ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም በታጣቂዎች ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ግን በርካታ አባቶች ተገደሉ፤ ታግተው ተወሰዱ

“ የተገደሉት አባት ለ12 ዓመት በብትውና የኖሩ ነበሩ። ቀብራቸው ተፈጽሟል። ጥቃት በተከፈተበት ዋሻ አካባቢ የነበሩ ሰባት አባቶችን ወደ ገዳሙ አምጥተናል ” – ደብረ ከዋክብት ዝቋላ ገዳም

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ባለው ደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም “የሸኔ ታጣቃዎች” ባህታውያን አባቶች በሚኖሩባቸው ዋሻዎች ተኩስ መክፈታቸውን ገዳሙ ማሳወቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም፤ “ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ግን በርካታ አባቶች ተገደሉ፤ ታግተው ተወሰዱ ” የሚል መረጃ በማህበራዊ ሚዲያው በሰፊው የተዘዋወረ ሲሆን በርካቶችን አሳዝኗል አስቆጥቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በበኩሉ፣ በሰሞንኛው የታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉት ምን ያህል አባቶች ናቸው ? ታግተው የተወሰዱስ አሉ እንዴ ? “ ይገደሉ ይኖሩ ገና አልታወቀም ” የተባለላቸው አባቶች ጉዳይስ ከምን ደረሰ ? ሲል ዛሬ ገደሙን ጠይቋል።

” ‘ሁለት አባቶች ተገድለዋል’ የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር፤ ይህን ያሉን አባቶች አንዱን አባት ከዋሻው ሲገድላቸው ሲያዩ ተደብቀው ቆይተው ሸኔዎቹ ሲሄዱላቸው ተኩስ ወደ ከተከፈተበት ዋሻ ሲመለሱ አንዱን አባት ሞተው አገኟቸው፤ ወደ ሁለተኛው አባት ዋሻ ሲሄዱ ግን አጧቸውና በተከታታይ ጥይት ተተኩሶ ስለነበር እሳቸውንም ገድለዋቸዋል በሚል ‘ሁለት አባቶች ሞተዋል’ ብለው ነገሩን ” ሲል መልሷል።

” ነገር ግን ትላንት ዋሻው ድረስ ሂደን አይተን ስናረጋግጥ የሞቱት አንድ አባት ብቻ ናቸው። ሌላኛው ‘ተገደሉ ተብለው የነበሩት አባት ደግሞ ሸኔዎቹን ሲያዩ ከዋሻቸው ወጥተው ተሰውረው ስለነበር በፍለጋ አግኝተናቸዋል” ሲል ገዳሙ ገልጷል።

የጥቃት ቀጠና በነበሩት የገዳሙ ዋሻዎች የነበሩ ሌሎች ሰባት አባቶችን ወደ ዋናው ገዳም አምጥተው ቦታ እንደሰጧቸው፣ የሞቱት አባት ደግሞ አምና ከተገደሉት አራት አባቶች አጠገብ የቀብር ሥርዓታቸው እንደፈጸመ ገዳሙ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ሟቹ ባህታዊ አባ ኃይለሚካኤል በመጀመሪያ ገዳማቸው ማኀበረ ስላሴ፣ ዲሙ የሚባል በርሃ፣ ደብረ ሊባኖስ ገዳም እንዳገለገሉ፣ በኋላም በዝቋላ ገዳም ብዙ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው ወደ ዋሻ ሂደው 12 ዓመት በብትህውና እንደኖሩ፣ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ/ም በጥቃቱ ሰማዕትነት እንደተቀበሉ ተመላክቷል።

” የታገቱ አባቶች አሉ ” ለሚለው መረጃስ እውነተኛ ነው ? ለሚለው ጥያቄ፣ ” ታግተዋል ተብሎ የነበረው በአቅራቢያቸው የነበሩ አባቶች ከተኩስ በኋላ በዋሻቸው ሲያጧቸው ጊዜ የተናገሩት እንጂ የታገተ ሰው የለም ” ሲል ገዳሙ  ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥቷል።

ሆኖም ግን አሁንም በዋሻ ያሉ አባቶችን፣ ታጣቂዎቹ፣ ” ‘እዚህ ሸኔ መጥቷል ብላችሁ ብትናገሩ ሙሉ ለሙሉ እንጨርሳችኋለን’ በሚል ዝተውቸዋል” ብሎ፣ መንግስትና ህዝቡ ከለላ እንዲያደርግለት ዝቋላ ገዳም በአጽንኦት ጠይቋል።