በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጉቶ ጊዳ እና ሱቡ ሶሬ ወረዳዎች የንጹሓን እያለቂት ቀጥሏል!

በወለጋ አማራዎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእልቂት ቀጠናነት ደጋግሞ የተነገረ ሲኾን ትንሽ በረድ ብሎ የከረመው አኹን ላይ ተቀስቅሶ ከኹለት ሣምንት በፊት 8 ንጹሓን በአሰቃቂ ኹኔታ የተገደሉ ሲኾን አራቱ እስከአኹን የት እንደደረሱ አይታወቅም። የአኹኑ በዋናነት በጉቶ ጊዳ ወርዳ ጃርቶ ቶሌራ፣ ፈይሳ፣ አርጆ፣ ሎኮ፣ ሊጎና ወጤ ቀበሌዎች ሲኾን በሱቦ ሱሬ ወረዳም በተለይ ደንገጆ ጉዮ ቀበሌ ዋነኛ የእልቂትና የጥቃት አካባቢዎች ናቸው፡፡

በአካባቢዎቹ እልቂቱ ቀጥሎ ሰኞ፣ ሰኔ 9 ንጋት ጀምሮ ደግሞ 9 ሰዎች የተገደሉ ሲኾን መቅበር እንኳን አልተቻለም፤ በርካታ ንብረትም ተዘርፏል፡፡ በአካባቢው ነዋሪዎች አጠራር “ሸኔ” ነው ግድያውን የፈጸመው። ነዋሪዎች ውጭ ነው የሚያድሩት፣ የመንግሥት አካል እንዲደርስ ብንጮኽም ሰሚ አላገኘንም፤ ግድያው አማራውንም ኦሮሞውንም እየጨረሰ ቢኾንም የዞንና የወረዳ አመራሮች ግን ሰውን በማንነቱ እየመረጡ እንዲሸሽ ያደርጋሉ፡፡ መከላከያውም አኹን እልቂቱ ከሚካሄድበትና ይበልጥ አስፈሪ ከኾነበት በ 5ኪ.ሜ ርቀት ውኬ ቀርሳ ላይ ያለ ቢኾንም በሕዝቡ ጥያቄ መሠረት እንቅቃሴ ጀምሮ ሳለ በዞን አመራሮች እንዲመለስ ተደርጓል የሚሉት ነዋሪዎች ቢያንስ ሕጻናትና ሴቶችን እንኳን ፈቅደው ወደ አጎራበች ቤንሻንጉል ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ቢደረግልን ለዘር እንተርፋለን ብለዋል፡፡ እስከዛሬ በተቻለን አቅም ራሳችንን ስንከላከል ኖረናል አኹን መሣሪያችንም ተነጥቋል፤ ወዲኽ ደግሞ “ሸኔ” እየተጠቀመው ያለው የርቀት መሣሪያ ጭምር ከገበሬው አቅም ጋር ሲነጻጸር ፍጹም ሰማይና ምድር ነው ይላሉ፡፡

ፓርቲያችን ግድያውን አውግዞ በኹለቱ ወረዳ ያለው ሕዝብ ከማለቁ በፊት መከላከያው ወደቦታው እንዲሰማራ፣ ሕዝቡም በሕጋዊ አግባብ ራሱን የሚከላከልበት አማራጭ እንዳይነፈገው ብሎም በዞንና ወረዳ አመራሮች እየተደረገ ያለው ተስማምቶ በኖረ ማኅበረሰብ መሐል በመግባት ማንነትን ማዕከል ያደረገው የእልቂት ጠመቃና ሚዲያ ጭምር በመጠቀም የሚደረጉ መሰል የፍጅት ቅስቀሳዎች እንዲቆሙ አበክረን እናሳስባለን፡፡