የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርዳታ እህል እንደሚዘረፍ አውቃለሁ አለ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርዳታ እህል እንደሚዘረፍ ለበርካታ ዓመታት ያውቅ እንደነበር በምርመራ ማረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል።

ድርጅቱ ርምጃ ያልወሰደው፣ መንግሥት በጦርነቱ ወቅት ወደ ትግራይ የሚገቡትን የእርዳታ ካሚዮኖች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል በሚል ስጋት እንደነበር መረዳቱን ዘገባው ጠቅሷል።

የተዘረፈው የእርዳታ እህል ለመንግሥት ወታደሮችና ለሕወሓት ተዋጊዎች እንደሚውል ይታወቅ እንንደነበርም ከአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የውስጥ ሰነድ መመልከቱን ዜና ምንጩ አመልክቷል።

ትግራይ ውስጥ የተዘረፈው የዕርዳታ እህል 450 ሺሕ ተረጂዎችን ላንድ ወር መመገብ የሚችል 7 ሺሕ ቶን ስንዴ እንደሆነ ከክልሉ ባለሥልጣናት መስማቱንም ዘገባው ጠቅሷል።

ይህንኑ ተከትሎ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራምን በትግራይ ከዕርዳታ አከፋፋይነት ለማስወጣት አቅዷል ተብሏል።