ተገቢውን ቪዛ እና የአየር ትኬት ይዘው ለውጭ ጉዞ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እስከ 100 ሺህ ብር እየተጠየቁ መሆኑን ተጓዦች ተጠየቁ

– “ቪዛ እና ትኬት ይዘን ቦሌ አየር ማረፊያ ስንደርስ ገንዘብ እየተጠየቅን ነው”— ተጓዦች

– “ይህ ድርጊት እንዳለ መረጃው የለንም፣ ካለ ግን ህገወጥ እና ሙስና ነው። አጣርተን ለሚመለከተው አካል እንልካለን”— የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት

ከሰሞኑ በርካታ ግለሰቦች ተገቢውን ቪዛ እና የአየር ትኬት ይዘው ለውጭ ጉዞ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከ50 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር እየተጠየቁ እንደሆነ መረጃዎች ሲደርሱኝ ነበር። አንዳንዶቹ “ከሄዳችሁበት ላትመለሱ ትችላላችሁ” እንደሚባሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ “በሚስጥር ብር አምጡ” እንደተባሉ ይገልፃሉ።

በዚህ ዙርያ መረጃ ከኤርፖርቶች ድርጅት መረጃ ጠይቄ ነበር። የተሰጠኝ መልስ “ይህ ድርጊት እንዳለ መረጃው የለንም፣ ካለ ግን ህገወጥ እና ሙስና ነው። አጣርተን ለሚመለከተው አካል እንልካለን። ይህን የሚያደርግ ሰራተኛ ካለ ተጠያቂ ይደረጋል፣ ግን እንደዛ አይነት አሰራር የለም። ምናልባት ብር የሚሰጥ ሰው ካለ እሱም የድርጊቱ አካል ነው፣ ድርጊቱም ህገ-ወጥ ነው” የሚል ነው።

ዜጎች ግን “እንዴት ቪዛ ሰጪው ኤምባሲ የፈቀደውን ላትመለስ ትችላለህ ተብሎ ሰው ከጉዞ ይታገዳል?” ብለው ይጠይቃሉ። በዚህ ምክንያት ከትምህርት፣ ጉዞ እና ህክምና የተስተጓጎሉ ሰዎች እንዳሉ የደረሰኝ መረጃ ይጠቁማል።

በዚህ ዙርያ የሚመለከተው አካል አጣርቶ ለህዝብ መረጃ ይፋ እንደሚያረግ ተስፋ እናረጋለን። – ኤሊያስ መሰረት