­

ከእስራኤል እና ከኢራን ጦርነት ባሻገር . . .

ከእስራኤል እና ከኢራን ጦርነት ባሻገር . . .

ከእስራኤል እና ኢራን ጦርነት ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ስጋቶች ውስጥ አንዱ ኢራን ምናልባት የሆርሙዝ ሰርጥን ልትዘጋ ትችላለች የሚለው አንዱ ነው።

የሆርሙዝ ሰርጥ ምንድን ነው?

የሆርሙዝ ሰርጥ አለማችን ላይ ወሳኝ ከሚባሉ የንግድ መተላለፊያዎች ውስጥ ዋነኛው ሲሆን ኢራንን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ከኦማን የሚለይ 167 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሰርጥ ነው።

ሰርጡ አስፈላጊ የሆነው የአለም ከ20-30 በመቶ የነዳጅ ሽያጭ የሚያልፍበት እና በቀን ከ20 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ በላይ በየቀኑ የሚሸጋገርበት መስመር በመሆኑ ነው።

የኢራን እና እስራኤል ጦርነት መካረርን ጨምሮ ኢራን ሰርጡን ልትዘጋ ትችላለች የሚል ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

ኢራን ሰርጡን ከዘጋች ምን ሊፈጠር ይችላል?

⛽️  የነዳጅ ዋጋ መናር

የዓለም ዋና ዋና የሚባሉ የነዳጅ ላኪ ሃገራት የነዳጅ ምርታቸውን ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ ይህንን ሰርጥ ሲጠቀሙ የሰርጡ መዘጋት ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን የነዳጅ መጠን በመቀነስ ዋጋው እንዲጨምር ያደርገዋል።

በጦርነቱ ጅማሬ ብቻ ከ7 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ያሳየው ነዳጅ ሰርጡ ተዘግቶ ጦርነቱ ከቀጠለ ዋጋው በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል።

በዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎች ሰርጡ እንኳን ሳይዘጋ በኢራን የኃይል ማዕከላት ላይ የሚፈፀም ጥቃት በራሱ የነዳጅ ዋጋን እስከ 90 ዶላር በበርሜል ሊያደርሰው እንደሚችል ግምታቸውን ሲሰጡ፤ ሰርጡ ከተዘጋ የነዳጅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ ሊንር ይችላል የሚል ስጋት አይሏል።

ከዚህ በፊት በእስራኤል የአረብ ጦርነት ወቅት የነዳጅ ዋጋ በ300 % ጨምሮ እንደነበር ይታወሳል።

የዋጋ ጭማሪው እና የአቅርቦት እጥረት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ነዳጅን ከውጪ የሚያስገቡ ሀገራት እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ሃገራት ተጨማሪ የኑሮ ውድነትን በማዋለድ የራስ ምታት ይሆናል።

⛵️ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር

ቀይ ባህር የአለማችን ወሳኝ የንግድ መስመር ሆኖ እያገለገለ ያለ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አሚፂያን በሚወስዷቸው ጥቃቶች የተነሳ ሚናው እየቀነሰ ነው።

የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት የዓለምን የነዳጅ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚቀንሰው ሲጠበቅ በቀይ ባህር በኩል የሚደረጉ የንግድ ዝውውሮችንም ውድ እና አደጋ አዘል ያደርጋቸዋል።

🇷🇺 ሩሲያ እና ሰርጡ

ዓለማችን ላይ አሉ ከተባሉ የነዳጅ አምራች ሃገራት አንዷ የሆነችው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለችው ውጊያ የተነሳ ወደ አውሮፓ የምትልከው የነዳጅ ምርት እገዳ ተጥሎባታል።

ሆኖም የሆርሙዝ ሰርጥ ተዘግቶ የነዳጅ እጥረት ከተፈጠረ እና ዋጋው ከጨመረ ሃገራት በተለይ አውሮፓውያኑ የግድ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ ሊያዞሩ ይችላሉ።

በማዕቀብ ኢኮኖሚዋ የተጎዳው የፑቲን ሀገርም በነዳጅ ገቢ ጦሯን ማጠናከር እና ከዩክሬን ጋር ያለባትን ውጊያ ማጠናከር የምትችልበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል።

🤩 ነዳጅ እና አሸባሪነት

በባህር ላይ የሚጓጓዝ ነዳጅ የአሸባሪዎች እና የሽፍታዎች ዋነኛ ኢላማ ሲሆን በዚህኛው ጦርነት የባህር ሽፍታዎች ነዳጅ የጫኑ መርከቦችን ኢላማ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ከዚህ በፊት ሲገለፅ እንደነበረውም ኢራን አማፂያንን በመደገፍ ሰርጡን ከመዝጋት በተጨማሪ የነዳጅ አቅርቦትን ልታስተጓጉል ትችላለች።

ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የኢራን መንግስት ሰርጡን ለመዝጋት እያጤነ ያለ ሲሆን ፤ የመዝጋቱ ሃሳብ ተቀባይነት ካገኘ እና ሰርጡ ከተዘጋ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ያመጣል።

ተንታኞች ይህ ከሆነ እና የነዳጅ ዋጋ ከናረ አሜሪካ ለራሷ ጥቅም ስትል ጦርነቱ እንዲያልቅ ልታደርግ ትችላለች የሚል መላምትን ያስቀምጣሉ።

አምስት ቀናት ያስቆጠረው ይኸው የሁለቱ ሀገራት ጦርነት እየተባባሰ ቀጥሏል። እንደሌሎቹ ጦርነቶች የተራዘመ ጦርነት እንደማይሆን ብዙዎች ቢያስቀምጡም ወደየት እንደሚያመራ መገመት ግን አዳጋች ይሆናል።

Source: Sputnik,EIA, Freightwaves, Economymiddleeast