በአርሲ ሮቤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ
========
በሮቤ ወረዳ የገደብሳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ።
በምሥራቅ አርሲ ሮቤ ወረዳ ቤተ ክህነት የገደብሳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ካህን ቀሲስ ተስፋዬ ረታ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 አካባቢ በታጣቂ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ተገልጿል።
ለማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ በደረሰን መረጃ ባለቤታቸው በተመሳሳይ ሁኔታ መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን አካባቢው ካህኑ የተወለዱበት እና ከዲቁና ጀምሮ በአሁኑ ወቅትም በቤተ ክርስቲያኑ በቅስና ማእረግ እያገለገሉ ነበር ተብሏል፡፡
የካህኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት በሮቤ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በወረዳው እየተባባሰ የሚገኘውን አፈና እና ግድያን በመፍራት እና በመስጋት በአካባቢው የሚኖሩ ምእመናን ከተማውን ለቀው እየተሰደዱ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቀሲስ ተስፋዬ ረታ የሰባት ልጆች አባት ሲሆኑ ልጆቻቸውም ምንም አይነት ሥራ መሥራት የማይችሉ እና ሕጻናት በመሆናቸው ለመጠለያ ይሆናቸው ዘንድ የወረዳው አስተዳደር 200 ካሬ ሜትር መስጠቱን የተናገሩት መረጃ ሰጪያችን የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጋራ ሆነው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ጣቢያችን ጉዳዩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የወረዳው የፀጥታ ኃይል ኀላፊን ለማግኘት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም መልስ ማግኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡