ላመነችበት የዋተተች ሕይወት – ታዲዮስ ታንቱ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ዋለልኝ አየለ፣ አዲስ ዘመን

ጋዜጠኝነትን እንደነፍሳቸው ይወዱታል። ከ30ዓመታት በላይ ኖረውበታል። በመምህርነት አገልግለዋል። በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ረጅም ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ በታጠቅ፣ ኢትዮጲስ፣ ፍትሕ… ጋዜጦች ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ በሚጽፏቸውና በሚያደርጉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በርካታ ውጣ ውረድ አጋጥሟቸዋል፡፡ በእስር ቤት ስቃይና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ የዛሬ የ ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ ይባላሉ።

በ1944ዓ.ም በቀድሞው ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በወላይታ አውራጃ በዳሞት ወይደ ወረዳ ግራራ ሚካኤል በሚባል አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ሻሸመኔ አጼ ናኦድ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከዚያም ወደ ናዝሬት በመሄድ በአጼ ገላውዲዎስ መርሐ ሙያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ተመርቀዋል፡፡ ከዚያም በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ አማርኛ ቋንቋና በታሪክ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከእርሳቸው ጋር የነበረንን ቆይታ እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- ከመምህርነት ሙያ ወጥተው በምን ሙያ ላይ ተሰማሩ?
ታዲዮስ፡- ከመምህርነት በኋላ በጦር ኃይሎች ዋና ፖለቲካ አስተዳደር በጋዜጠኝነት ተቀጥሬ በታጠቅ ጋዜጣ ላይ መሥራት ጀመርኩ፡፡ የታጠቅ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ጸሐፊም እኔ ነበርኩ፡፡ ከዚያ በኋላም በልዩ ልዩ ጋዜጦች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ እምቢ በይ ሀገሬ፣ አስኳል፣ ሜዲካል፣ ጦቢያ፣ ፍትሕ፣ አዲስ ታይምስ፣ ልዕልና፣ ፋክት፣ ኢትዮ ምህዳር፣ ነገረ ኢትዮጵያ እና የቀለም ቀንድ ላይ ሰርቻለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ሁሉ ጋዜጦች ላይ ሲሰሩ በአምደኝነት ብቻ ነው ወይስ ባለቤት የሆኑባቸው አሉ?
ታዲዮስ፡- አንድም ጋዜጣ ላይ ባለቤት ሆኜ አላውቅም፡፡ አቅሜም ለዚህ የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ ግን በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ በቋሚ ዓምደኝነት የሰራሁ እኔ ነኝ፤ የምሰራውም የራሴን ፎቶግራፍ በመለጠፍ ነው፡፡ መንግሥትን የሚተች ጽሑፍ በራስ ፎቶና በራስ ስም ቋሚ ዓምደኛ መሆን የተለመደ አልነበረም፡፡ እኔ በምጽፍበት ወቅት ብዙዎች የሚጠቀሙት የብዕር ስም ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ይህን የለመድኩት ከውጭ ጋዜጦች አሰራር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ሕይወትዎ እንመለስና ለ15 ዓመታት ያህል ተፈርዶብዎት ታስረው ነበር፤ እስኪ ስለ እሱ ይንገሩን፤ መቼ፣ እንዴትና ለምን ታሰሩ?
ታዲዮስ፡- የታሰርኩት በሚያዚያ ወር 1993 ዓ.ም ነው፡፡ የታሰርኩትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ረብሻ ስለነበር የጥፋቱ ተሳታፊነህ ተብዬ ነው፡፡ ወደ ሸዋሮቢት እስር ቤት ተወሰድኩ፡፡ ሸዋሮቢት ሦስት ወር እንደታሰርኩ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ የሚያስከስሰኝ ነገር ስላልነበረ ተለቀቅኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚያ በኋላም ታስረው እንደነበር ሰምቻለሁ፤ እውነት ይሆን?
ታዲዮስ፡- ከቅንጅት ጋር በተያያዘ በ1997 ዓ.ም ታስሬያለሁ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ቅንጅትን ለመመለስ የውስጥ አርበኛ ሆናችሁ እየሰራችሁ ነው ተብዬ ታሰርኩ፡፡ ይህ ሲሆን ከቤቴም ወረቀት ተገኝቷል፡፡ የተገኘው ወረቀትም በህቡዕ ገብተን እንዴት ይሄን መንግሥት መጣል እንዳለብን፤ የፋይናንስ አያያዝና የሰው ኃይል ምልመላ፣ እንዴት ግንኙነት ማድረግ እንዳለብን የሚጠራ የእጅ ጽሑፍ ነበር፡፡ ፖሊስ ይዞም ፍርድ ቤት አቅርቦታል፡፡ ኦርጅናሉ በፍርድ ቤት ይገኛል፡፡ በዚህኛው ክስ ነው 15 ዓመት የተፈረደብኝ፡፡ ነገር ግን እነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳሀቅ እና እነ ፓስተር ዳንኤል ባደረጉት ሽምግልና አንድ ዓመት ተኩል ታስሬ ተፈታሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የ1993ቱም ሆነ የ1997ቱ የታሰሩባቸው ምክንያቶች በሚጽፏቸው ጽሑፎች አይደለም ማለት ነው?
ታዲዮስ፡- በምጽፋቸው ጽሑፎች አይደለም፤ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ በማድረግ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የከተማው ህዝብ እንዲበጠበጥና ህዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ ቀስቅሳችኋል ተብሎ ነው፡፡ በእርግጥ በዚያው ወቅት ጋዜጣ ላይም ጠንካራ ሃሳቦችን እጽፍ ነበር፡፡ የምጽፋቸውም የቅስቀሳ ሃሳቦች ናቸው፤ ይሁን እንጂ ግን ክሱ ላይ የጋዜጣው ጽሑፍ አልተነሳም፡፡ ሁከት በመፍጠር ተብሎ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ምን አደረጉ?
ታዲዮስ፡- ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በአስኳል ጋዜጣ ላይ ‹‹ወግድ ይሁዳ›› በሚል ርዕስ የምፅፈውን ቀጠልኩበት፡፡ ወግድ ይሁዳ ለሦስት ዓመታት ያህል የዘለቀ ረጅምና ተከታታይ ጽሑፍ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የታሰሩት በሚጽፉት ጽሑፍ ሳይሆን በሌላ የፖለቲካ ቅስቀሳ ከሆነ በ «ወግድ ይሁዳ» ለምን አልተከሰሱም?
ታዲዮስ፡- በ«ወግድ ይሁዳ»ም ተከስሻለሁ፡፡ እንዲያውም ገና ጽሑፉን ሳልጨርስ ነው የተከሰስኩት፡፡ ታስሬም ዋስ ጠርቼ ተለቅቄያለሁ፡፡ ተለቅቄ እያለሁ ግን ከቅንጅት ጋር የተያያዘው ክስ ተጀመረና በሱ ታሰርኩ፡፡ ታስሬ ክሱን እየተከታተልኩ ጠዋት ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በሚል፤ ከሰዓት ደግሞ እንደ ሀሽሽና ጋንጃ፣ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ሲያዘዋውሩ ከተያዙት ጋር እታሰራለሁ፡፡ እነዚያ ውስጥ ደግሞ የአዕምሮ ህመምተኞች ሁሉ አሉ፤ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በወግድ ይሁዳ ጽሑፍ ግን በነጻ ነው የተለቀቅኩት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካ አቋምዎ ሳቢያ ከእስር ቤት ውጭ ምን አጋጥሞዎት ያውቃል?
ታዲዮስ፡- በጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም ፒያሳ ምኒልክ አደባባይ አካባቢ ሰዎችን እየያዙ ነበር፡፡ እኔን እዚያ አግኝተውኝ ከምኒልክ አደባባይ ጀምሮ ያለምንም መቋረጥ እየደበደቡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መሥሪያ ቤት ግቢ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ይሄም ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነበር የለቀቁኝ፡፡ ብዙ ያስሩኛል ብዬ ስጠብቅ ለቀቁኝ፡፡ ሌሊት ስምንት ሰዓት ሲለቁኝ ግን ወደከተማ መግባት በጣም ከባድ ነበር የሆነብኝ፡፡ አካባቢው ሁሉ በታንክ የተጠመደ ነው፡፡ ይገሉኛል ብየም ሰጋሁ፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን እስከ ንጋት 11 ሰዓት ድረስ እዚያው አካባቢ ቆየን፡፡ ከዚያ በኋላ እንደምንም ወደቤቴ ሄድኩኝ፡፡ ሰውነቴ ግን ተጠባብሶ ጉበት መስሎ ነበር፡፡ የፈነዳ ነገር የለውም፤ ያበጠ ስለነበር በጣም ነበር የሚያመኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከቅንጅት ፓርቲ ጋር የነበረዎት ግንኙነት ምን ነበር?
ታዲዮስ፡- የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል አልነበርኩም፤ ዝም ብሎ አባል ብቻ ነበርኩ፡፡ ግን ዕጩ ሆኜ ክፍለ ሀገር ላይም ለውድድር ቀርቤ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከፖለቲካውና ከጋዜጠኝነት ሙያው የትኛውን ነው ሥራዬ ነው የሚሉት?
ታዲዮስ፡- በሁለቱም ተሳትፊያለሁ፡፡ በጋዜጠኝነቱ የኔን ያህል ደፍሮ የጻፈ የግል ጋዜጣ የለም ብዬ ነው የማምነው፤ ለዚያውም በሰይፍ ስለት ላይ ቆሜ ነው የፃፍኩት፡፡ ብዙ የግል ጋዜጦች የመንግሥትን ደካማ ጎን እየጎረጎሩ ነው የሚጽፉት፡፡እኔ ግን የሕዝቡንም ሆነ የመንግሥትን ድክመትና ጥንካሬም ነበር የምጽፈው፡፡ በ«ወግድ ይሁዳ» ተከስሼ ስቀርብ እንኳን ምንም አይነት ምስክር አላስፈለገም፤ የራሴ ፎቶ፣ የራሴው ስምና ጽሑፍ ነው ለፍርድ ቤት የቀረበው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሚጽፉባቸው ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ ቢሆኑ ኖሮ ያደርጉት ነበር?
ታዲዮስ፡- እንዲያውም ዓምደኛ ሆኜ ከምጽፈው በላይ አደርግ ነበር፡፡ ‹‹የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ›› የተባለው መጽሐፍ ላይ ብዙ ነገር ጽፌያለሁ፡፡ መጽሐፉን ስጽፍ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ነበር፡፡ ከ«ወግድ ይሁዳ» ጀምሮ ሌሎች የማይደፈሩ ሃሳቦችንም ነው የጻፍኩበት፡፡ ማተሚያ ቤቶች እንኳን አናትምም ብለውኝ ነበር፡፡ ይሄም መጽሐፍ የራሴው ስምና የራሴው ፎቶ ያለበት ነው፡፡ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ‹‹ለገዥዎቻችን ላለመታዘዝ አቋም እንውሰድ….›› ይላል፤ ስለዚህ ዋና አዘጋጅ ብሆን ኖሮ ከዚህም በላይ ነበር የምሰራው፡፡ የራሴ ጋዜጣም ለመመስረት ሞክሬ ነበር፡፡ ከአሥር ሺህ ብር በላይ ያስፈልግ ስለነበር ያንን ማድረግ ስላልቻልኩ ነው የቀረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጋዜጠኛ ከፓርቲም ሆነ ከየትኛውም ፓርቲ ገለልተኛ መሆን እንዳለበት በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እርስዎ ግን የቅንጅት አባል ነበሩ፤ ይሄ ልክ ነው ብለው ያስባሉ?
ታዲዮስ፡- ጋዜጠኛ የፓርቲ አባል መሆን ይችላል፤ እንደማንኛውም ሰው የመሆን መብት አለው፡፡ ዳሩ ግን የሰናፋጭ ቅንጣት ታክል አድሎ ማሳየት የለበትም፡፡ ለህሊናው ታማኝ መሆን አለበት፡፡ አባል የሆነበትን ፓርቲ ደካማ ጎን ሁሉ ማውጣት አለበት፡፡ ይሄ ሲሆን ግን እንደ ጋዜጠኛ የፓርቲውን ምሥጢርም መጠበቅ አለበት፡፡ ይሄን ለመወሰን አዕምሮው ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ከፈለጉ ከፓርቲ ያስወጡት እንጂ ለሙያው ታማኝ መሆን አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የቅንጅት አባል ሆነው ቅንጅት ውስጥ ያለውን ችግር ጽፈው ያውቃሉ?
ታዲዮስ፡- የራሴ ጋዜጣ የለኝም፤ በወቅቱ የምጽፍበት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፈቃደኛ ሊሆንልኝ አልቻለም ነበር፡፡ በጀት የሚያገኝበት መንገድ ሌላ ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነልኝም፡፡ የራሴ ጋዜጣ ቢሆን ኖሮ ግን አወጣው ነበር፡፡

ስብሰባ ባለበት ሁሉ ግን ቅንጅትን እየኮነንኩ ተናግሪያለሁ፡፡ ደካሞች ነን፣ ተልፈስፍሰናል እያልኩ ተናግሪያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ቢለቅ እንኳን መምራት የማንችል ነን እያልኩ ተናግሪያለሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮች ሁኔታው ሲፈቅድ ነው የሚደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በ‹‹ወግድ ይሁዳ›› ጽሑፍ ከመንግሥት ይልቅ በግለሰቦች የደረሰብዎት ዛቻና ማስፈራራት እንደነበር ሰምቻለሁ፤ ይሄ ነገር እውነት ነው?
ታዲዮስ፡- ትክክል ነው፡፡ መንግሥት በጋዜጣው ሰበብ መክሰሱ እንደተጠበቀ ሆኖ በግለሰቦች ብዙ በደል ደርሶብኛል፡፡

አንድ ጊዜ ሁለት ሰዎች አገኙኝና ከበቡኝ፡፡ ከአጠገባቸው ራቅ ራቅ ያሉትም ዙሪያዬን ከበው ያያሉ፡፡ ‹‹ተመልከቱት! ይሄ ጀግናውን የትግራይን ህዝብ እየተሳደበ በየጋዜጣው ሲጽፍ የነበረ ታዲዮስ ታንቱ የሚባለው ነው» እያሉ ከበቡኝ፡፡ ምን ሊያደርጉኝ ይሆን? እያልኩ በመጠራጠር መልስ መስጠት ጀመርኩ፡፡ ተከራከርን፡፡ መጀመሪያ ዘለፋ ነበር፤ ቀጥሎ ግን እየለሰለሱ መጡ፡፡ እነርሱ ያሉትን ቃላት መናገር ባልፈልግም ብዙ ነገር አሉኝ፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ አንዱ ገና ከርቀት ሲያየኝ ‹‹ታዲዮስ!›› አለ፤ ታንቱ አልኩና የአባቴን ስም ጨመርኩለት፡፡ ጓደኛ ነበረው፤ ‹‹You Cannot Insult People! ትግራይ አሁን ምን አደረገ?›› አለና በጣም ተናዶ አጠገቤ መጣ፡፡ ምን ማለትህ ነው? ጋዜጣ ላይ ለጻፍኩት ጽሑፍ ጋዜጣ ላይ መልስ ስጥ አልኩት፡፡ ‹‹እኔ አንተን ከሰው ቆጥሬ ጋዜጣ ላይ መልስ አልሰጥም፤ በሁለት ቀናት ውስጥ እኔ የምወስደውን እርምጃ ታያለሀ!›› አለኝ፡፡ ይሄ ሁሉ ከወግድ ይሁዳ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ይሄ ጽሑፍ ደግሞ ኢንተርኔት ላይ ተለቆ ነበር፡፡
አሁንም ሌላ ጊዜ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር አካባቢ ከቱሪስት ሆቴል ፊት ለፊት አንድ ወጣት ገና ሲያየኝ ከርቀት ስድብ ጀመረ፡፡ ‹‹አንተ የምትሰድባቸው ሰዎች በሰሩት ልማት ነው የምትጠቀመው፤ አሁን አንተ ለኢትዮጵያ ምን ትጠቅማለህ?›› እያለ ዙሪያውን ያለውን ሕንጻ ያሳየኝ ጀመር፡፡ብዙ ጊዜ ደግሞ ከመኪና ውስጥ አንገታቸውን እያወጡ እየሰደቡኝና እየተፉብኝ የሚያልፉ አሉ፡፡

የራሴ ጎሳ አባላት የሆኑት ወላይታዎች ሳይቀር በጣም ይጠሉኛል፡፡ ‹‹ለእኛ ልማት፣ ለእኛ ዕኩልነት ይዞ የመጣውን፣ ከእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረገውን ሥርዓት፣ እነ ተሾመ ቶጋን ሚኒስትር ያደረገውን ሥርዓት፣ እንዴት ትኮንናለህ? የቀድሞው ሥርዓት እኮ እኛን ባሪያ እያለ ይሳደባል፤ አንተ ቁጥር አንድ የአማራ አሽከር ነህ!›› እያሉ ይሰድቡኛል፡፡ አንድ አቶ ኃይለማርያም የተወለዱበት አካባቢ የተወለደ ሰው ደግሞ ወግድ ይሁዳ ጽሑፌን የነፍጠኛ አስተሳሰብ ነው ብለው ይጠሉታል፡፡ ወላይታ ብቻ አይደለም ሌሎችም የደቡብ አካባቢዎች ተመሳሳይ እምነት ነበር ያላቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- «ወግድ ይሁዳ» የሚለው ተከታታይ ጽሁፍ በምን ላይ ነበር የሚያተኩር?
ታዲዮስ፡- ወግድ ይሁዳ በአመዛኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ነበር የሚያተኩር፤ ይህን አልክድም፡፡ ይሄ የእኔ አተያይ ነው፡፡ መነሻዬም በላይ ግደይና ዶክተር አሰፋ ሀብተማርያም የጻፉት የታሪክ መጽሐፍት ናቸው፡፡ በእነዚህ የታሪክ መጻሕፍት ሁሉም ነገር የመጣው ከትግራይ እንደሆነና ሌላው ምንም እንደማያውቅ ተደርጎ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ለአገር ያስተማረ ትግራይ ነው የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡ ይሄንን ነው እኔ የሞገትኩ፡፡ ምዕራፍ በምዕራፍ እየለየሁ እውነት እውነቱን ተናግሪያለሁ፡፡

ይህን ሁሉ ሳደርግ ይገሉሃል እየተባልኩ በተደጋጋሚ ተመክሪያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ተስፋዬ የሚባል ጋዜጠኛ ቤቱ ተገሎ ተገኝቷል፤ ደብረ ብርሃንም አንድ ጋዜጠኛ ተገሏል፡፡ ዮናስ ገብረማርያም የሚባል የመንግሥት ጋዜጠኛም ተገሏል፤ የሸዋሉል የምትባል ጋዜጠኛ ተገላለች፡፡ እነዚህን እየጠቀሱ አንተም ትገደላለህ እረፍ ተብዬ ተመክሬ ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ለጋዜጠኝነት የሚገባውን ያህል ሰርቻለሁ አልልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በጋዜጠኝነትም ሆነ በፖለቲካው ተሳትፎዎ ድክመቴ ነው የሚሉት ምንድነው?
ታዲዮስ፡- የራሴ ጋዜጣ ሊኖረኝ ይገባ ነበር፡፡ የራሴ ጋዜጣ ባለመኖሩም ያልሰራኋቸው አሉ፡፡ የጋዜጣው ባለቤቶች ከእኔ ፍላጎት ውጭ የነካኩበት ጊዜም ነበር፡፡ ይሄ ከመንግሥት ጋር ያጋጨናል አናወጣውም በማለት ያስቀሩብኝ ጽሑፍ አለ፡፡ የራሴ ጋዜጣ ቢኖረኝ ግን ይሄ ሁሉ አይሆንም ነበር፡፡ ይህን አለማድረጌ እንደድክመት እቆጥረዋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የጠቀሷቸው ችግሮች ሁሉ በኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ የሆኑ ናቸው፡፡ የጦር ኃይሎች ጋዜጠኛ ነበሩና እስኪ በደርግ ጊዜ የነበረውን የጋዜጠኝነት ሁኔታ ይንገሩኝ?
ታዲዮስ፡- በደርግ ሥርዓት የከፋ በደል አልደረሰብኝም፡፡ ከአንድ ኮሎኔል ጋር ተጋጭቼ ከሥራ ታግጄ ነበር፡፡ ኮሎኔሉ ከሀገር ሲለቅ ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፡፡ ከዚህ ውጭ በደርግ የማስታውሰው ከባድ ነገር አልደረሰብኝም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የፕሬስ ነጻነት በደርግ ሥርዓት ይሻል ነበር ማለት ነው?
ታዲዮስ፡- አይ! አይሻልም፡፡ በደርግ ጊዜ በነፃነት መፃፍ አይቻልም ነበር። ይህን ስለምናውቅ እኛም ደፍረን አንጽፍም፡፡ ነጻ ጋዜጣም አልነበረም፡፡ በጦር ኃይሎች ጋዜጣ ብቻ ነበር የምንሰራው፡፡ አዲስ ዘመን እና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያም የመንግሥት ልሳን ሆነው ነበር የሚሰሩት፡፡ ስለዚህ የፕሬስ ነጻነቱ በደርግ የተሻለ ነበር ማለት አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጋዜጠኝነት ተምረዋል?
ታዲዮስ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ትምህርቴ ውስጥ ሁለት ኮርስ ወስጃለሁ፡፡ ሌላው በንባብ እና በሥራ ልምድ ነው ያዳበርኩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ደም መላሽ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ባልተሰሙ እውነቶች›› የሚሉ መጻሕፍት እንደፃፉ ይታወቃል፤ ወደፊትስ ምን አስበዋል?
ታዲዮስ፡- አሳታሚ አጥቼ ነው እንጂ ያዘጋጀሁት መጽሐፍ አለ፡፡ መጽሐፉ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ አሁን አሳታሚ እያፈላለኩ ነው ካገኘሁ አሳትመዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥተው ያውቃሉ?
ታዲዮስ፡- ጂቡቲ እንኳን ሄጄ አላውቅም!
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ታዲዮስ፡- አሁን እየጻፍኩ ነው፡፡ ጋዜጠኝነትን የሚመለከቱ ነገሮችን ነው የምጽፍ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የየትኛውም ፖለቲካ አባል አይደለሁም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሙያው ለረጅም ዓመታት ስለሰሩ ስለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ምን ይላሉ?
ታዲዮስ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነት ሞቶ ነው የተወለደው፡፡ ጋዜጠኝነት ከመንግሥት እጅ ወጥቶ ነጻ ኩባንያ ነው መሆን ያለበት፡፡

ጋዜጠኞችም ከማንም የማያንሱ ባለሙያዎች እንደሆኑ ማመን አለባቸው፡፡ ባለሥልጣንን ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ በከፍተኛ የራስ መተማመን እንጂ ከአጠገቡ አቀርቅረው መሆን የለበትም፡፡ አሁን ጋዜጣም መጽሔትም አለ ብዬ አላምንም፤ ግን አነሰም በዛም መረጃ የሚሰጡ አሉ፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ወንጀል ሲፈጸም ፖሊስ ዝርዝር እስከሚያወጣ ነው የሚጠበቀው፤ ይሄ መሆን አልነበረበትም፡፡ ጋዜጠኛው ቀድሞ ነው ለህብረተሰቡ መረጃ መስጠት ያለበት፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሆነ ነገር ሲከሰት ባለሥልጣናት መግለጫ እስከሚሰጡ ነው የሚጠበቀው፡፡ ጋዜጠኛ እኮ ከፖሊስ በፊት ነው መረጃ ጎርጉሮ ማውጣት ያለበት፡፡ አሁን ያሉት ጋዜጦችና መጽሔቶች ይህን የሚያደርጉ አይደሉም፤ ፖሊስ የሰጠውን መግለጫ መለጠፍ ነው፡፡ ከላይ የራሱን ፎቶ አስቀምጦ ከታች የፖሊስን መግለጫ ይለጥፋል! አሁን ይሄ አያሳፍርም?
ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ተያዙ ብሎ ፖሊስ መግለጫ ሲሰጥ ጋዜጠኛ እኮ ይሄንን እንደወረደ ማቅረብ የለበትም፤ እንዴት ተያዙ? መቼ ተያዙ? የቱን ባንክ ሲዘርፉ? ብሎ ማረጋገጥ አለበት፡፡ እንዴት ባለሥልጣን የሰጠውን ብቻ አምኖ ይቀበላል?
ለዚህም ነው ሚዲያ ኩባንያ መሆን አለበት የምለው፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲያስፈልግ ኩባንያው ራሱ ነው መጥራት ያለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያስፈልጋልና ስጡኝ ብሎ ራሱ መጠየቅ ያለበት እንጂ ባለሥልጣኑ በሚፈልገው መንገድ ያዘጋጀውን ማስተላለፍ አይደለም፡፡ የባለሥልጣኑን ማስታወሻ መጠየቅ አለበት፤ ይሄ ማለት ግን ግለሰባዊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ይጠይቅ ማለት አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ የሚተወውንም ነገር መተው ያለበት እባረራለሁ በሚል ፍራቻ ሳይሆን ይሄ የአገር ምሥጢር ነው፣ ሕዝብንም የሚጠቅም አይደለም የሚለውን በራሱ አምኖበት ነው፡፡

እውነተኛ ጋዜጠኛና መንግሥት ምንጊዜም የሚዋደዱ አይደሉም፤ ስለዚህ ጋዜጠኛው ይህን ማወቅ አለበት እንጂ መንግሥትን አስቀይማለሁ ማለት የለበትም
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ስለቤተሰብዎ ትንሽ ይንገሩን?
ታዲዮስ፡- ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ አምስቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት ናት፡፡ ትልቁ ልጄ አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፤ የተቀሩትም ሁለተኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ነው ምኖረው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!
ታዲዮስ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011

ዋለልኝ አየለ