ንግድ ባንኮች እንደገና የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደገጠማቸው ከባንክ ባለሙያዎች መረዳቱን ጠቅሶ ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል። የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት የተፈጠረው፣ ባልተመጣጠነ የቁጠባና ብድር ምጣኔ፣ በዋጋ ግሽበት፣ በአስገዳጅ የመንግሥት ሰነዶች ግዥ፣ በመንግሥት ብድር መጨመርና በመዋቅራዊ ችግሮች ምክንያት እንደኾነ ባለሙያዎች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የውጭ ምንዛሬና ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ የሚልኩት ገንዘብ አነስተኛ መኾኑ እንዲኹም የወጪ ንግድ አፈጻጸም መዳከሙ፣ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው የባንክ ባለሙያዎች አስረድተዋል ተብሏል። ከአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ፣ የባንክ አካውንት ያላቸው ዜጎች ከ31 በመቶ እንደማይበልጡ የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።