ዶ/ር ደብረ ጽዮን በትግራይ ምርጫ ‘በአስቸኳይ’ እንዲካሄድ ጠየቁ

የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በትግራይ ክልል ምርጫ ‘በአስቸኳይ’ እንዲካሄድ ጠየቁ።

በፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት መሠረት በትግራይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን መምራት የሚችለው ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት መሆኑን ዶ/ር ደብረጽዮን በህወሓት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ግንቦት 21/ 2015 ዓ.ም በወጣው ጽሁፍ አስታውሰዋል።

“ራስን በራስ ማስተዳደርን መሠረት በማድረግ በአስቸኳይ ወደ ምርጫ መሄድ አለብን” ብለዋል የህወሓት ሊቀመንበር።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሥራውን አጠናቆ ቀሪውን ሥራ በሕዝብ ለሚመረጠው መስተዳደር ማስተላላፍም እንዳለበት መናገራቸውም በጽሁፉ ሰፍሯል።

“የነበረው አመራር ለሰላም ሲባል ፈርሷል” ያሉት ዶክተር ደብረ ጽዮን የትግራይ ሕዝብ በሚመረጣቸው አመራሮቹ ሊመራም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ህወሓት ማስተዳደር የለበትም ቢባል እንኳን፣ የትግራይ ሕዝብ በሚመርጣቸው መሪዎቹ ሊተዳደር ይገባል” ሲሉም መናገራቸው ሰፍሯል።

የህወሓት ሊቀመንበር በሰጡት አስተያየት ላይ እስካሁን ከጊዜያዊው የክልሉ አስተዳደሩ የተሰጠ አስተያየት የለም።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሁለት ወራት በፊት መቋቋሙ ይታወሳል።

በተዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖርን ውክልናን በተመለከተ 30 በመቶ ለህወሓት፣ 25 በመቶ ለትግራይ ሠራዊት፣ 15 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ቀሪው ለምሁራን እና ለሲቪክ ማኅበራት እንደሚሰጥም ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

በትግራይ ውስጥ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ በሽብርተኛ ቡድንነት ተፈርጆ የነበረው ህወሓት፣ የሽብተኝነት ፍረጃው የተነሳለት ቢሆንም ከምርጫ ቦርድ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

በአመጽ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፏል በሚል በጦርነቱ ወቅት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን የሕጋዊ ፓርቲነት ምዝገባን ሰርዞ ከቆየ በኋላ፣ ሕጋዊ ዕውቅናው እንዲመለስለት በተጠየቀበት ጊዜ የተሰጠው ምላሽ ፓርቲው አልተቀበለውም።

ህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ዕውቅናው እና የተወረሱ ንብረቶቹ እንዲመለስለት በጠየቀበት ጊዜ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለው ሕጋዊ አማራጭ እንደገና መመዝገብ እንዳለበት መግለጹ ይታወሳል።

ፓርቲውም ይህንን የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበለው እና እንደአዲስ እንደማይመዘገብ አሳውቁ ጉዳዩ መቋጫ ሳያገኝ በእንጥልጥል ይገኛል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነቱ በኋላ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ ግንቦት 03/ 2015 ዓ.ም. መጀመሩን አስታውቋል።

የቦርዱ ባለሙያዎች በትግራይ ክልል ካሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ምርጫ ለማካሄድ ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል እና በፀጥታ ችግር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚቀጥለው ዓመት 2016 ዓ.ም. ምርጫ ለማካሄድ እንደታቀደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሳምንታት በፊት መግለጹ ይታወሳል።

ቦርዱ ይህንን የገለጸው በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የ2015 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።

ነገር ግን በትግራይ ክልል እና ምርጫ ባልተካሄደባቸው ሌሎች አካባቢዎች ምርጫው መቼ ሊካሄድ እንደሚችል የተባለ ነገር የለም።