አፋር ክልል የዕርዳታ ክፍፍሉ ለፓለቲካ ትርፍ እና ለፖለቲካ ምስለ ግንባታ ሲባል ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ወድቋል

ተቃዋሚው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለአፋር ክልል የጦርነት ተጎጅዎች ባግባቡ እየደረሰ አይደለም ሲል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ ከሷል።

የምግብ ዕርዳታ ለተረጅዎች ሳይከፋፈል መጋዘን ውስጥ ታሽጓል ያለው ፓርቲው፣ የዕርዳታ ክፍፍሉ ለፓለቲካ ትርፍ እና ለፖለቲካ ምስለ ግንባታ ሲባል ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ወድቋል በማለት ወቅሷል።

የሰሜኑ ጦርነት በአፋር ክልል ላይ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመት የክልሉ መንግሥት ከገለጸው በላይ እንደሆነ እና የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ሥራዎችን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ያለ ሌላ ገለልተኛ አካል እንዲያከናውናቸው ፓርቲው አክሎ ጠይቋል።

ከአፋር ህዝብ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
:::::::::::::::::::::::::::::;:::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::

May be an image of palm trees and text that says 'PEOPLE'S PARTY (APP) AFAR QAFAR QAFAR UMMATTAH PARTI (QUP) (QUP)'እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፈው አንድ አመት ገደማ በጦርነት ውስጥ መቆየቷ እና በተለይ ደግሞ የአፋር ክልል ህዝብ አሁንም በሰሜኑ የክልላችን ክፍል ባልቆመ ጦርነት ውስጥ እንዳለም የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን እና የአፋር ህዝብ ተገዶ በገባበት በዚህ ጦርነት በርካታ ጀግኖቹን ያጣ ቢሆንም ክብሩን አስጠብቆ በሉዓላዊ ክልሉ ውስጥ ታሪክ የማይዘነጋው ተጋድሎ አደረጓል፡፡

ይህ ጦርነት የስልጣን ሽኩቻ መነሻውን አድርጎ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም በሌላ መንገድ ደግሞ የአፋር ህዝብ በአልሸነፍም ባይነት እና ጀግንነት ታሪካዊ ገድል ፈጽሟል፡፡ ይህም በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

ለዚህ ክብር እና ታሪካዊ ዝና ያበቁን ለህዝባቸው እና ለሀገራቸው ሲሉ ውድ እና መተኪያ የማይገኝለትን ህይወታቸውን ለሰጡን ጀግኖች ሰማዕታቶቻችን ዘላዐለማዊ ክብር ይገባቸዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ የአፋር ህዝብ የተተናኮሉትን የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቹን ድል ነስቶ አሳፍሮ መመለስ ታሪካዊ ልማዱ ነው።

አሁንም ወራሪው የትግራይ ኃይል እጅግ ዘመናዊ ትጥቅ ታጥቆ እና ከፍተኛ ስልጠና ወስዶ ያለ የሌለውን ሀይሉን ወደ አፋር ቢያዘምትም የመጣውን ወራሪ ሃይል በተለመደው መንገድ ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መልኩ መክቶ በራሱ የግዛት ክልል ውስጥ ለዘመናት ያቆየውን ክብሩን አስጠብቋል፡፡

የአፋር ህዝብ ሁልጊዜ ቅድምያ ለሌሎች የሚሰጥ፤ በስራ እንጂ በፕሮፖጋንዳ ሸብረክ የማይል፤የሉዓላዊነትን ትርጉም በጥልቀት የሚረዳ እና ለሁሉም ሰላማዊ ዜጎች ልዩ ክብር ያለው ህዝብ ነው፡፡ ጀግናው የአፋር ህዝብ ሰላም ያላትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለዚህም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ሕዝብ ነው። ይሁን እንጂ ከተንኮል፣ ከሽረባ እና ከእብሪት በስተቀር ለሰላም ቦታ የማይሰጡ፤ በብዛት እንጂ በጥራት ነገሮችን መከወን ለማይችሉ፤ሁልጊዜ በቁጥር እና በቁስ ነገሮችን ለሚገመግሙ የታሪክ ዝንጉ የሆኑ ሃይሎችን አስፈላጊውን ማስታወሻ አስይዞ መሸኘት የየዘመኑ የቤት ስራው ሆኗል፡፡

ይህ ጦርነት እኔ ካልገዘሁ ሀገር መፍረስ አለባት ብለው በተነሱ ኃይሎች፤ግጭቶችን በውይይት መፍታትን እና ጦርነቱ ሲጀመር ሳይሆን ሲያልቅ የሚኖረውን አደጋ ባለማመዛዘን በውስጣዊ ክፉ ስሜታቸው ብቻ በመመራት የተጀመረ እርባናቢስ ጦርነት ሲሆን የአፋር ህዝብ ቅድሚያ ለሠላም ቢሰጥም በጊዜ ሂደት ወደ አፋር ግዛቶች ተስፋፍቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የአፋር ህዝብ ፓርቲም ከጥቅም 24 በፊትም ሳይቀር የፖለቲካ መካረሩን አስቀድሞ ገምግሞ፤ ነገሮችን ወደ ብሄራዊ ምክክር በመውሰድ በሂደት ወደ ብሔራዊ መግባባት መሄድ አለባቸው ፤ ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት አለባቸው በማለት ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎም ለፖለቲካ ማህበረሰቡ ግልፅ የሆነ አቋሙን ሲያንፀባርቅ እንደቆየም ይታወሳል፡፡

እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ነገሮች ህዝብና ሀገር በሚፈልጉት መንገድ ሳይሆን በስልጣን የሚገዳደሩ እና አቅማቸውን መለካካት የሚፈልጉ ሰዎች እንዳቀዱት ሆነው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሀገራዊ ሰላሙ ለሁላችንም እንደሚያዋጣን ቢገነዘብም ስለ ብሄራዊ መግባበት እና ምክክር አቋሙን ሳይለውጥ በህዝባችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ደግሞ በግልፅ ለመከላከል እና ከህዝባችን ጎን መሰለፉን መርጠናል፡፡ ለአፋር ህዝብ ጥቅም እንደተቋቋመ ፓርቲ ይህ የሚያኮራን እና ለወደፊቱም ከህዝባችን ጎን መሰለፋችንን የምንቀጥል ሲሆን አሁንም የትግራይ ወራሪዎች በክልላችን በሰሜናዊ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ላይ የሚያደርጉትን ትንኮሳ እና ወረራ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እናስጠነቅቃለን።

የአፋር ህዝብም ሰፋ ያለ የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች ቀጠናዊ የፖለቲካ የበላይነታቸውን ለማሳየት እና አስፈላጊውን የአፍሪቃ ቀንድ ቀጠናን ለመቆጣጠር አፋርን ማዳከም እንደ ቁልፍ እስትራቴጂ ስለሚዋስዱ ያለምንም መዘናጋት እና ማንቀላፋት በተለመደው ንቃት እና ብርታት ሀገሩን መጠበቁን እንዲቀጥልበት እናስገነዝባለን፡፡

የአፋር ህዝብ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትን ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮችን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ከዚህ በታች የተመለከተውን መግለጫ አውጥቷል።

1. በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ

ህዝባችን ተገዶ በገባበት በዚህ ጦርነት እጅግ በርካታ ዜጎች ከቄያቸው ተፈናቅሏል፤ ሀብት ንብረታቸው ወድሟል፤ ቤተሰባቸውም ፈርሷል። ሕጻናት ወላጅ አልባ ሆነው ምድር የመሬት ሲኦል ሆኖባቸዋል። ከዚህ ጋርም በተያያዘ ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ እና ቁሳዊ መልሶ ግንባታ እንደሚያስፈልግ ፓርቲያችን አስቀምጧል፡፡ከዚህም አንፃር ድጋፎች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ክልሉ እየመጡ እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን። የክልሉም መንግስትም እያደረገ ያለውን ጥረት የበለጠ ማጠናከር አለበት ብለን እናምናለን፡፡ እንደፓርቲም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን እንገኛል፡፡

ሆኖም ግን የሚደረጉ ድጋፎች ከፖለቲካዊ የገፅታ ግንባታ ባለፈ ለትክክለኛው ተጎጂዎች እየደረሱ እንዳልሆኑ በርካታ ቅሬታዎች እየደረሱን ይገኛሉ።በተዘዋወርንባቸው የመጠለያ ካምፖች እንደታዘብነው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አስፈላጊውን ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነና አብዛኛዎቹ ድጋፎች በተለይም ምግብ ነክ የሆኑ ቁሳቁሶች በመጋዘን ተከማችተው ለህዝቡ በሰዓቱ እየደረሱ እንዳልሆነም ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ተግባር በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል ስንል በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ያለው የነፍስ አድን ስራ ሆኖ ሳለ እና ገና የመልሶ ማቋቋም ስራ ባልተጀመረበት በዚህ ወቅት፤ እንዲህ ዓይነት ብልሹ አሰራሮች ሊታረሙም ይገባለ፡፡ በመሰረቱ ይህን ስርዓት የሚመራ አሳታፊ የሆነ ተቋም ተዋቅሮ መሰራት ሲገባው መንግስት ብቻውን ጉዳዩን በሞኖፖል ይዞ ሌሎችን በማግለሉ የቴክኒክ እና የታክቲክ ችግሮች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ በመሰረቱ የድህረ ጦርነት መልሶ ግንባታ እና ማገገሚያ ፕሮጀክቶች ራሱን በቻለ ተቋም መመራት ይገባዋል እንጂ ባለው የመንግስት ተቋም ወይንም በኮሚቴ የሚሰራ ስራ አለመሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን።

የአፋር ክልላዊ መንግስት በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳትና በዚህ ሂደትም ምን ያህል ድጋፍ እንደተገኘና ለምን ተግባር እንደዋለ ለአፋር ህዝብ መግለፅ አለበት፡፡እንደ አፋር ህዝብ ፓርቲ በአፋር ክልል የደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግስት ከገለፀው መጠን እጅግ በብዙ እጥፍ ስለሚበልጥ መረጃዎቹ እንደገና በጥንቃቄና በጥልቀት በባለሙያ ተሰርተው ሊገለፁ ይገባል።

በአንዳንድ አከባቢዎች ሰፊው የአፋር ህዝብ ለሉዓላዊነቱ ስል የከፈለውን መስዋዕትነት ወደ ጎን በመተው ሕዝባዊ ድሉን የተወሰኑ ግለሰቦች ወይንም ቡድን አድርጎ የመውሰድ የድል ሽምያ በአስቸኳይ መታረም አለበት ብለን እናምናለን። በዚህ አጋጣሚም በጦርነቱ ሕይዎታቸውን ላጡ አባላቶቻችን እና ለመላው የአፋር ጀግኖቻችን ያለንን አክብሮት እንገልጻለን። እንደተለመደው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ለተሰዉት ጀግኖቻችን ቤተሰቦችንም ሆነ በአጠቃላይ የመልሶ ማቋቋም ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

2 ጀግናውን የአፋር ህዝባዊ ሰራዊትን በተመለከተ

ለጀግኖቹ የአፋር ህዝባዊ ሃይል እና መላውን የፀጥታ አካላትን በተመለከተ ሰፊ የሆነ የስልጠና፤የትጥቅና የስንቅ ብሎም ከድህረ-ጦርነቱ በኋላ ተገቢውን ካሳ እና እውቅና ከፌዴራልም ሆነ ከክልላችን መንግስት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ በሰላም ስለሠላም መነጋገር ባልተቻለ ነበርና፡፡

3. የዞን እና የወረዳ መዋቅሮችን በተመለከተ

ለአስተዳደራዊ ሂደቶች እንዲያመች የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በአዲስ መልክ መልሶ ያዋቀራቸውን ወረዳዎች እንዲሁም ዞኖች በሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት አፀድቆ ወደ ዓመታዊ የበጀት ድልድል ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ መንግስታዊ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም የወረዳ ለወረዳ እንዲሁም የዞን ለዞን ግንኙነቶችን ለማሳለጥ እንዲረዱ አስፈላጊውን ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

4. በአፋር ክልል ውስጥ ያሉ የስጋት ቀጠናዎችን በተመለከተ

ከያንጉዲ ራሳ እስከ ከሮማ-ገዋኔ ባለው መንገድ ላይ ሕዝባችን በገዛ መሬቱ ላይ በሰላም አልፎ ከአንደ አከባቢ ደወደ ሌላ አከባቢ እንዳይሄድ እየተደረገበት ያለው ሁኔታ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ሲሆን ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ በአጃቢ ካልሆነ መንቀሳቀስ እንደማይቻል እየታወቀ በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግስት መፍትሄ ባለመበጀቱ ሚክንያት ህዝባችን ለአጃቢ 10ሺ ብር እየከፈለ ለመከራ ተዳርጓል ይህ ችግር በአስቸኳይ መቀረፍ አለበት፡፡

5. ኪልበቲ ረሱን በተመለከተ

በኪልበቲ ራሱ ሕዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ማኀበራዊ ችግሮች ከመፈታት ይልቅ በውስብስብነቱ ቀጥሏል። በመሆኑም የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሕዝባችንን የደህንነት፤ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት የመኖር ህሉናውን እንዲያረጋግጥ እንጠይቃለን።

6. ሀገራዊ ምክከሩን እና ብሔራዊ መግባባቱን በተመለከተ

ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ሁሉም የሀገራች ኢትዮጵያ ህዝቦች አጀንዳዬ ብለው የሚያስቡትን በነፃነት የሚገልፁበት እና ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ግልፅ የሆኑ ሀገራዊ ስህተቶች የሚታረሙበት እንዲሆን የአፋር ህዝብ የፀና እምነት አለው፡፡

በመሆኑም ከሂደቱ እስከ ፍፃሜው ግልፅ፤ ገለልተኛ፤አካታችና ተዓማኒ እንዲሆን መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ባለመግባት እና ሌሎችም ጣልቃ እንዳይገቡ በመከላከል የተሳለጠ፤የተሳካ እና የሀገራችንን ችግሮች በጥልቀት ፤ በዕውቀት እንዲሁም በብልሃት እና በሰጥቶ መቀበል መንፈስ በዘላቂነት የምንፈታበት እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት መደረግ አለበት፡፡

ለፖለቲካዊ እንዲሁም የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ጫና ለመቋቋም የሚደረግ የማስመሰል ስራ እንዳይሆን ጥንቃቄ መወሰድ አለበት፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአፋር ህዝብ አጀንዳ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋራ የምንጋራቸው ጉዳዮች ቢኖሩም እኛን በቀጥታ እና ለብቻ የሚመለከቱን እና በሀገር አቀፉ መድረክ መቅረብ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም የአፋር የፖለቲካ ሃይሎች እና የክልሉ መንግስት በአስቸኳይ ተገናኝተን የህዝባችንን አንኳር ጉዳዮች ለይተን ቀድመን ማስቀመጥ እድንችል ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል በመሆኑም በተጫለን አቅም ይህን መድረክ እድናመቻች በአፅንዖት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥር 4/2014
ሰመራ ፤አፋር፤ ኢትዮጵያ