" /> የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው 20 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው 20 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው 20 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ
በአሁኑ ሰዓት (20) ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምላሽ አሰጣጥን (የኮቪድ-19) አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን ያከናወኗቸው ተግባራት፣
• ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተሩ ያሳለፉቸውን ውሳኔዎች ተከትሎ በየደረጃው ያለውን ተፈጻሚነት በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመው ከሚቴ በበላይነት በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
• ከቀን 14፣2012 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ሀገር የሚመጣ መንገደኛ በሆቴል ውስጥ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆይ በተወሰነው መሰረት በትላንተናው እለት ወደ ሀገራችን የገቡ ከ473 በላይ መንገደኞች በተመረጡ ሆቴሎች ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መሰረት
ኢንስቲትዩታችን የጤና ክትትል ባሉበት ሆቴል ውስጥ እያከናወነ ይገኛል፣
• በሀገራችን አስራ ሁለት (12) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው መሆኑን ቀደም ብሎ በተሰጡ መግለጫዎች ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከ12 ታማሚዎች ውስጥ ሁለቱ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆኑ ሌሎች ታማሚዎች በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ታማሚዎች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፣
• ወደ ሀገር ውስጥ መግቢያ ጣቢያዎች እየተደረገ የሚገኘው ምርመራ የተጠናከረ ሲሆን ስድስት መቶ ስልሳ ስምንት ሺ አራት መቶ ሰባ ስድስት ሰዎች (668,476) በሙቀት መለያ (ኢቦላና ኮቪድ-19 በማጣመር) አልፈዋል፡፡
• በሙቀት መለያ ካለፉት ውስጥ አስራ ሁለት ሺ ሁለት መቶ አርባ አምስት (12,245) ያህሉ በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት የመጡ ናቸው፡፡
• በአሁኑ ሰዓት አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ሀያ ሶስት (1,923) የሚሆኑት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ሰዎች ለ14 ቀን የጤና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ሲሆን አንድ ሺ ሰባት መቶ ሰባሁለት (1,772) የሚሆኑት ለ14 ቀናት ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው የኮሮና በሽታ ምልክት ያልታየባቸው በመሆኑ ክትትላቸው ተቋርጧል፡፡
• እስከ አሁኑ ሰዓት አራት መቶ አርባ ስድስት (446) ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ መቆያ ማእከል እንዲቆዩ ተደርጎ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን አራት መቶ ሰላሳ አንድ ሰዎች (431ዎቹ) ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡
• በአሁኑ ሰዓት የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሀያ ሰዎች(20) ናቸው፡፡
• ከዚህ በፊት ከተሰራጩት የህክምና መስጫ ግብአቶች በተጨማሪ ከሁለት ሚሊየን (2, 000,000) በላይ የፊት ማስክ ለሁሉም ክልሎች ተሰራጭቷል፤
• የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰራጩት በተጨማሪ ሀምሳ ሺ (50.000) ፖስተሮች ፤ ሁለት መቶ ሺ (200,000) ብሮሸሮች፤ ለሁሉም ክልሎች እየተሰራጩ ይገኛሉ፡፡
• የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ የፊት ማስክ እና የእጅ ጓንት ለ112 የሚሆኑ የፌደራል መስሪያቤቶች እየተሰራጨ ይገኛል፤
• ከስደተኞችና ስደት ተመላሾች ጉዳዮች ጋር በመተባበር የኮሮና በሽታ ስርጭትን በስደተኞች ካምፕ ውስጥ የመከላከል ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከተለያዩ ተቋማት የተገኙ ድጋፎች
• ከጃክ ማ ኢኒሼቲቭ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለአፍሪካ ሀገራት የሚሰራጩ 5.4 ሚሊየን የፊት ማስክ (Face masks,) 1.08 ሚሊየን የላብራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች( test kits) 40,000፣የፊት መሸፈኛ መነፅርና 60,000 የጤና ባለሙያዎች የመከላከያ ልብሶች( protective face shields) ድጋፍ ተደርጓል፡፡
• ሁዋጃን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት የመከላከያ ልብሶች ድጋፍ አድርገዋል።
• የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ለክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚውሉ ክሎሪንና የአደጋ ጊዜ የህክምና መርጃ መሳሪያዎች (emergency drug kit ) ድጋፍ አድርጓል፣
• ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ተግባር ለመደገፍ ፋብሪካው 400 ሊትር የእጅ ማጽጃ አልኮል ለኢንስቲትዩቱ ድጋፍ አድርጓል፣
• የግብርና ሚኒስቴርም ለጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ የፊት መስክ፣ የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙት የመከላከያ አልባሳት፣ የእጅ ጓንትና አይን መነፅር ( goggles)ድጋፍ አድርጓል፡፡
ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች
• የክቡር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የንፁህ እጅ ጥሪን ተከትሎ በሀገራችን ከክቡር ጠ/ሚኒስትር ጀምሮ ሌሎች አመራሮችና መላው ህብረተሰብ በሚባልበት ደረጃ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ማህበረሰቡ ይህንን በሚተገበርበት ወቅት አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ ሁኔታ ላይ ክፍተቶች የተስተዋሉ በመሆኑ ህብረተሰቡ በአንድ ሜትር ርቀት እንዲጠብቅ በጥብቅ እናሳስባለን፣
• በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች በዛ ያሉ ሰዎች የተገኙባቸው ስብሰባዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑ ስብሰባዎቹ በሚካሄድባቸው ጊዜ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲተገበሩ እንመክራለን፣
• ህብረተሰቡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞችን ለ14 ቀናት ራሳቸውን ለይተው በሚቆዩበት ወቅት በስልክ ወይም የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሞራል ድጋፍ እንዲያደርግና እንዲያበረታታቸው ፤ ታማሚዎችንና የታማሚ ቤተሰቦችንም አገግመው ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት አልያም በለይቶ ማከሚያ ውስጥ ያሉትንም በተመሳሳይ መልክ ድጋፍ እንዲያደርግና አካላዊ ርቀቱን በመጠበቅ መንፈሳዊ አንድነቱን እንዲያጠናክር እንጠይቃለን፣
• በተጨማሪም የኮሮና በሽታን (ኮቪድ-19) ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደረግ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም 952 ፤ በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡

የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV