የሰኔ 15ቱ የግድያ ወንጀል ምርመራ መጠናቀቁ ተነገረ፡፡

የሰኔ 15ቱ የግድያ ወንጀል ምርመራ መጠናቀቁ ተነገረ፡፡

የአማራ ክልል የሠላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በፀጥታው ዘርፍ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

(አብመድ) ሰኔ 15 2011ዓ.ም የተከሰተው የመሪዎች ግድያ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ እንዳለፈ የገለጹት አቶ አገኘሁ በ2011ዓ.ም ዜጎች በሠላም የማይንቀሳቀሱበት ዓመት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የደረሰውን ችግር ለማለፍ ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጋራ በመሆን የፀጥታ መዋቅሩን በማደረጃት ችግሩን ማለፍ እንደተቻለም አንስተዋል፡፡ ክልሉ በዚህ ወቅት ግን የተረጋጋ እንደሆነንና ከቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡ አሁንም በክልሉ በግበዓት እና በሰው ኃይል አደረጃጀት በኩል ሥራዎች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል፡፡

‹‹የክልሉ ችግር ውስጣዊና ውጫዊ ነው›› ያሉት አቶ አገኘሁ የውጩን ችግር ለመቋቋም የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የክልሉን ሠላም ለማናጋት ‹ሌት ከቀን› የሚሠሩ አከላት እንዳሉ የገለጹት አቶ አገኘሁ በተለይም በለውጡ የተገፉ አካላት የሚፈጥሩትን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላተዋል፡፡

ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሉ ጋርም በጋራ እየተሠራ እንደሆነና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ አቋሙ እንሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተም በተለይም ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ጋር ያለው ቅንጅት መልካም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል የጋራ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም እየተሠራ እንደሆነ ገልጸው ከአፋር ክልል ጋርም ባጋራ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም ከአፋር ክልል መንግሥት ጋር የጋራ ምክክር እንደሚኖርም አስታውቀዋል፡፡

‹‹የቅማንት ብሔረሰብን የራስ አስተዳደር ጥያቄ አጀንዳ በሌሎች አካላት ተነጥቀን ለብዙ ችግር ተጋልጠናል›› ያሉት አቶ አገኘሁ ችግሩን ለመፍታት ሠላማዊ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ አብዛኛው የኮሚቴ አባልም በሠላም እንደገባ ያነሱት ኃላፊው በቅርቡ ውይይት እንደተደረገና ከኮሚቴው እና ከክልሉ ከተውጣጡ ኮሚቴዎች ጋር ምክክር በማድረግ ችግሩ በዘላቂነት እንደሚፈታም ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ የማይታለፉ መስመሮች እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ሞትና እና መፈናቀል ይብቃ›› ሲሉ አጽንዖት የሰጡት አቶ አገኘሁ የክልሉ መንግሥት ለማንኛውም ነገር መሰዋዕት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በሰኔ 15 የግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ አካላት አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አስታውቀዋል፡፡ በታክቲክ፣ በቴክኒክ፣ በሰው ማስረጃና በፎረንሲክ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት የተሰበሰበው መረጃ እንደተጠናቀቀና በቅርቡም ለሕዝቡ ይፋ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ችግሩ ታስቦበት፣ ክህደት የተፈጸመበትና ለስልጣን ጥም የታሰበ ነው›› ያሉት አቶ አገኘሁ ወንጀሉ ውስብስብ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በወንጀሉ ተጠርጥረው የነበሩ ዜጎች ዋስትና የሚገባቸው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ እንደወጡ የገለጹት አቶ አገኘሁ በወንጀሉ ተሳታፊ በሆኑ ተጠርጣሪዎች ላይ በቅረቡ የፍርድ ቤት ክስ እንደሚጀመርም አመላክተዋል፡፡ ምርመራውን ካካሄደው የምርመራ ቡድን መካከል 75 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ፖሊስና ዐቃቢያነ ሕግ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡
በሃይማኖት በኩል የሚከሰተውን አለመግባባት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ እንደሆነ ገልጸው ሕግን የሚጥሱ ላይ የየትኛውም የሃይማኖት ተከታይ ይሁኑ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱም አመላክተዋ፡፡

የማኅበረሰብ ፖሊስና የልዩ ኃይል ስልጠና በእቅድ እንደተያዘና በቅርቡም ወደሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራበት እንደሆነም አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል፡፡ ሕግን ለመስከበር እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ወጣቶች ያመሰገኑት አቶ አገኘሁ በጥቅም እየተታለሉ የማኅበረሰቡን ሠላም የሚያውኩ ጥቂት ወጣቶችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

በሌሎች ክልሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሌሎች ክልሎች ርዕሳነ መስዳድሮችና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ የተከሰተው ችግር የሥራ ኃለፊዎች ችግር እንደሆነ ገልጸው ‹‹የውስጡን ካጸዳን የሚመጣውን የውጭ ኃይል ለማስቆም አንቸገርም›› ብለዋል፡፡ የፖሊስ አባላትም በሙያቸውና በሚችሉት አቅም እንዲሠሩ በቅርቡ የለውጥ ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡