ፋኖ ኢላማ አድርጎናል ሲሉ የብልፅግና ሰዎች አማረሩ

በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሰዴ እና ቢቡኝ ወረዳዎች የብልጽግና ፓርቲ አባላትና የመግሥት ሹመኞች ቤተሰቦች ንብረታቸው በፋኖ ታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ እየኾነ መኾኑን ዋዜማ ከምንጮች ሠምታለች። ታጣቂዎቹ ቤት ማቃጠልን፣ ሰዎችን አፍኖ ገንዘብ መጠየቅንና የቤት እንሰሳትን መውሰድን የመሳሰሉ ድርጊቶች እንደሚፈጽሙ የሹመኞች ቤተሰቦች ተናግረዋል። የሚሊሻና የአድማ ብተና አባላት ቤተሰቦችም ለተመሳሳይ ጥቃት እንደተጋለጡ ምንጮች ገልጸዋል። በሰዴ ወረዳ የጥቃት ዒላማ የኾኑ አብዛኞቹ ሰዎች ከቀያቸው ሸሽተው ወደ ወረዳዋ ዋና ከተማ ተፈናቅለዋል ተብሏል። በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ደሞ፣ በታጣቂዎችም ኾነ በመንግሥት ሹመኞች ወገን ያሉ ቤተሰቦች የጥቃት ተጋላጭ መኾናቸው ተነግሯል።