በቤተክርስቲያን ላይ በአንዳንድ ካህናት፣ መነኮሳትና ጳጳሳት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተበራከቱ

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ለበርካታ ዘመናት በቤተክርስቲያን ላይ በአንዳንድ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ጳጳሳት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እግር በእግር በማጋለጥና መወሰድ ስለሚገቡ እርምቶች የምድረ በዳ ጩኸት ሲያሰሙ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከውጭ የሚመጡባትን ወረራዎችንና ጥቃቶች እየመከተች በማሸነፍ ሉዓላዊነቷንና ክብሯን ጠብቃ ከሁለት ሽህ ዓመታት በላይ ቆይታለች። ሆኖም ከውስጥ ሆነው ዝሙት በመፈጸም፣ ሴቶችን በመድፈር እንዲሁም ጸያፍና አስነዋሪ ድርጊቶችን በማድረግ ህዝብ እንዲሸሻትና እንዲጠላት የሚያደርጓት ካህናት እጅግ ከፈተኛ ፈተና ሆነውባታል። ይህ ጉዳይ በግላዥጭ አደባባይ አይውጣ እንጅ ምዕመናን በየቤታደው የሚምከነከኑበትና የሚያዝኑበት ከሆነ ውሎ አድሯል። እንዲንከባከቧቸውና እንዲጠብቋቸው አደራ የተሰጣቸውን የምዕመናን አደራቸውን በልተውና ዕምነታቸው አጉድለው ዝሙት በመፈጸም ቤተክርስቲያንን እያደሙና እየገዘገዙ ያሉ ካህናትና መነኮሳት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ከዛሬ 11 ዓመታት በፊት አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ በመትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝሙት መፈጸሙ በማስረጃ የተረጋገጠበትን ታደሰ ሲሳይ የተባለ ግለሰብ ተወግዞ ስልጣነ ክህነቱ እንዲዘረዝ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሆኖም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል ከታደሰ ሲሳይ ጋር በመመሳጠር የተላለፈው ውግዘት እንዳይጸናና ግለሰቡም በዝሙት ተጨማልቆ ቤተክርስቲያንን ማርከሱንና ማቆሸሹን እንዲቀጥልነት አድርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ የሲኖዶስ አባል የሆነው “አቡነ” ኤውስጣጢዎስ የተባለው ግለሰብ ዋሽንግተን ሲያትል ውስጥ በሚገኘው Orthodox Church in America መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ከዛሬ 12 ዓመታት በፊት ከሁለት ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸሙ በማስረጃ ተረጋግጦበት ከኮሌጅ መባረሩ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቀሲስ አስተርአየ የግለሰቡን በዝሙት ምክንያት ከኮሌጅ መባረር አስተመልክቶ የተጻፈው ደብዳቤ ከኮሌጁ ተልኮላቸው ስለነበር ግለሰቡ ከክህነት አገልግሎት እራሱን እንዲያርቅ ቢመክሩትም በማን አለብኝነት ዝሙቱን እየፈጽመ ቤተክርስቲያንን እያረከሰ ይገኛል። አቡነ ፋኑኤል ግለሰቡ በዝሙት ምክንያት ከኮሌጅ እንደተባረረ እያወቁ አብረው በመቀደስ ለዝሙቱ ድርጊቱ ድጋፍ ሰጥተዋል።

ሰሞኑን የተሰማው ጆሮ ጭው የሚያደርግ እጅግ አስደንጋጭ ወንጀል አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ ካህን መፈጸሙን ምዕመናን ከሰሙት ጀምሮ ወሬው በከፍተኛ ፍጥነት ተሰራጭቶ ሚዲያውን በሙሉ ተቆጣጥሮታል። የዚህኛው የዝሙት ወንጀል እጅግ አደገኛ የሚያደርገው ዕድሜዋ ለእቅመ ሔዋን ካልደረሰች ልጅ ላይ በጉልበት (በትራስ በማፈን) መሆኑ እራሷ ወንጀሉ የተፈጸመባት ሴት አስታውቃለች። ይህንን ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ አቡነ ፋኑኤል እንደ ታደሰ ሲሳይና ሌሎች ዝሙት ፈጻሚዎችን ሸፍነው       እግዚአብሔርና ህዝብን አጭበርብረው ማለፍ የሚችሉ አይመስለም። ሆንም ምዕመናን ለኃይማኖታቸው ቀናኢ በመሆን ዝሙት የሚፈጽሙና ቤተክርስቲያንን የሚያቆሽሹ ወሮበሎችን መታገል ይጠበቅባቸዋል። “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።” ማቲዎስ 14፡15  ስለሆነም በዝሙትና በተለያዩ ወንጀሎች የወደቁ ካህናት እንኳንስ ምዕመናንን ሊታደጉና ሊያድኑ ለራሳቸውም አዳኝ፣ መሪ፣ መካሪና አጋዥ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ከስራቸው ታውቃላችሁና ተጠንቀቁ እንደተባለው ነጣቂና የውሸት ካህናትን ከአውደ ምህረት እየጠረገን ማስወገድ አለብን። ኃይማኖት ዋጋ ያስከፍላልና እንዲሁ እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ የሚመጣ ለውጥ የለም። ለኃይማኖት መቆርቆር ጊዜን፣ ትኩረትን፤ገንዘብንና ፅናትን ይጠይቃል። የቀደሙ አባቶች ቤተክርስቲያኒቷን እዚህ ያደረሷት የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈሉ እንጅ እንዲሁ ተቀምጠው በማየትና ከንፈር በመጠጥ አይደለም።

በአስቸኳይ መደረግ ያለበት በአሜሪካ ህግ የተፈጸመው ወንጀል ተጣርቶ ልጇቷ ፍትህ እንድታገኝ ማድረግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሚስጢራዊነቱ በተበቀ ሁኔታ ዝሙትና ሌላም ወንጀሎች በቤተክርስቲያን ላይ የፈጸሙ ካህናት ላይ ጥቆማ የሚያደርግ የስልክ መስመርና ድረ ገጽ መቋቋም ይገባዋል። አንዳንድ አንቱ የተባሉና ሰገንት ላይ የወጡ የዘመኑ ካህናት፣ መምህራንና ቆሞሳት ህጸጽ ያላባቸውና ለክህነት ከክህነት አገልግሎት መወገድ የሚገባቸው አሉ። በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚፈጸሙ የዝሙት ወንጀሎች እጅግ ስር እየሰደዱና እየጨሩ ስለመጡ ቤተክርስቲያን ለመከላከል ጥረት መደረግ አለበት። እንደሚታወቀው በአቡነ ማቲያስ የሚመራው ሲኖዶስ የወደቀና በፖለቲካ ሴራ የተተበተበ የመንግስት መገልገያ መሳሪያ ስለሆነ ከሱ የሚጠበቅ ነገር የለም። ዋናው የችግሩ መንስዔም ሲኖዶሱ ውስጥ በዝሙት፣ በሌብነት፣ በዘረኛነትና በተለያዩ ወንጀሎች የተጨማለቁ ጳጳሳት ተብየዎች የተሰገሰጉበት ተቋም መሆኑ ነው። ስለሆነ የአሁኑ ሲኖዶስ ህገ ቤተክርስቲያንን ያፈርሳል እንጅ ይጠብቃል ይከላከላል ተብሎ አይጠበቅም። ቀሲስ አስተርአየ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በታደሰ ሲሳይ ላይ የዛሬ 11 ዓመት ያስተላለፉትን የውግዘት ውሳኔና ሰሞነኛውን የቤተክርስቲያን ሁኔታ አስመልክተው በቱንቢ ሚዲያ ላይ ከመምህር ፋንታሁ ዋቄና ከዲያቆን ዮሴፍ ከተማ ጋር ያደረጉትን ቃል ምልልስ አቅርበንላችኋል። በቀድሞው ቀሲስ ታደሰ ሲሳይ ላይ የተላለፈ ውግዘት ማርች 2014