" /> ኤልያስ መልካ ከፅዮን እስከ በገና — ከተወልደ በየነ (ተቦርነ) | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ኤልያስ መልካ ከፅዮን እስከ በገና — ከተወልደ በየነ (ተቦርነ)

ኤልያስ መልካ ከፅዮን እስከ በገና
ከተወልደ በየነ (ተቦርነ)
____________________________
አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አብነት አዲስ ከተማ በ1970 አ,ም የተወለደው ዘርፈ ብዙው ባለተሰጥኦ ህይወቱን የሰጠላትን ሙዚቃን ከመቀላቀሉ በፊት በልጅነቱ ትንሹ ማራዶና እስከመባል የተዋጣለት እግርኳስ ተጫዋች ነበር። የኘሮቴስታንት እምነት ገና ባልተስፋፋበት እና ወታደራዊው መንግሥት በእምነቱ ላይ ጫና በሚያሳድርበት ዘመን የእምነቱ ተከታዮች በየመኖሪያ ቤቶቻቸው እየዞሩ በጊታር ፣በኦርጋን ፣በድራም ወዘተ ነበር ዝማሬዎቻቸዉን የሚከውኑት
ታዲያ በተደጋጋሚ ስርዓቱ ከሚከወንባቸው ቤቶች ባንዱ ውስጥ ያለው ታዳጊ ከጊታር የተለዬ ፍቅር ያዘው። አልፎ አልፎም መነካካት ጀመረ። በኃላም ክህሎቱ እየጨመረ መጣ። ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል ሲዘዋወር ክረምቱን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገባ። በዛም ከብዙሰዎች ጋር የመገናኘት እድል ገጠመው። በኋላም የሙሉጊዜ ተማሪ በመሆን ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ።

ከተሳተፈባቸው የሙዚቃ ቡድኖች(ባንዶች)

1_ፅዮን መንፈሳዊ የሙዚቃ ቡድን
2_መዲና የሙዚቃ ባንድ
3_3M የሙዚቃ ባንድ
4_ዜማ ላስታስ
5_አፍሮ ሳውንድ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ።

በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ የዘመን ርክክብ ሲነሳ ወርቃማው የሙዚቃ ዘመን ሮሀ ባንድ በአሞራው የሙዚቃ ባንድ አሞራው የሙዚቃ ቡድን ወደ አቀናባሪ መሀመድ አማን ከመሀመድ አማን ወደ ሙሉጌታ አባተ ከሙሉጌታ አባተ ወደ ኤልያስ መልካ ተሸጋገረ። በነዚህ የዘመን ቅብብሎሽ የነበረውን የተለመደ አቅጣጫ ቀይሮ በአዲስ የሙዚቃ አብዮት ተቆጣጠረው። የመጀመሪያውን የቅንብር አቅምና ችሎታውን ያስለካው በትዝታው ንጉሥ ማሀሙድ አህመድ “ሁሉም ይስማው” በተሰኘው የሙዚቃ አልበም ነበር። በመቀጠል የኤሊያስ የሙዚቃ አብዮተኛነትን ያወጀው የቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) ሁለተኛ የሙዚቃ አልበም ነበር። በዚህ የሙዚቃ አልበም ውስጥ የሙዚቀኛ ዳግማዊ አሊ አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው ።ኤሊያስ ከአቦጊዳ የሙዚቃ አልበም በኋላ ንግሥናውን አረጋግጦ ሙዚቃን ፍቅርና አምሮቱን መወጫው አደረጋት። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ በመቆጣጠር ተሰምተው የሚደጋገሙ የሙዚቃ አልበሞችን አበረከተ።

በኤልያስ መልካ ሙሉ ለሙሉ ከተቀናበሩ የሙዚቃ አልበሞች መሀከል
1_ተሾመ ወልዴ (አቻዬ መልሴ)
2_አረጋኸኝ ወራሽ (በቃበቃ)
3_ግርማ ገመቹ (ትመችኛለሽ)
4_ትዕግስት በቀለ (ሳቂታው)
5_ጎሳዬ እና አሌክስ (ኢቫንጋዲ)
6_አብነት አጎናፍር (ድብቅ ውበት)
7_ማዲንጎ አፈወርቅ (አይደረግም)
8 _ኃይልዬ ታደስ (ሁሌ ሁሌ)
9_ፍቅር አዲስ ነቅአ ጥበብ (ልኡል አስወደደኝ)
10 ይርዳው ጤናው (ጀንበር)
11_ገረመው አሰፋ (ንፁህ ነሽ)
12_ደረጄ ዱባለ (አይኔን አላሽም)
13_እንዳለ አድምቄ (ኦሮማይ)
14 _ሚካኤል በላይነህ (አንተ ጎዳና)
15 ዘመነ መለሰ (አልወለድም)
16_ሙሉ(ሞኒካ)ሲሳይ (ሸክሽክ ዝም ብለህ)
17 _ኃይሌ ሩት (ችጌ)
18_አስቴር ግርማ(እሺ ግዴለም)
19_ምናሉሽ ረታ
20_ኤሊያስ የማነህ (ኪዊ) በቃኝ በቃኝ

በጣም ጥቂቶቹ ሲሆኑ ከሌሎች አቀናባሪዎች ጋር በጋራ ከተሳተፈባቸው ቅንብሮቹ መካከል

1_የቴዎድሮስ ካሳሁን (አላምን አለና ፣ሸመንደፈር ፣ዳህላክ
፣ላንባዲና
2_የጎሳዬ ተስፋዬ (ታምሪያለሽ ፣ቶክሲዶ ፣ልጆቼን ብለው ጠየቁኝ
3_ኩኩ ሰብስቤ (ከጉንጮቼ ወለል ፣አንተ የልቤ ወራሽ ፣የኔ የብቻው ነው
4_ላፎንቴኖች (ባቡሬ ፣ከፍጥረት የግልሽ ፣ምንጃር)
ለመረጃ ያክል ተጠቃሽ ናቸው ።

ዘርፈ ብዙው ባለ ተሰጥኦው ኤልያስ መልካ ከውጤታማ የሙዚቃ ቅንብሮች ጎንለጎን ባለ ተሰጥኦዎች በሙያ ገርቶና አርቆ የራሱን ጀግኖች ያወጣ ምርጥ ባለሙያነው። ከነዚህም መካከል
1_ዘሪቱ ከበደ
2_ኢዮብ መኮነን
3_ሚካያ በሀይሉ የውጤታማነቱ ማሳያ ናቸው ።

ኤሊያስ ለሀገር በተዜሙና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በተሰሩ የህብረት ዜማዎች ላይም ጉልህ ስፍራ ነበረው። ከነዚህም መካከል
በፀረኤድስ ዘመቻ ከተዜሙ

1_ማለባበስ ይቅር
2_መላመላ
3_ኑር ባታምንም

ከትራፊክ አደጋ ደህንነት ጋር በተያያዘ
_አሽከርክር እረጋ ብለህ
ከአፍሪካ ህብረት ጋር በተያያዘ
_ አዲስ አስተሳሰብ የኤሊያስ ድንቅ ተሰጥኦው ያረፈባቸው የህብረት መዝሙሮች ናቸው ።

ኤልያስ በግጥም ሥራዎቹ ፍልስፍናን ፣ተስፋን ፣ቅንነትን ትኩረት ያደረጉ ሀሳቦችን ያንፀባርቃል

በኢዮብ ሥራ ውስጥ
መልክን የሻረው
አንችጋር ምን ተሻለው
ከሩቅ ሳትስቢ
አየሁ ልቤ ስትገቢ እያለ ሰው ከውበት በላይ በምን መሻል እንዳለበት ያትታል።
የቋንቋ ፈላስፋ በሚለው ሥራውስጥ ደግሞ
ሀምሳ ሎሚ ከብዶኝ ይሸከም ጉልበቴ
አታግዙኝ ይቅር ጌጤነው ቅርጫቴ ይላል
ይህ የኢዮብ ዜማ ኤልያስን ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መንገድ ይጠቁማል ብዬ አስባለሁ
ኤልያስ ከአመታት በፊት ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ ለሚያቋቁመው የስኳር ህመምተኞች ማህበር መርጃ የሚውል “ስኳርን ታዘብኩት” የሚል ዜማ በአቀናባሪነት ሰርቶ ነበር።ይህ በሽታ ዛሬ ኤልያስን እንድናጣው ምክንያት ሆነ።

ባለድንቅ ተሰጥኦው ኤልያስ መልካ አይረሴ የሆኑትን የጥበብ ሥራዎቹን የከወነባት በገና እስቲዲዮ ዋናዋ ናት። ኤልያስ 19 ዓመት በቆየበት የሙዚቃ ህይወቱ 40 የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቶ በተወለደ በ42 ዓመቱ አርብ መስከረም 23 2012 ከሌሊቱ 9ስዓት ይችን ዓለም ተሰናብቷል። የቀብር ስነስርዓቱ ሰኞ መስከረም 26,2012 አ ም ጴጥሮስ ወ ጳዉሎስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይፈፀማል።

ኤልያስን ለ15 ዓመት በሥራም በወዳጅነትም አውቀዋለሁ። ኤልያስ “እሱ እንዲህ አደረገ” እንዲባልለት የማይፈልግ ደግነት የህይወቱ መመርያ የነበረ ምርጥ ሰው ቢሆንም ግባተመሬቱ ከመፈፀሙ በፊት ስለውለታው ጥቂት ልል ወደድሁ። ኤልዬ በመከራዬ ቀን ቀኝእጅ ሆኖ ችግሬን መክቷል! በህይወቴ ውስጥ ደግነትን ካዋጡ ጥቂት መልካም ሰዎች አንዱ ነበር። ስለ ኤልያስ ነበር እያሉ ማውራት እንዴት ያማል? ፈጣሪ በደጋጎቹ ጉን ያኑርህ!
ኤልዬ ደህና ሁን! ።

Image may contain: 1 person, smiling, flower

የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV