ፡፡ ይሄ የአንድ ድርጅት ጥቅም ሳይሆን የጋራ ነው፡፡ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ከተማ መቆርቆር ያለብን ነገር ነው፡፡
ሠላሳኛ ዓመቱን የተሻገረው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር (ኢቅባማ)፣ ክብረ ዓመቱን አስመልክቶ በቦርድ ፕሬዚዳንቱ አማካይነት ባስተላለፈው መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
‹‹ኢቅባማ የተቋቋመበት ዓላማ ታሪካዊ ቅርስ የሆኑ ተደናቂነት ያላቸውን ሕንፃዎችንና ሥፍራዎችን ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የታሪካችን ቋሚ ምስክር የሆኑ አዲስ አበባ ስትመሠረት የተገነቡ ጥንታዊ ቤቶች በቅርስነት ተመዝግበው እያሉ ትኩረት በማጣት እንዲፈርሱ እየተደረጉ ነው፡፡ ሕጉም ጠንካራ ባለመሆኑ ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ ማኅበራችን በተደጋጋሚ ጩኸቱን ቢያሰማም ሰሚ አላገኘም፡፡ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ትጋቱን ይቀጥላል፡፡
‹‹ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ መጪው ትውልድም እንዲደሰት፣ እንዲጠቀም እና ካለፈው ትሩፋት እንዲማር ይሠራል። ቅርሶችን መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ እንዲሁም ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል ኃያል መንገድ ነው፡፡ የአገራችንንም አልፎም የዓለምን ሕዝቦች በጋራ እሴት ዙሪያ አንድ ያደርጋል፡፡
መሰንበቻውን እየፈረሱ ያሉትን ሕንፃዎች ካስተዋሉ የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች አርክቴክት ባይሞት ጸጋዬ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹የአዲስ አበባን አፍርሶ የመገንባት ጉዳይ›› በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ በሰጡት ሙያዊ ትንታኔ እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹በአንድ የከተማ አካባቢ የተሻለ ‹Sense of Place› (ሴንስ ኦፍ ፕሌስ/ መካነ ትውስታ) የሚፈጠረው በአዲስ ‹ውብ› ሕንፃ ስለተተካ ብቻ አይደለም፡፡ የካሳንቺስ አካባቢን አፍርሶ በአዳዲስ ‹ውብ› ሕንፃዎች ቢተካም የቀድሞው ትውስታ ጠፍቷል፡፡ አዲስ የተሻለ ሴንስ ኦፍ ፕሌስ ሊፈጠር አልቻለም፡፡ ይህም የሆነው ስለ ‹ከተማ ዲዛይን› አስፈላጊነት ፖለቲከኞቹ ዕውቅና ባለመስጠታቸው ነው፡፡ የከተማ ፕላኒንግና የከተማ ዲዛይን ተደጋጋፊ ቢሆኑም፣ የከተማ ፕላኒንግ የከተማ ዲዛይንን አይተካም፡፡ በእርግጥ በፖለቲከኞች ዘንድ የከተማ ዲዛይን ዕውቅና ቢያገኝ ኖሮ ታሪካዊ ሕንፃዎችን እና ታሪካዊ አካባቢዎችን ‹ለተሻለ ልማት ተብሎ› መፍረስ ባላስፈለገ ነበር፡፡
‹‹ታሪካዊ ሕንፃዎችን እና ታሪካዊ አካባቢዎችን ከመጪው የከተማ ዕድገት ጋር ማጣጣም (Urban Revitalization) የከተማ ዲዛይን አካል ይሆን ነበር፡፡ ነባር አካባቢዎችና ግንባታዎች በዘመናት የማያቋርጥ ማስተካከያና ማሻሻያ ብዛት ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ በመሆን ለሰው ልጅ ፍላጎት ወደ ፍጹምነት የቀረቡ በመሆናቸው እንዲፈርሱ አይመከርም፡፡ ይልቁንም የዘመናዊ ግንባታዎች የፅንሰ ሐሳብ (Theory) ምንጭ በመሆን ማመሳከሪያዎች ናቸው፡፡