ምዕራብ ጎጃም ለሁለት ተከፈለ

ቀደም ሲል የምዕራብ ጎጃም ዞን በ14 የገጠር ወረዳዎችና በስምንት የከተማ አስተዳደሮች ተዋቅሮ ማዕከሉን ፍኖተ ሰላም አድርጎ ሲተዳደር ነበር። ሆኖም አንዳንድ ወረዳዎች ከማዕከሉ የራቁ በመሆናቸው አስተዳደራዊ ሥራዎችን ለማከናወን ነዋሪዎቹ ተቸግረው እንደቆዩና «ዞን ይከፈልልን» ጥያቄያቸውን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ እንደ ነበር ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ሆኖም ከብዙ ጊዜ በኋላ ጥያቄው ቢመለስም ማዕከሉ ባሕር ዳር መሆኑ ተገቢ እንዳልነበር ከምክንያታቸው ጋር የነገሩን የአዴት ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ ይሔነው ዐወቀ ናቸው።

«ዞኑ በጣም ሰፊና ለማስተዳደርም አስቸጋሪ ስለነበር ለሁለት መከፈሉ ትክክል ነው፣ ሆኖም ማዕከሉ በስሩ ካሉ ወረዳዎች በአንዱ መሆን ነበረበት ምክንቱም ያ ከተማ የማደግና ዘመናዊ የመሆን ዕድል ይኖረው ነበር፣ ባሕርዳር ከተማ መሆኑ ግን ለኃላፊዎች ምቾት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።» የብዙዎቹ ወረዳዎች ነዋሪዎች ጉዳይ ለማስፈፀም ወደ ፍኖተ ሰላም ሲጓዙ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደርን ተሻግረው ይሄዱ እንደነበር የገለፁልን ደግሞ የዱር ቤቴ ከተማ ነዋሪውና የአስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ውበት ጥላሁን፤ ጥያቄው በመመለሱ ኅብረተሰቡ ደስተኛ እንደሆነ አስረድተዋል። የሰሜን ጎጃም ዞን ማዕከል ባሕር ዳር መሆኑንም ለሁሉም የአዲሱ ዞን ማዕከል በመሆኑ ተስማምተን ያደረግነው ነው ብለዋል።

ጉዳዩን ሲያስተባብሩ ከነበሩ የኮሚቴ አባላት መካከል አቶ አበረ ዓለሙ ኅብረተሰቡ ያመነባቸው አመራሮች ዞኑን እንዲመሩ መሾማቸውን ጠቅሰው በዚህም ኅብረተሰቡ ደስተኛ አንደሆነ ነው ያመለከቱት። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ «አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የዞንና የወረዳ ይከፈልልኝ ጥያቄዎች ተገቢ እንዳልሆኑ ጠቁመው የምዕራብ ጎጃም ዞን ለሁለት መከፈሉ ግን ትክክለኛና ተገቢ ነው።» ብለዋል። የክልሉ ርእሰ መስተዳድርም ለዋና ዋና የሥራ ኃላፊዎች ሹመት መስጠታቸውን ተናግረዋል። አዲሱ የዞን አመራርም ከሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ ም ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው ያረጋገጡት። የባሕር ዳር ከተማ የአዲሱ ዞን ማዕከል የሆነውም አማካይ ቦታ በመሆኑ ወረዳዎቹ ራሳቸው ተስማምተው ያደረጉት እንደሆነ ነው ያስረዱት። አዲስ የተዋቀረው የሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜንና ደቡብ አቸፈርን፣ ሰሜንና ደቡብ ሜጫን፣ ይልማና ዴንሳን፣ ጎንጂ ቆለላንና ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳዎችንና የመራዊ፣ ዱርቤቴና አዴት ከተማ አስተዳደሮችን ያቀፈ ነው፣ አዲሱ ዞን ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የያዘ እንደሆነ ታውቋል።