በጋዜጠኛና የታሪክ ምሁሩ አቶ ታዲዎስ ታንቱ የክስ ሂደት ላይ ሲካሄድ የነበረው ምስክር የመስማት ሂደት ተቋረጠ

በጋዜጠኛና የታሪክ ምሁሩ አቶ ታዲዎስ ታንቱ የክስ ሂደት ላይ ሲካሄድ የነበረው ምስክር የመስማት ሂደት ተቋረጠ!

👉ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ጀነራል አበባው ታደሰ ፍርድ ቤት አንቀርብሞ ብለዋል

በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ “የሰነድ ማስረጃዎች ከቀረበው ክስ ጋር ግንኙነት የላቸውም እንዲሁም እንዲመሰክሩ የተጠሩት ምስክሮች ተከላከሉ ከተባሉበት አግባብ አንፃር ትክክለኛና ቀጥተኛ የሆኑ ስላልሆኑ ሊሰሙ አይገባም” ሲል በፅሁፍ አቤቱታ ማስገባቱን ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ ለሮሃ ቲቪ ተናግረዋል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ጉዳያቸው እየታየ ያለው አቶ ታዲዮስ ታንቱ በአራት ክሶች መከሰሳቸውን ይታወቃል። ክሶቹም መከላከያ ሰራዊትን በተመለከተ፤ ከታሪክ አንጻር የተናገሯቸው ንግግሮች ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ አድርገዋል የሚልና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተሳድበዋል የሚሉት ናቸው።

በእነዚህ በቀረበቡባቸው ክሶች ዙሪያ እየተከራከሩ የሚገኙት አቶ ታዲዎስ ታንቱ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ በጠየቁት መሰረት በጠበቆቻቸው በኩል የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። በዚህም ጋዜጠኛ መስከረም አበራ ፣ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ምስክርነታቸውን ከሰጡ መካከል ናቸው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ጀነራል አበባው ታደሰ ደግሞ ለመቅረብ ፍቃደኛ ያልሆኑ መሆናቸው ታውቋል።

በዚህም የሰነድ ማስረጃዎችና ቀሪ የመከላከያ ምስክሮች ከዛሬ ከግንቦት 14 እስከ 16 እንዲቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቶ ነበር። ነገር ግን ዛሬ ግንቦት 14/2015 በዋለው ችሎት አቶ ታዲዎስ ሲያሰሙት የነበረው መከላከያ ምስክር የማሰማት ሂደት ተቋርጧል። በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ “የሰነድ ማስረጃዎች ከቀረበው ክስ ጋር ግንኙነት የላቸውም እንዲሁም እንዲመሰክሩ የተጠሩት ምስክሮች ተከላከሉ ከተባሉበት አግባብ አንፃር ትክክለኛና ቀጥተኛ የሆኑ ስላልሆኑ ሊሰሙ አይገባም” ሲል በፅሁፍ አቤቱታ ማስገባቱን ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ ለሮሃ ቲቪ ተናግረዋል። ስለሆነም ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ በአቃቤ ህግ አቤቱታ ላይ አስተያየት ለመስጠት ለረቡእ መቀጠሩን ነግረውናል።

መረጃው የሮሃ ሚዲያ ነው።