ላለፉት 49 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ አዋጅ በአዲስ ሊተካ ነው

አዲሱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅ . . .

ላለፉት 49 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው የሕዝብ በዓላትን እና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የወጣ አዋጅ በአዲስ ሊተካ ረቂቅ መዘጋጀቱ ሲገለፅ ፓርላማው መጋቢት ወር ላይ ወደ ሥራ ሲመለስ ይመለከታቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ አዋጆች መካከል ይህ ረቂቅ አዋጅ የሚገኝበት መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው በደርግ መንግሥት የወጣው አዋጅ 13 የሕዝብ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩ የደነገገ ሲሆን ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በዚህ አዋጅ ውስጥ የድል ቀን ላይ ብቻ ማሻሻያ በማድረግ ይሄንን አዋጅ መተግበር መቀጠሉና አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ እና በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉት ተጠቁሟል።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ያመጣቸው ለውጦች ምንድናቸው?

– አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ከቀድሞው አዋጅ የሚለየው ዋነኛ ጉዳይ የበዓላት አከባበርን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታዎችን የያዘ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ የሕዝብ በዓላትን “ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት” ፣ “ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት” እና “ሃይማኖታዊ በዓላት” ሲል ይከፋፍላቸዋል።

– ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት መደበኛ ሥራ ዝግ የሚሆንባቸው ቀናት እንደሆነ ረቂቁ ላይ የሰፈረ ሲሆን እነዚህም የዘመን መለወጫ፣ የአድዋ ድል፣ የላብአደሮች ቀን እና የአርበኞች (የድል) ቀን ናቸው።

– ሥራ ሳይዘጋ ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት 2የሰማዕታት ቀን እና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን መሆናቸው ሲገለፅ ወደ ም/ቤቱ የተላከው ረቂቅ ላይ በሃይማኖታዊ በዓልነት የተቀመጡት አምስት የክርስትና እንዲሁም ሦስት የእስልምና እምነት በዓላት ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዝርዝር ውስጥ የተደረገ ለውጥ የለም ተብሏል።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛ ነው