ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ::

ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ::

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ከሕዳር 11—12 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በፓርቲ ውሕደት፣ በፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ኢሕአዴግ ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበ ድርጅት ነው፡፡ የድህነት ምጣኔን በመቀነስ፣ ተከታታይና ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና በመሳሰሉት ጉልህ ስኬቶችን ማስመዝቡም ይታወቃል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍም በትምህርትና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት መልካም ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ ይሁን እንጂ በስኬቶቹ ልክ በርካታ ጉድለቶችም የተስተዋሉበት መሆኑን መገምገማችን ይታወሳል፡፡ በተለይም በብሔራዊ ማንነት እና በሀገራዊ አንድነት መካከል ሚዛን ጠብቆ በመሄድ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን በማረጋገጥ፣ እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ጉድለቶቹ የበዙ ነበሩ፡፡

እንደዚሁም አርብቶ አደሩን የሀገራችንን ክፍል የወከሉ ድርጅቶች “አጋር” በሚል አግላይ አሠራር በሀገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ የማይሰጡ የሩቅ ተመልካች እንዲሆኑ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ለውጡን መምራት የሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወከሉበት፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሚሳተፉበት፣ ዘመኑን የዋጀ የነገ ፓርቲ በመሆን እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ለማድረግ ራሱን ፈትሾ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የፕሮግራም ማሻሻያ ማድረግ የግድ እንደሚለው በየጊዜው ሲካሄዱ በነበሩ ጉባኤዎችና ድርጅታዊ መድረኮች አቅጣጫ ሲቀመጥ ቆይቷል፡፡

በድርጅቱ 11ኛ መደበኛ ጉባኤ የፓርቲ ውሕደት አጀንዳ አንኳር ከነበሩት የውይይት አጀንዳዎች ተጠቃሽ ነበር። በጉባኤውም የውሕደት ሂደቱ ከሚገባው በላይ የተጓተተ መሆኑን በመገምገም ጥናቱ በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል። የኢሕአዴግ ምክር ቤትም ጥናቱን እንዲፋጠን በማድረግ ተከታትሎ በማስፈፀም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ይታወቃል።

በዚሁ መሠረት ጥናቱ በዘርፉ ልምድና የካበተ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን ተካሂዶ ለየብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት፣ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይትና አስተያዬቶች ተሰጥተውበት እየዳበረ እንዲመጣ ተደርጓል። የኢሕአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም ውሕደቱ በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች አባላትና አመራር ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሁም በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተከናወነ ስለመሆኑ በተናጠል ባደረገው ጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሕዳር 06 እስከ 08/ 2012 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥናቱ ላይ ዝርዝር ውይይት አድርጎ በአብላጫ ድምጽ ካጸደቀው በኋላ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለምክር ቤቱ አስተላልፏል። ምክር ቤቱም በአሠራሩ መሠረት ለሁለት ቀናት ባካሄደው ውይይት የውሕደት ውሳኔ ሐሳቡን፣ የፓርቲውን ፕሮግራምና ሕገ ደንብ በዝርዝር ካየና ካዳበረ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ ውሕድ ፓርቲው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት ቀሪ ሂደቶችን በፍጥነት አጠናቅቆ የቆመላቸውን ዓላማዎች ወደሚያሳካባቸው ተጨባጭ ሥራዎች እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችም አስቀምጧል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፍ እስካሁን የነበረው የኢሕአዴግ አደረጃጀትና ፕሮግራም የአቃፊነት ጉድለት የሚታይበት በመሆኑ የባለቤትነት እና የባይተዋርነት አሰላለፍን እንደፈጠረና ይህም ድርጅቱን እና ሀገራችንን ወደ ከፋ ክፍፍል ያመራና ፅንፈኝነትን እየወለደ የሄደ መሆኑን በመገንዘብ አቃፊ የፖለቲካ አቅጣጫን መከተል እንዳለበት በማመን ነው፡፡ ለተፈጠረውም ሀገራዊ ችግር መፍትሔው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑበት፤ በሀገራቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወስኑበት ኅብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መገንባት እና የቡድንና የግለሰብ መብቶች ተጣጥመው የሚሄዱበት የፖለቲካ ዓውድ መገንባት መሆኑን ምክር ቤቱ አምኖበታል።

ውሕደቱ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥና እመርታ የሚያመጣ የአንድነት፣ የአብሮነትና የእኩልነት መንፈስን የሚፈጥር ነው። የፓርቲ ውሕደቱ ሁሉንም የሚያካትት፣ ተደራሽና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሳይገደብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ በመፍጠር ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ያስችላል። በተጨማሪም የቡድንና የግል መብትን እንዲሁም ብሔራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣም በሕገ መንግሥታችን ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው።

ውሕድ ፓርቲው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ግዙፍ ዓላማ ማዕቀፍ ውስጥ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በዘላቂነት ለማሟላት ጥራትና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋግጥ፣ የሕዝቦችን ድህነት፣ እርዛትና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በሀገራችን እውን ሆኖ ለማየት የሚሠራ ፓርቲ ነው። ለዴሞክራሲ ባሕል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ባሕልና ተቋማት በመገንባት፣ የሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠባት ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም ፓርቲው ከሚታገልላቸው ቁልፍ አጀንዳዎች አንዱ ነው። በማኅበራዊ ልማት መስክም መልካም ሀገራዊ እሴቶችና ባሕሎችን በማዳበር በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን መፍጠር፣ የማኅበረሰብ ጤና ተጠብቆ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሠላም ተፈጥሮ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ይተጋል።

መላው የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፤
ድርጅታችን በታሪኩ ያስመዘገባቸውን መልካም ስኬቶች በማስቀጠልና ስህተቶችና ድክመቶችን በማረም የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ ፓርቲ ይሆን ዘንድ ትግል ስታደርጉ ቆይታችኋል። እነሆ ትግላችሁ ፍሬ አፍርቶ ኅብረ ብሔራዊ ቅርፅና አካታችነት መገለጫው የሆነ ሀገራዊ ፓርቲ ለመሆን በቅተናል። በመሆኑም ምክር ቤታችን ለዚህ አዲስ ምዕራፍ በመብቃታችን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል።

ውሕደቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራላዊና ኅብረ-ብሔራዊ ሥርዓትን እውን የሚያደርግ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማንነታቸው በተገቢው መልኩ እውቅና አግኝቶ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ የሚሆንበት፤ በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ሥርዓት እውን እንዲሆን እና ሁሉም የሚሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት ስለሆነ ለስኬቱም መላ አባላትና ደጋፊዎቻችን ከምንጊዜው በላይ ርብርብ እንድታደርጉ ምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርብላችኋል።

ለአጋር ድርጅቶች አመራርና አባላት፤
በኢሕአዴግ ጉባዔዎች ጨምሮ በሁሉም የፓርቲ መድረኮች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ እንዳትሆኑ መታገዳችሁ አሳማኝ ምክንያት የሌለው አግላይ አካሄድ መሆኑን በማንሳት ስትታገሉ ቆይታችኋል። ኢሕአዴግም የዚህን ጥያቄ ተገቢነት በማመን ለማስተካከል ከወሰነ ዓመታት አልፈዋል። ይህን በመፈፀም ረገድ የነበሩ እግር የመጎተት ችግሮች አሁን ተፈትተው ለዚህ ታሪካዊ ቀን በመድረሳችሁ የኢሕአዴግ ምክር ቤት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል። እንኳን ለዚህ የአጋርነት ታሪክ ምእራፍ የተዘጋበትና አካታች አዲስ የትግል ምዕራፍ የተሸጋገራችሁበት መድረክ አበቃችሁ።
ውሕድ ፓርቲው ሁላችንም በእኩል የምንታይበትና የምንሳተፍበት አዲስ ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ለመቀየር በሚያደርገው ርብርብ በጋራ ጠንክረን እንድንሠራ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፤
በሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መደማመጥ፣ መቻቻል፣ መከባበርና ሚዛናዊ ትብብርና ፉክክር መገለጫው የሆነ የሰለጠነ ፖለቲካ በሀገራችን እውን እንዲሆን፣ የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ እንዲቀር መሥራት ውሕድ ፓርቲው ከሚታገልላቸው አጀንዳዎች ውስጥ ዋነኛው ነው። በመሆኑም እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲሰፍን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሠራን በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ ደግሞ በሰለጠነ፣ ሠላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተደራደርን ችግሮችን በመፍታት አገራችንን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የበኩላችሁን ገንቢ ሚና ትጫወቱ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

መላ የሀገራችን ሕዝቦች፤
ፓርቲያችን አሁን የደረሰበት ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው ሳይገደቡ፤ ቤተኛና ባይተዋር ሳይሆኑ እኩል የሚሳተፉበት የሁሉም መታገያ መድረክ ለመሆን ከመብቃቱም በላይ ይህንኑ እውን የሚያደርግ ፕሮግራም ይዞላችሁ ቀርቧል።

ውሕድ ፓርቲያችን ሁሉንም ብሔሮች የሚያሳትፍና ከቀደመው አግላይ አካሄድ የምንማርበት፣ የሕዝብን ጥያቄ በተናበበ ሁኔታ የምንመልስበት፣ በፓርቲ ውስጥ መግባባትን በማጠናከር አጠቃላይ በአገራችን ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችለን በመሆኑ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት እውን የሚሆንባት፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደረገው ርብርብ ሁሉ ድጋፋችሁ እንደማይለየው ፓርቲያችን እርግጠኛ ነው። በመሆኑም ብዝኃነታችንን ጠብቀን ለበለፀገች ኢትዮጵያ ግንባታ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሠራ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት
ሕዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ