በኦሮሚያ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ500 ብር ጀምሮ በግዳጅ መዋጮ ተሰበሰበ

በኦሮሚያ ክልል አዋሽ ቢሾላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ለሁለት ወራት የመሠረታዊ ውትድርናና ፖለቲካዊ ሥልጠና ሲወስዱ ለነበሩ የክልሉ የመንግሥት አመራሮች አቀባበል ለማድረግ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ500 ብር ጀምሮ በግዳጅ መዋጮ እንደተሰበሰበ ዋዜማ ሠምታለች። አመራሮቹ፣ ሥልጠናውን አጠናቀው ትላንት ወደየመጡባቸው አካባቢዎች መመለሳቸውን ዋዜማ ተረድታለች። መዋጮውን ለማዋጣት ፈቃደኛ ባልኾኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ሰደረግባቸው እንደነበርም ምንጮች አስረድተዋል። ከ17 ሺሕ በላይ ሠልጣኝ አመራሮች መካከል ስድስቱ በሥልጠናው ክብደትና በአካባቢው ሞቃት የአየር ጠባይ ሳቢያ ስድስቱ ሕይወታቸው ማለፉንና 200 ያህሉ ከካምፑ መጥፋታቸውን ዋዜማ ቀደም ሲል መዘገቧ አይዘነጋም።