አቶ ገመቹ ዱቢሶ – ጠንካራና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ አስገራሚው የመንግስት ባለስልጣን


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ዘወትር የሚታዩ አይደሉም፤ በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአገሪቱን የመንግሥት ተቋማት ዓመታዊ ሪፖርትና የኦዲት ግኝት ሲያቀርቡ የተቋማት ኃላፊዎች ጭንቀት ከፊታቸው ላይ ይነበባል። እርሳቸው በተደጋጋሚ የታየው የተቋማት የአሰራር ግድፈት ዳግመኛ ያለመሻሻሉ እያበሳጫቸው፤ አንዳንዴም እልህ በተሞላበት አነጋገር፤ አንዳንዴም አሰራራቸውን እንዲያስተካክሉ ተግሳፅ ቢጤ ቃላትን ይወረውራሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ለስለስ ሲሉም እባካችሁ አሰራራችሁን ህጋዊ መስመር አስይዙት ሲሉ ይስተዋላሉ።

ሰውየው ይህንን ይበሉ እንጂ የየተቋማቱ ኃላፊዎች አሰራር ከሪፖርቱ መደመጥ በኋላ አድሮ ቃሪያ እየሆነባቸው በቀጣዩ ዓመት የወጪ ብክነቱ ጨምሮ፤ ህጋዊ አሰራር ተጥሶ መገኘቱን በድጋሚ በሪፖርታቸው ያቀርቡታል። እርሳቸውም እባካችሁ አስተካክሉ ማለትን አይተዉትም። መንግሥት ያንን ሁሉ የተቋማቱን ግድፈት አይቶ የማረሚያ እርምጃ ያለመውሰዱ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው አገርና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በቆራጥነትና በድፍረት እየተወጡ ያሉ እኚህ ኢትዮጵያዊ በ1957 ዓ.ም. አርሲ ክፍለ አገር ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ተወለዱ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን «ሀ» ብለው የጀመሩት በዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ሉተራን ሚሽን ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከ 1ኛ እስከ 3ተኛ ክፍል እዚያ ከተማሩ በኋላ ከ4 እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ ዝዋይ ዱግዳ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

የ2ተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰላ ተምረው በ1976 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የሚሆን ነጥብ በማግኘት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በ1979 ዓ.ም. መጨረሻም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመከታተል እንግሊዝ አገር በሚገኘው «ግላስ ዶክ ካሊዶኒያን» ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀቁ፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ።

በ2000 ዓ.ም. በሹመት ወደ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተዛውረው ሥራ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ በታላቅ ታማኝነት፣ በግልጽና በነጻነት ማንንም ሳይፈሩ የኦዲት ግኝቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የዛሬው የአዲስ ዘመን የእለተ ዓርብ ዕትማችን እንግዳ ያደረግናቸው እኒህን ጠንካራና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰው ናቸው። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

አዲስ ዘመን 2000 . ወደ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሲመጡ ስራውን እንዴት አገኙት?

አቶ ገመቹ እንግዲህ ኦዲትን በትምህርት ተምሬያለሁ፤ ከዚያ ባሻገር ቀደም ብዬ ባገለገልኩባቸው መሥሪያ ቤቶች ሂሳቤን ኦዲት አስደርጌያለሁ። ከዚህ ውጪ ስለ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ብዙም እውቀቱ አልነበረኝም። ነገር ግን ኃላፊነቱ ሲሰጠኝ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ስለነበርኩኝ አልከበደኝም ።

እኔ የመጣሁበት ወቅት መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (ቢ.ፒ.አር.) እየተሠራ የነበረበት ጊዜ ስለነበር ብዙ ስራዎች ቀልለውልኛል። ይህንን ጅምር ለማስቀጠልም ተሞክሮ ለመቀመር ወደ ተለያዩ አገራት ሄደናል። እኔም የምመራው ቡደን ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ ተቋማችን ምን ዓይነት መልክ መያዝ እንዳለበት፤ እንዲሁም የት መድረስ እንደሚፈለግ በግልጽ በማስቀመጥ ጥሩ ሥራዎችን አከናውነንም ተመልሰናል ለስራውም ጥሩ መደላደልን ፈጥሮልኛል።

ያኔ ሥራውን ስጀምር እንደ ችግር ይነሳ የነበረው የአገሪቱ የኦዲት ሽፋን በጣም ትንሽ መሆኑ ነበር፤ በዚህም ኦዲት መደረግ ከሚገባቸው ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 32 በመቶዎቹ ብቻ ነበሩ ኦዲት የሚደረጉት፤ እነዚህም ቢሆኑ በየዓመቱ አይደረጉም ነበር። ይህንን ቀይረን መቶ በመቶ እናመጣዋለን የሚል ግብ አስቀምጠን በመንቀሳቀስ ውጤታማ ሆነናል።

ሌላው የመሥሪያ ቤቱን የህግ ማዕቀፍ ማሻሻልና ተቋሙ ነጻና ገለልተኛ የሚሆንበትን የህግ ማዕቀፍ ለማግኘት በዚህም እንዲደራጅ፤ ዋና ኦዲተር ሆኖ የሚመጣው ሰውም የአገልግሎት ጊዜ ገደብ እንዲኖረው ማድረግ ፤ የበጀት የአስተዳደር ነጻነቶችን የሚያጎናጽፉ የህግ መሠረቶችን መጣል የመጀመሪያ ሥራዎች የነበሩ ሲሆን፤ እነዚህንም በ2001 ዓ.ም. ሲሰራ ቆይቶ ግንቦት 2002 ዓ.ም. ላይ አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ሆኗል። በዚህም ተቋሙ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል ።

በሌላ በኩል የኦዲት አሰራር ዘዴውን መለወጥ በተለይም ወቅታዊነቱን የጠበቀ የኦዲት ሪፖርት ለማምጣት በእቅድ የተያዘ ስለነበር የአሠራር ዘዴውን ቀድሞ ከነበረው በመቀየርና ሂሳብ ከተዘጋ በኋላ ይሰራ የነበረውን ሂደት በመተው ኦዲት ሂሳብ ሳይዘጋ እንዲጀመር ልክ ሂሳቡ ሲዘጋ የማጠናቀቂያ ስራዎች እንዲሰሩ ለማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመን በተለይም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን ወደ ኦዲት ለማምጣት የታሰበው ሀሳብ ተሳክቷል 32 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል?

አቶ ገመቹ፤ አዎ! ተሳክቷል አሁን ላይ ሁሉም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በሚባል ደረጃ ሂሳባቸውን ኦዲት ያስደርጋሉ ።

አዲስ ዘመን፤ ባለፉት 10 እና 11 ዓመታት እርስዎ በአገሪቱ በተለይም በባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሚታዩ የኦዲት ከፍተቶችን ለመግለጽ ሞክረዋል፤ እርምጃ ሊወስድ የሚገባው አካል ግን ምንም ሲሰራ አይታይምና ይህ በእርስዎ ላይ ምን ስሜት ይፈጥራል?

አቶ ገመቹ፤ እኔ አንግዲህ እንደ አንድ ኃላፊ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ምንም ሳንሰንፍ መስራት የሚገባንን ሰርተናል ብዬ አስባለሁ። መጮህ በሚገባን ልክም ጮኸናል። ስራው በህብረተሰቡ ዘንድ የበለጠ እንዲታወቅ ተቋሙም ተዓማኒ እንዲሆን ጥረናል፤ ከእኛ የሚጠበቀውም ይኸው ነው። ግን በሚገኙ የኦዲት ግኝቶች አማካይነት ደግሞ እርምጃ መወሰድ ያስፈልጋል፤ ይህን ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት መውሰድ ያለበት እያንዳንዱን ባለበጀት መሥሪያ ቤት ሲሆን ቀጥሎ መሥሪያ ቤቶቹ ተጠሪ የሆኑለት አካል፤ ከዛም አለፍ ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ናቸው።

እዚህ ላይ ከፋይናንስ አንጻር የገንዘብ ሚኒስቴርም የራሱን ኃላፊነት መወጣት ነበረበት። ከነኝህ ሁሉ ሲያልፍ ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝም ብሎ ቁጭ ማለት አልነበረበትም። ግን ይህ ባለመሆኑ በሚፈለገው ልክ ለውጥ መምጣት አልቻለም።

በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት እኔ ምክር ቤት የኦዲት ግኝት ሪፖርቴን ሳቀርብ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ችግር ስለነበር «አንተ ምን እርምጃ ወሰድክ?» ብለው ይጠይቁኝ ነበር።

ይህንን በመረዳትም በምክር ቤቱ ያሉ ሁሉንም ተቋማት የሚከታተሉ ቋሚ ኮሚቴዎችን የዋና ኦዲተር የሥራ ኃላፊነት ምንድን ነው? የሚለውን ማስተማር ጀመርን፤ ከዚያም አለፍ ሲል በተለይም ተቋሙን የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴዎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ በመሰራቱ ምክር ቤቱ ግንዛቤው አደገ፤ እኔን መጠየቅ ትቶም የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱ መወትወት ጀመረ፤ ነገር ግን ጨክኖና ገፍቶ ጉዳዩ ሊደርስ በሚገባው ደረጃ ማድረስ አልቻለም።

በመሆኑም በአጭሩ ልንቀጫቸው የሚቻሉ የኦዲት ክፍተቶች ከዓመት ዓመት እየተሻገሩ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደሩ በሰዎችም ዘንድ የማናለብኝነት ስሜት እንዲፈጠር አድርገዋል።

አሁን ላይ ግን የተሻለ ሁኔታ ይታያል በምክር ቤቱ ግፊቶች እየመጡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጀንዳው ላይ መነጋገር የገንዘብ ሚኒስቴርም መርሐ ግብር ቀርጾ እንዲያቀርብላቸው ማድረግ በመጀመራቸው ጥሩ እርምጃ እየታየ ነው።

አዲስ ዘመን፤ በአንድ ወቅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በየዓመቱ በማቀርበው ሪፖርት ለውጥ የማያመጣ ከሆነ የእኔ እዚህ መቀመጥ ትርጉም የለውም ፤ብለው ነበርና አሁንስ ለውጥ እያዩ ነው የቀጠሉት?

አቶ ገመቹ፤ በዚህ ዓመት ያቀረብኩት 10ኛ ሪፖርቴን ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ ሪፖርትን ሳነብ የሚሰማኝ «ለውጥ የማላመጣ ከሆነ እኔ እዚህ ምን እሰራለሁ » የሚል ነው፤ ይህ ስሜት ይሰማኝ እንጂ እኔ የምችለውን አድርጌያለሁ፤ ነገር ግን የሪፖርቱን ውጤት ተከትሎ በየደረጃው ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች በመዘግየታቸው በቀላሉ ሊቀረፉና ሊስተካከሉ የሚችሉ ክፍተቶች ሳይሞሉ ቀርተዋል፤ ምናልባት በየዓመቱ የማቀርበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ እርምጃ ተወስዶ ቢሆን ኖሮ ሰዎችን ማትረፍ፣ የግብር ከፋዩን ገንዘብ ከዝርፊያ ማዳን፣ የመንግሥትን ተአማኒነትን ማሳደግ፣ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ይቻል ነበር፤ ተቋማትም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተሻለ ደረጃ መወጣት ይችሉም ነበር።

ግን እርምጃ በመዘግየቱ ወይም በመቅረቱ እየተንጫጫን ኖረናል። ከዚህ በኋላ ግን ምናልባት መሻሻሎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ፤ ለከዚህ በፊቱ እንደ ዜጋም እንደ ባለሙያም አዝናለሁ።

እኔ በዚህ ደረጃ አገሬን እንዳገለግል እድል ማግኘቴ በጣም ትልቅ ነገር በመሆኑ ኃላፊነቴም ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ችግሩ እንዲቀረፍ በማድረጉ በኩል አልተሳካልኝም በመጮህ ግን ተዋጥቶልኛል ። ጩኸት ግን ለውጥ ካላመጣ ጠቃሚ አይደለም።

አዲስ ዘመን፤ እርምጃ የማይወሰደውና ከዓመት ዓመት ለውጥ የማይታየው ለምን ይመስሎታል?

አቶ ገመቹ፤አንዱ የግንዛቤ እጥረት ነው፤ ሁለተኛውና ዋናው ግን ሰዎች ተጠያቂ አለመሆናቸው ነው። ምናልባት ተጠያቂነት ሲባል ማሰር ብቻ ላይሆን ይችላል፤ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችሉ ነበር። ግን የትኛውም ተግባራዊ አልሆነም።ይህ ባለመሆኑ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

አዲስ ዘመን፤ከዚህስ በኋላ ለውጥ ይመጣል ብለው ያስባሉ ?

አቶ ገመቹ፤አሁን የተያዘበት አግባብ ጥሩ በመሆኑና መንግሥትም ዝም ባለማለቱ ለውጥ ይለወጣል ብዬ አስባለሁ። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በዚህ ዓመት እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ሲፈራረም አንዱ መለኪያው ኦዲት መሆኑ ነው። ሌላው ምክር ቤቱ ውስጥ ያለው እርምጃ መወሰድ አለበት የሚለው ሀሳብ መነሳሳት በጣም ያስደስታል፤ ከዚህ አንጻርም እንደ ባለፉት ጊዜያት ዓይነት የኦዲት ክፍተት በምንም መንገድ ይቀጥላል ብዬ አላስብም። አሁንም የሚታይ እርምጃ አይወሰድ እንጂ በእነዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በተቋማት ኃላፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የእጠየቅ ይሆን ፍራቻ ነግሷል፤ ይህንን አስተሳሰብ ማምጣት በራሱ ውጤት ነው ።

በዚህ ዓመት በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መነሻነት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ለጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እርምጃ እንድትወስዱ ሲሉ ደብዳቤ ጽፈዋል፤ ይህ ለእኛም ለሌሎች አካላትም ግልባጭ ደርሶናል። ስለዚህ ጩኸታችን በዚህ ደረጃ ፍሬ እያፈራ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ከእናንተ ጋር ነው ወይስ ከምክር ቤቱ ጋር ነው አብሮ የሚሰራው?

አቶ ገመቹ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በራሱ ይሰራል። ግን የመረጃ ምንጮቹ እኛ እንሆናለን፤ ምክር ቤቱ ደግሞ እርምጃው ተወስዶ ማየት ነው የሚፈልገው፤ በዚህ ደረጃ መንቀሳቀሱ ደግሞ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያሳያል። እኛም ከጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጋር የጀመርነው ሥራ አለ እሱም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፤ ከአሁን በኋላ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ፍሬ ያፈራሉ ማለት ይቻላልን?

አቶ ገመቹ፤ አዎ በሚገባ፤ ሪፖርቶች እንደከዚህ ቀደሙ የተለመዱ ናቸው ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፤ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ ከአሁን ወዲህ ስራው የእቃ ዕቃ ጨዋታ የሚሆንበት ሁኔታ አብቅቷል። በመሆኑም ሁሉም እራሱን፣ ቤተሰቡንና ተቋሙን ቢጠብቅ እንደሚሻልም አሁንም እናገራለሁ። ይሰማሉ ብዬም አስባለሁ።

መንግሥት ሙስናን፣ የመንግሥት ሀብትን አለአግባብ መጠቀምንና ማባከንን በጥብቅ እዋጋዋለሁ እያለ ነው። ይህ ደግሞ የመንግሥትም የምክር ቤቱም ሀሳብ ከመሆኑም በላይ እኛም እስከ አሁን ስናደርግ የነበረውን ሥራ የበለጠ ገፍተን እንድንቀጥል የሚያደርገን ነው።

አዲስ ዘመን፤ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥራውን ሲያከናውን ጉድለቱ የሚጎላው የገንዘቡ ነው ወይስ የክዋኔ ኦዲት ?

አቶ ገመቹ፤ ሁለቱም ናቸው፤ ገንዘቡ ብዙ የሚመስለው በቁጥር ስለሚገለጽ ነው። ያም ቢሆን ግን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግዢ ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው። ምንም እንኳን የግዢ ስርዓታችን ጠበቅ ያለና ግልጽነት የተሞላበት ቢሆንም ይህንን አልፎ የህግ ጥሰቶች ይደረጋሉ። ገንዘቦች ይመዘበራሉ። ዋና መንስኤው ቀድሞ አለማቀድና አስቸኳይ በሚል ግዢ ህግ መጣስ ነው ። ሌላው እቅድ ውስጥ የተካተተን ግዢ እንኳን ተከትሎ ማስፈጸም የለም።

ትልቁና መሠረታዊው የገንዘብ ጉድለት የሚታይበት ዘርፍ ግንባታ ነው፤ ብዙ ግንባታዎች ወይም ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ጥናት ተደርጎ አዋጭ መሆናቸው ተረጋግጦ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ተቀባይነትም አግኝቶ መጀመር ቢኖርባቸውም ብዙዎቹ እነዚህን ደረጃዎች ሳይከተሉ ይጀመራሉ።

ዘንድሮ እንኳን ባቀረብነው ሪፖርት ላይ ምንም ሳይጠኑ ፕሮጀክቶች ተጀምረው 250 ሚሊየን ብር ገደማ ከወጣባቸው በኋላ የተሰረዙ አሉ። ይህ በጣም አስደንጋጭ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ሳይጠኑ በቂ ዲዛይን ሳይዘጋጅላቸው ወደ ሥራ ስለተገባ ዋጋቸው በእጥፍ አድጓል። በዚሁ ዓመት ያየነው አንድ ፕሮጀክት በ 4 ቢሊየን ብር ይሠራል ተብሎ እኛ ኦዲት ስናደርግ ወጪው 14 ቢሊየን ብር ደርሷል። ይህም ብቻ አይደለም አሁንም የዲዛይን ችግር ስላለበት 2 ቢሊየን ብር ገደማ እንደሚያስጨምር ተናግረዋል። ይህ አንግዲህ ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር የሚያያዝ ችግር ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶቹም እንዲጓተቱ ያደርጋል ። ለታለመላቸው አገልግሎትም በጊዜው አይደርሱም።

ክዋኔ ኦዲት ጋ ስንሄድ አዋጅ ወጥቶ ደንብ ሳይወጣ 10 ዓመት ይቀመጣል። በዘንድሮም ሪፖርት ላይ በቀረበው መሰረት በተለይ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ 1995 ዓ.ም. የወጣ አዋጅ እስከ አሁን የማስፈጸሚያ ደንብ አልወጣለትም። ሌላው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ያለው የቢሮክራሲው አቅም በጣም ችግር ያለበት ነው፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ገንዘብ ሚኒስቴር ለማሰልጠን ቢሞክርም ለውጥ ማምጣት አልተቻለም።

በዚህ ዓመት የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ያልተወጣውን ከዛም ደግሞ እራሱን ተቃርኖ ምላሽ የሰጠውን የብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ከዛም አልፎ ለመዋሸት የሚሞክሩ ብዙ ተቋማት አሉ።

የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ካሉበት ሁኔታ አፈጻጸማቸው ከተልዕኮ ስኬትና እየሄዱበት ካለው አካሄድ አንጻር ለእኔ በጣም አሳሳቢው የክዋኔ ኦዲት ነው። በመሆኑም ሰዎች የህዝብ አገልግሎት የህዝብ አደራ ነው ብለው ማሰብ መጀመር አለባቸው። ያንን አደራ እስከተወጡ ድረስም ብቻ እንደሆነ በቦታው ላይ የሚቆዩት ማሰብ አለባቸው። ተቆጣጣሪ አካላትም ስራቸውን አድምተው ውጤታማዎቹን ማስቀጠል የሚቀልዱትን ደግሞ ከቦታው በማንሳት ተጠያቂም በማድረግ ስራውን ለሚመጥኑ ሰዎች ማስተላለፍ አለባቸው።

አዲስ ዘመን፤እዚህ ላይ ስለ ግንባታ ወጪ ከተነሳ በተደጋጋሚ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስም አብሮ ይነሳልና በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ገመቹ፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ህግና ስርዓት ሊበጅላቸው ሲገባ ያልተበጀላቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይህንን በ2006 ዓ.ም. ጎንደር ላይ አፈጉባዔው በመሩት፣ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን ባሉበት ይህንን ችግር እንቅረፍ ተብሎ ተመን የሌላቸውም ተመን ይውጣላቸው ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ምንም ሳይሰራ አሁን በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ የመጨረሻ እልባት አገኘ። ምናልባት ይህ ጉዳይ በ2007 ዓ.ም. እልባት አገኝቶ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገሮችን ማትረፍ ይቻል ነበር።

አሁን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ሲበዛ ተለጥጠዋል፤ የሚቀበሉት ተማሪ ብዙ ነው፤ ጎን ለጎን ደግሞ የግንባታ ሥራ ያከናውናሉ፤ ያንን ተከትሎ በጣም ግዙፍ ግዢ አለ፤ ከዛ ደግሞ ማስተማርና የምርምር ሥራዎች ይጠበቅባቸዋል፤ እነዚህ ስራዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ እኔ ከዛሬ 4 ዓመት በፊት ጀምሮ መፍትሔ የምለውን ምክረ ሀሳብ ሰጥቻለሁ።

በወቅቱም ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ግንባታ ሥራ ውስጥ መግባት የለባቸውም፤ በብዙ ቢሊየን ብር የሚያወጣ ግዢንም መፈጸም የለባቸውም፤ በመሆኑም ግንባታውም በሌላ አካል ይገንባ፣ ግዢውም በተመሳሳይ ሌሎች ተቋማት ይፈጽሙ የሚል ነበር። በዛ ምክረ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ መፍትሔ ቢፈለግ ኖሮ እዚህ የከፋ ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር።

በተለይ ግዢ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ላይ ብቻ የሚታይ ችግር አይደለም፤ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ቢሆኑ የሚፈልጓቸውን እቃዎች በራሳቸው ካልገዛን ይላሉ ምክንያቱም ከዛች የምትገኝ መጠነኛ ነገር ስላለች ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት 184 ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች አሉ፤ አንድ እቃ ለመግዛት 184 መኪና ፕሮፎርማ ለመሰብሰብ ይሰማራል። ለዚህ መኪና የሚወጣው ነዳጅ የመለዋወጫ እቃ የምናባክናቸው ሰዎች ቁጥር ቢታሰብ በጣም ብዙ ነው። በመሆኑም ይህንን በአንድ ተቋም ሰብሰብ አድርጎ መጨረስ ከተቻለ ግን ይህንን ሁሉ ማትረፍ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፤ በየዓመቱ ይህንን ያህል ገንዘብ ባክኗል እየተባለ የሚቀርበው ሪፖርት ላይ የሚጠሩት ገንዘቦች ወደ ልማት ተቀይረው ቢሆን ኖሮ ይህንን ያስገኛሉ ብላችሁ ሰርታችሁ ታውቃላችሁ?

አቶ ገመቹ፤ በዚህ የኦዲት ክፍተት ምክንያት መንግሥት ምን አጣ የሚለውን በትክክል አስልቶ ማውጣት አልተቻለም ፤ ምክንያቱ ደግሞ የየዕለቱ የገበያ ዋጋ መኖር አለበት። በያዝነው ዓመት የኦዲት ሪፖርት እንኳን ፕሮጀክቶች ያለ እቅድና ዲዛይን ወደ ሥራ በመግባታቸው 44 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ወጪ አውጥተናል፤ ከዚህ ውስጥ 20 ቢሊየኑ በትክክል ባክኗል ብንል ይህ ገንዘብ ከአዲስ አበባ አዳማ የተሰራውን የፍጥነት መንገድ ሶሰት ሊሰራልን ይችል ነበር።

አዲስ ዘመን፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ለማቋቋም አዲስ አዋጅ ጸድቋል፤ ይህ ከቀድሞው በምን ይለያል? ስራችሁንስ ምን ያህል ያግዛል?

አቶ ገመቹ የሚለየው «በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ተመጣጣኝ እድገት እንቅፋት ካልሆኑ በስተቀር ድጋፍና ድጎማ ያደርጋል፤ ይህንን ድጋፍና ድጎማም ቁጥጥር ያደርጋል » ይላል። ቁጥጥር የሚያደርግበት ተቋሙ ደግሞ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ነው። ይህንን ተከትሎ ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍና ድጎማ ለክልሎች ይሰጣል የራሳቸውም ገቢ አላቸው። በተለይ የፌዴራል መንግሥቱን ድጋፍና ድጎማ ግን እንዴት ተጠቀሙበት የሚለውን ቁጥጥር ለማድረግ ለዋና ኦዲተር መሰጠት ነበረበት አዋጅ 669 /2002 ላይ ነበር፤ 982/2008 የወጣው አዋጅ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ይህ እንዲሻሻል እኛ ባንጠይቅም ከእኛ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ አንድ ሰው ጥያቄ አንስቶ ከዛም አዋጁ ተሻሽሎ ወጥቷል ።

ሌላው በዛው አዋጅ 669/2002 ላይ የነበረ የዋና ኦዲተሩ የሥራ ዘመን እንዲገደብ የሚያዝና 6 ዓመት ብሎ የተቀመጠው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተቀመረበት የነበረና እንደ አስፈላጊነቱ ለአንድ 6 ዓመት ሊራዘምለት ይችላል የሚል አስቀምጠናል አሁን 6 ዓመቱ ቀርቶ ለተጨማሪ ጊዜ ሊያገለግል ይችላል ተብሎ ቀርቧል። ይህ አዲስ አስተሳሰብና ጉልበት ወደተቋሙ እንዳይመጣ ይገድባል፤ ይህም በአዲሱ አዋጅ እንዲመለስ ሆኗል።

ኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የሚባል አለ እንዲሁ በተለምዶም ለዋና ኦዲተር ተጠሪ ነው ይባላል ግን ተጠሪ የሚያደርገው የህግ አግባብ የለም። ይህንን ክፍተት ለመሙላት ተጠሪ መሆኑን ለማመልከት አስችሏል።

አዋጁ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችንና ፕሮጀክቶችን ኦዲት ለማድረግ ትልቅ አቅም ይሆነናል ።ዋና ኦዲተር ነጻና ገለልተኛ ተብሏል። ሆኖም ዋና ኦዲተርና ምክትሉ በሥራ ላይ እያሉም ሆነ ከሥራ ሲሰናበቱ የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም እንዴት እንደሚጠበቅ በግልጽ በህግ እንዲታወቅ ሆኗል። በጠቅላላው ግን ሥራውን የበለጠ ያጠናክረዋል።

አዲስ ዘመን፤ እርስዎ በጣም ሥራ ይበዛብዎታል በእረፍት ቀናት ሳይቀር ይሠራሉ ይባላልና የቤተሰብ ሁኔታዎ ምን ይመስላል፤ ባለትዳር ነዎት? ልጆች አልዎት?

አቶ ገመቹ ትዳር አለኝ ፤ አንድ ወንድና አራት ሴቶች ልጆችም አሉኝ። በጣም ደስተኛ ቤተሰብ ነን። ነገር ግን ከቤተሰብ ይልቅ ለስራው አድልቼ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በዚህ የተነሳም ብዙ ጊዜ አልሰጣቸውም።ይህ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከመጣሁ በኋላ የሆነ አይደለም ባህሌ ነው። ወደ ሥራ አለም ከገባሁ 32 ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ። በእነዚህ የስራ ዘመኖቼም ጥሩ አለቆች ገጥመውኛል፤ የሥራ ታታሪነት አስተምረውኛል፤ ይህንን የእነሱን ባህርይ ወርሼ በዚያው ቀጥያለሁ።

በ 32 ዓመታት የሥራ ቆይታዬ 15 ቀን እረፍት ወጥቻለሁ እርሱም ትዳር ለመመስረት ነበር። ከዛ ውጪ ሥራ ላይ ነኝ። ቤተሰቦቼም ይህንን ባህሪዬን ለምደውታል። እንዳልዋሽ እዚህ መስሪያ ቤት ሳልመጣ 2 የእረፍት ቀናትን ቤተሰቦቼን ይዤ ከከተማ ውጪ ሄጃለሁ ያሳየኋቸው ይህንኑ ነው። ስለዚህ የተጣለብኝን ኃላፊነት በአግባቡ እንድወጣ የቤተሰቦቼና የሥራ ባልደረቦቼ ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም።

አዲስ ዘመን፤ እርስዎን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች አቶ ገመቹ ለመስክ ሥራ ከከተማ ሲወጡ የውሎ አበል አይቀበሉም ብለውኛልና ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ካልተቀበሉስ በምን ይጠቀማሉ?

አቶ ገመቹ፤ አበል እወስዳለሁ፤ ግን የምወስድበት አግባብ አለ፤ ለምሳሌ ከእዚህ አዳማ ለሰብሰባ ሄጄ ከሆነ ምንም አበል አያስፈልገኝም ፤ምክንያቱም እዛው መስተንግዶ ተሰጥቶኛልና። ሰዎች ለስብሰባ ይሄዱና አስፈላጊው መስተንግዶ ተደርጎላቸው አበል ይወስዳሉ። አበል አላማው እኮ ለሥራ ሲወጣ ከኪስ የተወሰደን ገንዘብ ማካካሻ ነው። በመሆኑም የሚያስፈልገኝ ከተሟላልኝ አበል መውሰድ አይገባኝም።

አዲስ ዘመን፤ ሥራው አደጋ ያለው ሆኖ ሳለ እርስዎ ግን የግል ጠባቂ የልዎትም፤ አይፈሩም ማለት ነው?

አቶ ገመቹ፤ የግል ጠባቂ መጠየቅ እችላለሁ፤ በመጀመሪያ ማንም ከምንም ሊያተርፈኝ አይችልም፤ ጠባቂዬ እግዚአብሔር ነው ብዬ ነው የማስበው። ቀኔ ከደረሰ ምንም ልሆን እችላለሁ። ለግዜው የእኔ እምነት ይህ ነው።

አዲስ ዘመን፤ የተደሰቱበት፣ የሚያዝኑበት ወይም የሚናፍቁት ነገር ምንድን ነው?

አቶ ገመቹ፤ እዚህ ከመምጣቴ በፊት የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን አላውቅም ነበር፤ ይህ ቢሮ የሚታይ የተገለጠ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን በማድረጌና በዚህ ደረጃ አገሬን ለማገልገል በመታደሌ በጣም ደስ ይለኛል። በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማውራቴ ነው። ይህ ምናልባትም አሁን በተጀመረው አካሄድ ይቀረፋል ሰውም ህግና ስርዓትን አክብሮ የተሰጠውን አደራ ተወጥቶ የማይ ይመስለኛል። ቢሆን ብዬ የምመኘው የፋይናንስ አስተዳደሩ ተጠናክሮ የመንግሥትና የህዝብ ገንዘብ ህግና ስርዓትን ተከትሎ በሥራ ላይ ውሎ፣ ተጠያቂነት ኖሮ፣ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ የሚያሳኩ ሆነው፣ በስርዓት የምንመራ አገር ሆነን ማየት ነው።

አዲስ ዘመን፤በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ገመቹ፤– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 5/2011