ግብረሰዶማዊነትን ያስፋፋል የተባለው የ’ሳሞአ’ ስምምነት እንዲሰረዝ ተጠየቀ

ግብረሰዶማዊነትን ያስፋፋል የተባለው የ’ሳሞአ’ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግስት ይሰርዝ፤ ፓራላማውም እንዳያጸድቅ- የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ

 (አዲስ ማለዳ)የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዛሬ የካቲት 1 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ በአውሮፓ ሕብረት እና በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት መካከል “የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር” ተብሎ በ’ሳሞአ’ ደሴት ላይ የተፈረመውን ስምምነት አወገዘ።

ለ20 ዓመታት እንዲዘልቅ ታሳቢ ተደርጎ የተከናወነው የትብብር ስምምነት በውስጡ “ከኢትዮጵያ ህዝብ የሃይማኖትና የባህል እሴቶች ጋር የሚፃረሩ ፅንሰ ሀሳቦችና ትርጉሞች ስላለው የ’ሳሞአ’ ስምምነት ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን እንዲሰረዝ” ጎባዔው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በመግለጫው ካነሳቸው ነጥቦች መሀል “በስምምነቱ ከግብረሰዶም መብቶች፣ ከፆታ መቀየር፣ ውርጃ ህጋዊ ማድረግ ተካቷል” ብሏል።

አዲስ ማለዳ ከሣምንታት በፊት በኢትዮጵያ ‘ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ’ የተባለ የፀረ ግብረሰዶማዊነት ማህበር መስራች እና ሰብሳቢ ደረጀ ነጋሽን አነጋግራ ባዘጋጀችው ዘገባ “በማር የተለወሰ እሬት የሆነ በትውልድ ላይ ሞት የሚያውጅ ስምምነት” ነው መባሉ አይዘነጋም።

የማህበሩ መስራችም “የኢኮኖሚ ትብብሩ እንዳለ ሆኖ ይህ ሰነድ በውስጡ ከያዛቸው የድጋፍ ስምምነቶች ጀርባ ለድጋፉ ምላሽ ፈራሚ አገራቱ ‘አካታችነት’ በሚል የተጠቀሱ ነጥቦችን እንዲያሟሉ ይገፋል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባወጣው ባለ አራት ገጽ መግለጫ የ’ሳሞአ’ ስምምነትን በአንቀጽ ከፋፍሎ የተመለከተው ሲሆን “አካታችነት” በሚል የተጠቀሱ ነጥቦች በአጽንኦት ሊታዩ እንደሚገባ አሳስቧል።

ስምምነቱ የተፈረመበት ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምላሽ ሳይሰጥ የመቆየቱን ምክንያት ስትጠይቅ “የተፈረመው ስምምነት ብዙ አንቀጾች በመያዙ ጠለቅ ያለ ማጣራት እየተደረገበት በመቆየቱ” መሆኑን የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ሀጂ መስዑድ አደም ተናግረዋል።

አክለውም በማንኛውም የሀይማኖት አስተምሮት ውጭ የሆነ እና እንደ ሀይማኖታዊ ሀገር ተቀባይነት እንደሌለው አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ከጉባዔው መግለጫ አዲስ ማለዳ እንደተመለከተችው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሥሩ ያሉ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የስምምነት ሰነዱ ውስጥ በዝርዝር የቀረቡትን በተለይም ከሰብኣዊ መብቶች፣ ከወሲባዊና የተዋልዶ ጤናና መብቶች፣ ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት፣ አካታችነት እና መሰል በሰነዱ የተካተቱ አንቀጾች ወይም ይዘቶች ከግብረሰዶማዊነትና ጾታን ከመቀየር እንዲሁም ከልቅ ወሲብና ከውርጃ ጋራ በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው ጽንሰ ሃሳቦች መሆናቸውን በመረዳት ይህንን እጅግ አደገኛ ስምምነት ባለማጽደቅ ህዝባዊና ታሪካዊ አደራውን እንዲወጣ” በአጽንኦት ተጠይቋል።

የ’ሳሞአ’ ስምምነት “ከሃይማኖቶቻችን መሠረታዊ አስተምህሮ፣ ከዶግማዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ጋር የሚቃረኑና በአገራችን ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታና ደረጃ በምንም መልኩ ፍፁም ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ” አጽንት የሰጠው ጉባዔው “98 በመቶ የሚሆነውን ህዝባችንን እንደመወከላችን ይህን ቁርጠኝነታችንን የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ምዕራባውያኑ አገራት እና የአፍሪካ ኅብረት ከወዲሁ እንዲገነዘቡ በአጽንኦት” አሳስቧል።

‘ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ’ ማህበር ሰብሳቢ ደረጀ ነጋሽ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባወጣው መግለጫ ደስተኛ እንደሆኑ መግለጫው ይፋ ከሆነ በኋላ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ በጋራ ለመስራት ጥሪ ማቅረባቸው የሚገልጹት የማህበሩ ሰብሳቢ በጉዳዩ ላይ በጋራ እንደመከሩበት እና አብረው እንደሚሰሩ ለአዲስ ማላዳ ተናግረዋል።

ደረጀ ነጋሽ “የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሁሉንም ሃይማኖቶች የሚወክል በመሆኑ ከ80 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነው፤ ስለሆነም ተፈጻሚነት እንዳይኖረው አሁንም ትግላችንን እንቀጥላለን” በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።