” ለምሳሌ የካ ክፍለ ከተማ ወደ 100 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን በማስረጃዎች አረጋግጠናል፤ ወደ ቦሌ ወደ 200 የሚሆኑ አሉ ” – ድርጅቱ
” ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ” የመብት ተሟጋች የተሰኘው ድርጅት፣ ” የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ በዘፈቀደ እየታሰሩ ነው ” ሲል ለቲካቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡
ስለእስሩ በተጨባጭ ያላችሁ መረጃ ምንድን ነው ? ብለን የጠየቅናቸው የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብሪሂ ብርሃነ፣ ” በባለፉት ሁለት፣ ሦስት ሳምንታት ያለየፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ ያለበቂ ጥርጣሬ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ እየታሰሩ ስለሆነ ይህን መሠረት አድረገን ክትትል ስናደርግ ቆይተናል ” ብለዋል።
” ከክትትል ባለፈ ደግሞ ተጨባጭ ማስረጃ ካገኘን በኋላ እና ታስረው የወጡት፣ የታሳሪ ቤተሰቦችና ጓደኞችን ከጠየቅን በኋላ ሪፖርት አውጥተናል ” ብለው፣ ” ሰዎች ከሕግ ውጪ ሲታሰሩ ብቻ ሳይሆን ያለበቂ ጥርጣሬ ታስረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ሲቀር ይሄ የዘፈቀደ እስር ነው ” ሲሉ ወንጅለዋል።
” ሰዎች ሊታሰሩ ይችላሉ። ግን ሕግ ቢተላለፉ እንኳ ወደ ፍርድ ቤት ነው እንጂ የሚቀርቡት ከ48 ሰዓታት በላይ ፓሊስ አስሮ ማቆየት አይችልም በወንጀል እንኳ የተጠረጠረውን። እነዚህ ግን የወንጀል ጥርጣሬም የላቸውም፣ ለምን እንደታሰሩም አይነገራቸውም ” ነው ያሉት።
እስራቱ ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ” እስሮች በየጊዜው ይፈጸማሉ አሁን በትግራይ ተወላጆች ትኩረቱን አደረገ እንጂ፤ ከዚህ በፊትም ማንነት ተኮር እስሮች አሉ። ምክንያቱን አሳሪዎቹ ናቸው የሚያውቁት ” ብለዋል።
” አንድ ሰው ከታሰረ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት እንጂ አንድ ቦታ አጎሮ ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት ማቆየት ሕገ ወጥ ድርጊት ነው በወንጀልም ያስጠይቃል። በቁጥጥር ሥር የሚያውሏቸው ሰዎች ‘እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው’ ነው የሚሉት ” ብለዋል።
” ሰዎች በሕገ መግስቱ አንቀጽ 25 መሠረት በእኩልነት ነው መስተናገድ ያለባቸው ” ያሉት ም/ዳይክተሩ፣ ” የታሰሩ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ከፍለው የወጡበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ የሙስና ተግባራትም አለ ለማለት ያስችላል ” ብለዋል።
በተጨባጭ ድርጅቱ ባለው መረጃ መሠረት ምን ያክል ሰዎች ታስረዋል ? የት ክፍለ ከተማስ ነው የታሰሩት ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረላቸው ጥያቄ፣ ” በተጨባጭ በእያንዳንዱ ከተማ ምን ያህል ሰው እንደታሰረ መቁጠር ያስፈልጋል። ግን ለምሳሌ የካ ክፍለ ከተማ ወደ 100 ሰዎች መታሰራቸውን በማስረጃዎች አረጋግጠናል፤ ወደ ቦሌ ወደ 200 የሚሆኑ አሉ ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
” በመቶዎች ወይም እስከ 1000 ሊሆን ይችላል ብለን እንገምታለን አጠቃላይ በቁጥጥር ሥር ውለው የተፈቱትና አሁንም በእስር ላይ ያሉት” ያሉት አቶ መብሪሂ፣ “ሰዎቹ የታሰሩት ቦሌ፣ ሲኤምሲ፣ ሾላ፣ ልደታ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ሰዎች ወንጀል ከሰሩ በሕግ አግባብ አይጠየቁ አንልም ነገር ግን በጅምላ እየተወሰዱ፣ አንዳንዴም ገንዘብ እየጠየቁ እየሆነ ያለ ተግባር ስለሆነ በማንም ተወላጅ ላይ ሊደረግ አይገባም። መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ይስጥበት ” ሲሉም አሳስበዋል።