የኢሳና አፋር ደም አፋሳሹ ግጭት መቼ ነው የሚያበቃው? እንዴስ ያበቃል? – አካደር ኢብራሂም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

ከአካደር ኢብራሂም

በኢትዮጵያ ውስጥ ዝነኛ የሆነ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ማለቂያ የለለውና መፍትሄ ያልተግኝለት ጦርነት። በተለምዶ በግጦሽና በሳር የሚፈጠር የአርብቶ አደሮች ግጭት በመባል ይታወቃል።

ጉዳዩ ግን ሰፋ ያለ ሌላ ትኩረት የሚስብ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያነገበ ስለመሆኑ ብዙ የተባለ ቢሆንም የተገኘ መፍትሄ ግን የለም። ችግሩ የሚመለከተው አካል መፍትሄ አለመስጠቱ ብቻ አይደለም። ዋናው ችግሩ መንግስታት የሁለቱ ወገኖች ግጭትን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀማቸው ነው። በዚህ ጉዳይ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ምሁራን ብዙ ጥናቶች አድርገዋል። በጣም ብዙ ጊዜ ደግሞ በሃይማኖት አባቶችና በባህላዊ ሽምግልና ዕርቅ ተሞክሯል። ችግሩ ግን ሊቆም አልቻለም። ለምን ይሆን?

የታሪክ ደርሳናት እንደሚናገሩትና ኢሳዎችም ጭምር የማይክዱት አንድ ሀቅ አለ። የኢሳ ሶማሌ ጎሳ ከዘላዓ ወዲህ የሚታወቁበት መሬት እንዳልነበራቸውና በተለያዩ ጊዜያቶች በተደረጉ ጦርነቶች ግዛታቸውን እያስፋፉ እንደመጡ ይነገራል።

ብዙ ሰዎች በተለይ አሁን አሁን ከማንነትና ከመሬት ይገባኛል ጋር የሚያያዙ ግጭቶች ከፌደራሊዝም ጋር ያያዙታል። የኢሳና አፋር ግጭት ግን በጣም የቆየና ቁርጠኛ የሆነ ገለልተኛ ውሳኔ የሚፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ከንጉሠ ነገስት ሃይለስላሤ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ በኢሳና በአፋር መሃል የተደረጉ ስምምነቶችን ጥሶ የሚገኘው የኢሳ-ሶማሌ ጎሳ እንደሆነ ማስረጃዎች ያሳዩሉ።

የኢሳ (ሶማሌ) ድንበር ከአፍደም ወደ አሁኑ የሶማሌ ክልል 147 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደነበረ በ1962 ዓ.ም በኤረር ላይ በአፋርና ኢሳ መካከል በተደረገ ስምምነት ተገልጿል። ነገር ግን በአሁኑ ግዜ ኢሳዎች አፋርን እያጠቁ ያሉት ከኤረር 300 ኪ.ሜ. ወደ ውስጥ ገብቶ የአዋሽ ወንዝ ዳርቻ አዳይቱ፣ ኡንዳፎኦ እና ገዳማይቱ በተባሉ የአፋር ግዛት ውስጥ ነው።

እ.አ.አ ጀንዋሪ 22/ 2012 በእንግሊዝ ሀገር በተደረገው የኢሳ ዲያስፖራዎች ሰብሰባ ላይ ከኢሳ ማህበረሰብ በጣም ተዋቂ ከሚባሉ ሰዎች አንዱ የሆኑትና ቀደም ብሎም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የነበሩት አቶ ሁሴን ቡሕ የተባሉ ሰው በግልጽ ለኢሳዎች የተናገሩት ይኸው ነበረ።

በዛ ሰብሰባ ላይ እኛ ኢሳዎችኮ መሬት የለንም፣ ዘላዓ ከተባለ አከባቢ ውጭ ምንም አልነበረንም። በኋላ ግን የራሳችን የምንለው መሬት ለማግኘት ታግለን የአፋርን መሬት ወስደናል ይላል በቪዲዮ የተቀዳው የአቶ ሁሴን ንግግሩ።

ከንጉሱ ጊዜ እስከ ደርግ ጊዜ በተደረጉ የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ግጭቱ የግጦሽ ክልል የይገባኛል ግጭት እንደነበረ ቢገለጽም ባለፉት 28 አመታት ግን ግጭቱን የበለጠ ለፖለቲካ ፍጆታ የተጠቀሙበት ጊዜ ነበረ ማለት ይቻላል።

የኤርትራ ባሕር በር ከተዘጋ በኋላ ኢትዮጵያ እንደ አማራጭ የወሰደችውና እስከ ዛሬ የምትጠቀመው የጀቡቲ ወደብ በመሆኑ የህወሓትና የኢሳዎች የጠበቀ ግኑኝነት እንዲኖሯቸው ካደረጉ አጋጣሚዎች አንዱ ነው ተብሎ ይታመናል።

ከዚህ ባሻገር የድሬ ዳዋ ተወላጅ የሆኑት የጀቡቲው ፕሬዚደንትና ህወሓቶችን አንድ የሚያደርጋቸው ሁለቱም በቁጥር ከእነሱ የሚበዙ ብሄሮችን በመጨቆን፣ ያለ ርህራሄ መጨፍጨፍና ማሳቃየት ያመሳስላቸዋል።

በፕሬዝዲንትነት ከሚመሯት ጀቡቲ በላይ በኢትዮጲያ የሚኖሩ ጉሳዎቻቸው የሚያሳስቧቸው አቶ እስማኢል ኡመር ጉለህ ባለፉት 30 አመታት የዚህ ግጭት ዋና ተጠያቂ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት ጀኔራሎችና የኢሳ ታጣቂዎች በጋዳማይቱ እና ኡንዳፎዖ ከተሞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የኮንትሮባንድ ንግድ በትብብር ሲሰሩ እንደነበሩ ሚስጥር አይደለም። በተለይ በእነዚህ 28 አመታት በዚህ አካባቢ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስና የአፋር ክልል የህወሓት ተሾሚዎች ግጭቱን ከማስቆም ይልቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረጋቸው ችግሩን አባብሶታል።

በአፋር ክልል ከብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። በእርግጥ ሀገራቸው ስለሆነ መኖርም አለባቸው። እስካሁን በማንነታቸው ምክንያት የእናንተ ክልል አይደለም ተብለው የተፈናቀሉ የሉም። የኢሳ ጉዳይ ግን ኢትዮጵያዊነትና አብሮ ተቻችሎ መኖር ሳይሆን እየገደሉ መሬት መያዝና በደረሱበት ሁሉ የሶማሌ ክልል ባንዲራ እየሰቀሉ መቀጠል ነው። ይህንን ወረራ ግን ማስቆም የነበረበት ሀገርን የሚያስተዳድረው መንግስት ቢሆንም መንግስት ግን በዝምታ መመልከቱን ቀጥሏል።

በአቶ አባይ ጸሃዬ ሓሳብ አቅራቢነትና በኋላም በፌዴራል ጉዳዮች ሚንስቴር ውሳኔ ሰጭነት እ.አ.አ 2014 አዋሽ ላይ የተወሰነው ውሳኔ ችግሩን የሚያባብስ እንጂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል የአፋር ሽማግሌዎች በአዋሽ ሰብሰባ ረግጠው ከወጡበት ከዚሁ ቀን ጀምሮ በአፋር በኩል በጽኑ ሲነገር ቆይቷል።

ኢሳ-ሶማሌዎች በውጭ መንግስታት ሳይቀር እየታገዙ በጦርነት በያዙዋቸው ቦታዎች ላይ እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በሶማሌና አፋር ክልል መሪዎች እንዲሁም በፌዴራል ተወካዮች ተወስኖ ነበረ። ይህ ህገ-መንግስትን መሰረት ያላደረገ ውሳኔ በአፋር ህዝብ ዘንድ ምንም አይነት ተቀባነት እንዳለገኘ በግልጽ ይታወቃል። ከክልል መሪዎች ተብዮቹ አሻንጉልቶች ውጪ ይህንን ውሳኔ የተቀበለ አልነበረም። ኢሳዎች በዚህ ሁኔታ በተጠቀሱት ከተሞች ከእነሱ ውጭ ማንም እንዳይኖር ነው የሚፈልጉት። አንድ ከተማ እንኳን ለእነሱ ለአፋሮችም ቢሆን በአፋር ክልል የብቻዬ የማለት መብት የሚሰጥ ህግ አለ እንዴ?

የአሁኑ ግጭት ደግሞ በሚገርም መልኩ ከአፋር ክልል የህወሓት አደራ ጠባቂዎች ሲባሉ የነበሩ ሰዎች ከስልጣናቸው በተሰናበቱ ማግስት ትምህርት ቤቶች ላይ የአፋር ክልል ባንዲራን በማውረድ የሶማሌ ክልልን ባንዲራ በመስቀል ተጀምሯል። ያወረዱትን ባንዲራ እያቀጠሉ በኢንተርኔት ላይ ለቀዋል።

የሄ ሁሉ እየተደረገ በአከባቢው ያለው መከላከያ ሰራዊትም ሆነ ፌደራል ፖሊስ በዝምታ ይመለከተው ነበር። በአፋር በኩል ህዝቡ በራሱ እርምጃ ከሚወስድ ህግ እንዲያስከብር መንግስት ላይ ግፊት ማድረጉን መርጠ። በዚህ መልኩ የአፋር ክልል ልዩ ሃይል ፖሊሶች ወደ አከባቢው በመሄድ ባንዲራን ሲመልሱ በኢሳ ሶማሌዎች ትኩስ ተከፈተባቸው።

ለሶስት ቀናት በዚህ ሁኔታ በጋዋኔ፣ በኡንዳፎዖና ጋዳማይቱ ብዙ ሰዎች የሞቱበት ጦርነት ተደረገ። የመከላኪያ ሰራዊት ይህን ሁሉ እያየ ጣልቃ ሳይገባ እየተመለከት ነበረ።

ጉዳዩ የፖለቲካ እጅ አለበት የሚያስብለን ለምን አሁን? ከሚለው ጥያቄ በመነሳት ነው። ነባር መሪዎች በተሰናበቱ ማግስት ይህ መሆኑ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ብለን ማመን ይከብዳል። መከላከያው በቦታው እያለ ዝምታን የመረጠው ለምንድነው?

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በህወሓት አክቲቪስቶች ፌስቡክ ላይ በኢሳና አፋር መሃል ከፍተኛ ግጭት ይነሳል በማለት ሲለቀቁ የነበሩ መልዕክቶች ተራ ትንቢት ነበሩ ብለን ማለፍ አንችልም።

በኋላ ደግሞ የመከላከያ አዛዥ የነበረው አንድ ጀኔራል በመቀየሩ ግጭቱ ወዲያው በኢሳዎች በኩል የቆመውስ አጋጣሚ ነው ብዬ አላምንም። (ምንም እንኳ መሉ በመሉ ባይቆምም ማለት ነው)። ችግሩ ፍትሃዊ የሆነ ህጋዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል።

መፍትሄው ደግሞ ጦርነት በተነሳ ቁጥር ማርገብ ወይም ማራገብ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ከተፈለገ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች የአስተዳደር ወሰን ታሪክን መሰረት በማድረግ በፍጥነት ማካለል ነው።

መከላከያ ሰራዊት በፈለገበት ሰዓት ጦርነት የሚቀሰቅስ፣ በለፈገበት ሰዓት ደግሞ የሚያስቆምበት አካሄድ ሳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ ካልተደረገ በአከባቢው ሌላ ችግር ሊከሰት ይችላል። አከባቢው በኤርትራም ሆነ በጀቡቲ የኢትዮጲያ ጎሮሮ እንደመሆኑ መጠን ሰላም ሳይደፈርስ መንግስት ትኩረት መስጠት አለበት።

አሁን በአፋር በኩል ያለው ብቸኛው ጥያቄ ኢሳ-ሶማሌዎች እንደ ማንም ኢትዮጵያዊ በሰላም መኖር ካልፈልጉ ወደሚፈልጉት ሶማሌ ክልል ከመሬታችን ተንስተው ይሄዱ የሚል ነው።

መንግስት ፍቅርና መደመር ለማይገባቸው ሌላ መንግድ ካላበጀ ወደ መተራመስ እየሄደን መሆኑ ልብ እንበል።