የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ፓርቲ ኢዜማ አራት ከፍተኛ አመራሮቹን አገደ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ህገ-ወጥ ሰነድ አዘጋጅተው አሰራጭተዋል ብሎ የጠረጠራቸውን የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር ጨምሮ 4 አባላቱን አገደ። የታገዱት አመራሮች ከልደቱ ፓርቲ ኢዴፓ ተገንጥለው ወደ ኢዜማ የፈረሙ ናቸው። አስተያየት ሰጪዎች የታገዱት አመራሮች ኢዴፓን በፖለቲካ ሴራ ሲያምሱ ኖረው አሁን ደግሞ ኢዜማ እየበጠበጡ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ባልደራስና ኢዜማ ውስጥ በርካታ በደሕንነት ቢሮ ተከፋይ የሆኑ የፖለቲካ ሰዎች እንዳሉ መረጃዎች አሉ።

በፓርቲው የሥራ ኃላፊዎችና በአባላቱ ላይ እግድ የጣለው የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው፡፡ግለሰቦቹ የሳምንት ሥራ መከታተያ ቅፅ በሚል ህገ-ወጥ ሰነድ አዘጋጅተው ግንቦት 2/ 2014 ዓ.ም በብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የዋትስ አፕ ግሩፕ ላይ በመላክ ተጠናክረው መታገዳቸው ሸገር ከፓርቲው ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውም ከትናንት በስትያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ መክሮ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ሰነዱ ፍፁም ስህተት እና የፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሂደት ዲሞክራሲያዊነትን የሚያቀጭጭ ብሎታል በውሳኔው፡፡በመሆኑም ሰነዱን አዘጋጅተዋል ተብለው የተጠረጠሩት 4 የፓርቲው አባላት በሰነዱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎና የህግ ጥሰታቸው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለፓርቲው ህገ ደንብ ትርጉምና ዲሲፕሊን ኮሚቴ ተመርቷል ተብሏል፡፡

ጉዳዩ በኮሚቴው ተመርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስም ፡-

• የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ መምሪያ ሀላፊው አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ
• የፋይናንስ መምሪያ ሀላፊው አቶ አንድነት ሽፈራሁ
• የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደና
• አባል የሆኑት አቶ ኢዮብ መሳፍንት ከሀላፊነታቸው ለጊዜው እንዲታገዱ ወስኗል። ( ሸገር ራዲዮ)