የሕወሓት የደሕንነት ሹም በነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ክስ መዝገብ ላይ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ በ26 ተከሳሾች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው እና ማንነታቸው የማይገለፅ 29 ምስክሮችን ማሰማት ጀመረ — በተያያዘ የፍርድ ቤት ችሎት ዜና አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባ አንድ ላይ እንዲገናኙ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አፈፃፀሙን ለመመልከት በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
(ኤፍ.ቢ.ሲ) በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ በተከሰሱ በ26 የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ላይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የዐቃቤ ህግ ምስክር ማሰማት ጀመረ።
በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ በ26 የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች በተከሰሱበት በአዋጅ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ሰዎችን በመያዝና በማሰር ስልጣንን ያለ አግባብ መገልግል ወንጀል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከመጋረጃ ጀርባ ማንነታቸው የማይገለፅ ምስክሮችን ዛሬ ማሰማት ጀምሯል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት አጠቃላይ 22 ተከሳሾች ሲሆኑ፥ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አፅበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይ እና ሺሻይ ልኡል በሌሉበት ነው ጉዳያቸው የታየው።
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በምስክር ጥበቃ አዋጅ 699/ 2003 መሰረት ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው እና ማንነታቸው የማይገለፅ 29 ምስክሮችን ያዘጋጀ ሲሆን፥ በዛሬው እለት ሶስቱን አቅርቧል።
በዚህም አንድ ምስክር መሰማት ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሚታየው የቪዲዮ ማስረጃ ጥራት ጉድለት ምክንያት ቀሪ ምስክሮቸን ከመጋረጃ ጀርባ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
————————————————————–
በተያያዘ የፍርድ ቤት ችሎት ዜና አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባ አንድ ላይ እንዲገናኙ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አፈፃፀሙን ለመመልከት በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይም ቀርበው ትእዛዙ መፈፀሙን አብራርቷል።
እነ አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባም ትእዛዙ መፈፀሙን ገልፀዋል።
የአቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና የአቶ ሸምሰዲን ጠሃ ጠበቃ ለችሎቱ ደንበኞቹ 30 ደቂቃ ብቻ አየር እያገኙ መሆኑን በመግለፅ፤ ከ30 ደቂቃ በላይ የፀሃይ ብርሃን እና አየር እንዲያገኙ ትእዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም በቂ አየር እና የፀሃይ ብርሃን እንዲያገኙ ትእዛዝ ሰጥቷል።