የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክንያት የነበራቸውን “ግጭት” በማስቆም “ሰላም” ማምጣታቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ ይህንን ያሉት በሥልጣን ዘመናቸው ጣልቃ በመግባት ያስቆሟቸውን ግጭቶች በመዘርዘር እሁድ ሰኔ 8/2017 ዓ.ም. ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸውን ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው።
ትራምፕ፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተቀሰቀሰውን የእስራኤል እና የኢራን ግጭትን ትኩረት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሕንድ እና ፓኪስታን በቅርቡ ገብተውበት የነበረውን ግጭት “ከአሜሪካ ጋር የሚደረግን ንግድ” በመጠቀም፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ወደ “ምክንያታዊነት፣ ቅንጅት እና ቀልባቸው” እንዲመጡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ “ሁለቱ ምርጥ መሪዎች በፍጥነት መወሰን እና መቆም ችለዋል” ሲሉ የነበራቸውን ሚና ገልጸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸውም በሰርቢያ እና ኮሶቮ መካከል “ለአስር ዓመታት” የቆየውን እና “ጦርነት ሆኖ ሊፈነዳ ጫፍ ደርሶ የነበረውን ግጭት” ማስቆማቸውን ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚሁ ጋር አያይዘው ያነሱት “ሌላኛው ኬዝ” ሲሉ የጠቀሱትን ኢትዮጵያ እና ግብፅን ጉዳይ ነው። ሁለቱ ሀገራት “በግዙፍ ግድብ ምክንያት ግጭት ውስጥ” እንደነበሩ በመልዕክታቸው አስፍረዋል። ግድቡ፤ “በአስገራሚው የናይል ወንዝ ላይ ተጽዕኖ ያለው” እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል “ሰላም አለ፤ በእኔ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ቢያንስ አሁን ላይ [ሰላም አለ]። እናም እንዲህ ሆኖ ይቆያል!” ሲሉ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
“እንደዚህ ሁሉ” በእስራኤል እና በኢራን መካከል “በቅርቡ ሰላም እንደሚፈጠር” በማመልክት “አሁን በርካታ ጥሪዎች እና ስብሰባዎች እየተካሄዱ ነው” ብለዋል።
“ብዙ ነገር አከናውኛለሁ። ለየትኛውም ጉዳይ እውቅና አግኝቼ አላውቅም። ግን ምንም አይደለም፤ ሕዝቡ ይረዳዋል። መካከለኛው ምሥራቅን በድጋሚ ታላቅ እናደርጋለን” በማለት ጽፈዋል።
ትራምፕ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል “ሰላም ማምጣታቸውን” ቢያነሱም ፕሬዝዳንቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ የነበራቸው ሚና በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚነሳው በአሉታዊ ጎኑ ነው።
ትራምፕ በ2013 ዓ.ም. በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ወራት ላይ ግብፅ ግድቡን “ልታፈነዳ ትችላለች” የሚል ንግግር ማድረጋቸው ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የትራምፕ ንግግር የቆጠረው “በሥልጣን ላይ ባለ” የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደተደረገ “የጦርነት ቅስቀሳ” ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዝዳንቱ ንግግር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት “የማያንጸባርቅ” እንዲሁም “በሀገረ መንግሥታት መካከል የሚደረጉ ንግግሮችን በሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ሕጎች ተቀባይነት የሌለው” እንደሆነ ገልጾ ነበር።
በወቅቱ መንግሥት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ማይክ ራይነርን የትራምፕን ንግግር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጎ እንደነበረም አይረሳም።
በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ “ኢትዮጵያ አስቀድሞም ሆነ ወደፊት በሉዓላዊነቷ ላይ ለሚቃጡ ጥቃቶች እንደማትንበረከክ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር የሦስትዮሽ ድርድርን ለመቀጠል ቁርጠኛ እንደሆነች” ለአምባሳደሩ እንደገለጹላቸው ይፋ ተደርጎ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያ ለማንኛውም ዓይነት ትንኮሳ እጅ እንደማትሰጥ” አስታውቆ ነበር።
ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የህዳሴው ግድብ ሙሌትን ማከናወኗም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እርምጃ ያስከተለ ጉዳይ ነበር።
አሜሪካ ሙሌቱ ተከናወነው ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ስምምነት ሳይደረስ መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረው እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ለማቋረጥ እንደወሰነች ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተሳተፉበት እና በየካቲት 2012 ዓ.ም. የተካሄደው የዋሽንግተን ድርድር ላይም የትራምፕ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ፍላጎት የሚቃረን አቋም ይዞ እንደነበር በወቅቱ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብፅ ወግነው መቆማቸውን ገለጹት ምንጮች ሁኔታውን የገለጹት ኢትዮጵያ “4 ለ 1” በሆነ ሁኔታ እንተሟገተች በመጥቀስ ነበር።
ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ የተገኘችው በግድቡ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ላይ ለመነጋገር ቢሆንም፤ በአሜሪካ በኩል “ማን ምን ያህል የውሃ ድርሻ ይኑረው” የሚለውን የሚመለከት ክፍል የያዘ ሰነድ እንደቀረበ ምንጮች ገልጸው ነበር።
በዚህም ምክንያት ሀገራቱ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ድርድሩ የተበተነ ሲሆን፣ አሜሪካም የትራምፕ ንግግር እና የአስተዳደራቸው እርዳታ የማቋረጥ ውሳኔ የመጣው ከዚህ በኋላ ነበር።
ከትራምፕ በኋላ በመጡት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን አሜሪካ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የጎላ ሚና ሲኖራት አልተስተዋለም።
በጆ ባይደን የሥልጣን ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ እና ግብፅ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ ተደጋጋሚ ድርድሮችን በሚያደርጉም ስምምነት ላይ አልደረሱም። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግድቡ ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን በ2016 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ የውሃ ሙሌቱን ተጠናቅቋል።
ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጪው 2018 ዓ.ም. መጀመሪያ ይመረቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።