ብልፅግና እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ የህዝብ ውይይት በማካሄድ ፋኖ ያገኘውን ህዝባዊ ቅቡልነት ለማንኮታኮት ስብሰባው ቀጥሏል

ብልፅግና ፋኖን ለመበተን አስቦ ባዘጋጀው ባለ 52 ገፅ የትግበራ ሰነድ ከተቀመጡት ተግባራት መካከል እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ የህዝብ ውይይት በማካሄድ ፋኖ ያገኘውን ህዝባዊ ቅቡልነት ማንኮታኮት ዋነኛው ነው።

ትላንት ግንቦት 04 ቀን 2014 ዓ.ም በርዕሰ- መስተዳድሩ የተመራው የባህርዳሩ ህዝባዊ ስብሰባም የዚህ አካል ነው። ” ርዕሰ መስተዳድሩ መንግስት ሰላም ለማስከበር በቁርጠኝነት ሲሰራ ህዝቡ ሊተባበረን ይገባል አሉ” የሚለውን አሚኮ ርዕሰ አንቀፅ ያደረገበት ምክንያትም ይኸው ነው። ይህ ስብሰባ በሁሉም ወረዳወች እና የቀበሌ ማዕከላት ይቀጥላል። መድረኮች ቢያንስ እስከ ግንቦት 10 እንዲጠናቀቁ እቅድ ተይዟል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ፋኖ የክልሉ የሰላም ስጋት አይደለም። በፋኖ መደራጀት ምክንያት የተፈጠረ አንዳችም የፀጥታ ችግር ሆነ የተስተጓጎለ ልማት የለም። የኑሮ ውድነቱ፣ የማዳበሪያ ዋጋ መናር እና እጥረት፣ የአዲስ አበባው ድምፅ አልባ ወረራ፣ የህወሃት የጦርነት ዝግጅት፣ በርካታ የክልሉ ግዛቶች በህወሃት እጅ መኖር እና በአጠቃላይ የአማራ ህዝብ የደህንነት ስጋት ዋና ዋና አጀንዳወቻችን ሊሆኑ በተገባ ነበር። ይሁን እንጅ የአማራ ብልፅግና እነኝሀ ሁሉ ጉዳዮቹ አይደሉም። ይልቁንም የፋኖ መኖር እና መደራጀት እንደልቤ ተጋልቤ (ተላልኬ) እንዳልኖር እንቅፋት ይሆንብኛል የሚለውን ብቸኛ ስጋቱ አድርጎ ተቀብሏል።

በተዘጋጀው የትግበራ ሰነድ መሰረት ፀረ-ፋኖ ዘመቻውን የሚመሩት የዞን አስተዳዳሪወች ናቸው። ይህንን በቀላል ምሳሌ ብናዬው ምስራቅ ጎጃም ላይ አንድ የፋኖ አባል በፀጥታ ኃይል ቢታሰር ወይም ቢገደል ኃላፊነቱን የሚወስደው ወንድም አብርሃም አያሌው ይሆናል ማለት ነው። በሌላው አካባቢም እንደዛው።

መድረኮች የተለመደ ተሳታፊ ብቻ እንዲገኝባቸው እና “መንግስት ህግ ያስከብርልን” የሚለው በሚዲያ እንዲጮህ የተወሰነ ቢሆንም የአማራ ህዝብ ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ በመድረኮች በመገኘት እንዲሞግት እና የሀገር ሽማግሌወች እና የሐይማኖት አባቶች ሴራውን ሳይረዱ የብተና ፕሮጀክቱ ተባባሪ እንዳይሆኑ በንቃት ይሰራበት።

መላው የፋኖ አባል፣ ወጣቶች እና አክቲቪስቶች፣ የምንኖረው በህዝባችን ብርታት እንደሆነ በማመን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ህዝቡን ያማከለ ይሁን።

የሚዲያ ተቋማት፣ ዩቱበሮች እና ምሁራን አዲስ ትውልድ! አዲስ አስተሳሰብ! አዲስ ተስፋ!ለግዜዉ ሌሎች አጀንዳወችን ወደ ጎን ብላችሁ ይህን አደገኛ ፕሮጀክት የማክሸፍ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባችሁ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

የብልፅግናን የፋኖ ብተና እቅድ እንዳይተገበር ማድረግ ለአማራ ህዝብ ህልውና እና ለዘላቂ ሰላም መሰረት ነው ሲሉ ጠበቃ አስረስ ማረ ዳምጤ ከትበዋል።

አሻራ ሚዲያ