በደቡብ ክልል በበረከቱት የክልል እንሁን ጥያቄዎች ላይ ምክክር ተደረገ

DW : አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጁት መድረክ በደቡብ ክልል በበረከቱት የክልል እንሁን ጥያቄዎች ላይ መክሯል። በውይይቱ የተጋበዙ የሲዳማ ልሂቃን ሳይገኙ ቀርተዋል።

በክልል ደረጃ ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ብሄር ብሄረሰቦች በውስጣቸው ያሉ ሌሎችን አናሳ የብሄርና ብሄረሰብ አባላት እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ግልጽ የተቀመጠ ነገር አለመኖር እና በተለይ ደግሞ ደቡብ ተብሎ ብዙዎች በአንድ ላይ ሆነው በተዋቀሩበት ክልል የውክልናና የስልጣን ክፍፍሉ ግልጽ መስፈርቶች አለመኖራቸው ነው ሲሉ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የተባሉ የህግ ምሁር ተናገሩ።

በሌላ በኩል የብሄረሰቦችን መብት የሚደነግጉት የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 እና 47 እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ጭብጦች ያሉት መሆኑም መሰል ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል። ሃገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የስዊዘርላንድንና የህንድን የፌዴራል አወቃቀርና የችግር አፈታት መንገዶች ጊዜ ወስዳ ብትመለከት መልካም ነው ተብሏል። መሰል ጥያቄዎች ይዘውት የሚመጡት ችግር ከባድ በመሆኑ በልዩ ጥንቃቄ እንዲታይም ተጠይቋል። ይህንን በተመለከተ ዛሬ በተደረገ ውይይት የህገ መንግስት ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚገባም ሃሳብ ተሰንዝሯል።

በዚህ ውይይት ላይ የደቡብን በተለይ የሲዳማን ጉዳይ በተመለከተ ሃሳቦች ተሰንዝረው የተንጸባረቁ ሲሆን ፣ ጥያቄው የረጅም ጊዜ እና ነባር ቢሆንም ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ስለመሆኑ ተነስቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት የተጠየቀው ምርጫ ቦርድ ምንም ማለት እንደማይችል የቀረበለትን ህዝበ ውሳኔ ተቀብሎ የማደራጀትና የማስፈጸም ሃላፊነት ብቻ እንዳለው አብራርቷል።

DW