ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የልዑል አለማየሁን አጽም ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ

  • ቢቢሲ ኒውስባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በዊንድሶር ካስል ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበረውን የኢትዮጵያዊ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን አጽም እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበል ገለፀ።

ልዑል አለማየሁ ቤተሰብ፣ የልዑሉ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ እና መንግሥት የልዑሉ አጽም ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አጥብቀው ቢጠይቁም፣ የእንግሊዝ ንጉሥውያን መልስ ግን “ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አይቻለንም” የሚል ሆኗል።

የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ልዑል አለማየሁ ተቀብሮ ባለበት ስፍራ “አርፈው የሚገኙት ሳይረበሹ አጽሙን ማውጣት የሚቻል አይደለም፤ ስለዚህ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት እንደማንችል እናሳውቃለን” ሲል ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።

ልዑል አለማየሁ እግሩ የእንግሊዝ ምድርን ሲረግጥ ገና የሰባት ዓመት ታዳጊ የነበረ ሲሆን፣ እናቱ በጉዞ ላይ መሞታቸውን ተከትሎ ወላጅ አልባ ሆኖ ነበር።

በጎንደር ያሉት የልዑሉ ቤተሰቦች ግን አጭር ዕድሜውን በሰው አገር በብቸኝነት አሳልፎ በሐዘን ሕይወቱ ያለፈው ልዑል፣ ከእንግሊዝ ነገሥታት ጎን መቀበሩ ብቻ “ለነፍሱ እረፍት አይሰጥም” ይላሉ።

በጎንደር የሚገኙ የአጼ ቴዎድሮስ ሦስተኛ እና አራተኛ ትውልድ ቤተሰብም ልዑሉ “የዘላለም እረፍት” ያገኝ ዘንድ አጽሙ ወደ ትውልድ አገሩ መመለስ አለበት ሲሉ ለባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ይፋዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር።

የአጼ ቴዎድሮስ አራተኛ ትውልድ ቤተሰብ የሆነው ፋሲል ሚናስ፣ ልዑሉ ማረፍ ያለበት በባዕድ አገር ሳይሆን በአባቱ አገር ጎንደር ነው ይላል።

“በዊንዘር መቀበሩ መልካም አስበው እንደሆነ እረዳለሁ፣ ከእንግሊዛውያን ነገሥታት ጎን መቀበሩም እኔን አይደንቀኝም። ምክንያቱም እርሱም ልዑል ነበር” ይላል።

ወደ ብሪታንያ ከተወሰደ በኋላ እኤአ በ1879 በ18 ዓመቱ በመተንፈሻ አካላት ሕመም የሞተው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ከንጉሣውያን ቤተሰቦች የገንዘብ እገዛ ይደረግለት ነበር።

የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ የልዑሉን አጽም ሌሎች በስፍራው አጽማቸው ያረፉትን ሳይረብሹ ለማውጣት አዳጋች መሆኑን ገልፀዋል።

“አጽሙን ሌሎች በስፍራው ያረፉ በርካቶችን ሳይረብሹ ማውጣት እጅግ በጣም አዳጋች ነው።”

አክለውም በቤተክርስቲያኒቱ የሚገኙ አስተዳዳሪዎች የልዑል አለማየሁ ትውስታዎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ጠቅሰው፣ “እንዲሁም ደግሞ የሟችን ክብርም የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።

ቤተ መንግሥቱ ከዚህ ቀደም “ኢትዮጵያውያን ልዑካን ስፍራውን ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ” ማስተናገዱንም አስታውሰዋል።

ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ጋር

ከደብረታቦር እስከ ዊንዘር

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በጎንደር የተወለደን የንጉሥ ልጅ መጨረሻ ርቆ ባለ ባሕር ማዶ በሚገኝ የባዕድ አገር ማለም ከባድ ነው።

የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ዕጣ ፈንታ ግን የሆነው ያ ነው።

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ተወዳጅ ልጅ የነበረው ልዑል አለማየሁ፣ ትውልድ እና ዕድገቱ በሰሜን ኢትዮጵያዋ ደብረ ታቦር ነበር።

ልዑል አለማየሁ የአጼ ቴዎድሮስ ብቸኛ ልጅ ባይሆንም፤ ከእቴጌ ጥሩወርቅ የሚወለደው ብርቅዬው እና በመቅደላ አብሯቸው ይኖር የነበረ ልጃቸው ነው።

በዘመነ መሳፍንት በጎበዝ አለቃ ትመራ የነበረችን የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ብዙ የደከሙት አጼው፤ እኤአ በ1862፣ የጦር ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለንግሥት ቪክቶሪያ የጻፉት ደብዳቤ ምላሽ ባለማግኘቱ የእንግሊዝ መንግሥት ተወካዮችን ማሰራቸው የልዑል አለማየሁን ብቻ ሳይሆን የአጼውን እና የኢትዮጵያን ታሪክ በእጅጉ የቀየረ ሆነ።

በአጼ ቴዎድሮስ የተያዙ እስረኞችን ለማስለቀቅ የእንግሊዝ መንግሥት በሰር ሮበርት ናፒዬር የተመራ 13 ሺህ ያህል ጦር ወደ ቀድሞዋ ኢቢሲኒያ ላከ።

አንትሮፖሎጂስት እና የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት፤ “አጼ ቴዎድሮስ ከብሪታኒያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይሹ ነበር። …ለንግሥቲቱ የጻፉት ደብዳቤ ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር ሚሽነሪዎችን አግተው ያዙ። ብሪታኒያ ከሕንድ ጭምር ወታደሮቿን ወደ መቅደላ አዘመተች” ይላሉ።

በዚህ ጦርነት ላይ ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ የብሪታንያ ሙዚየም ሰዎችም ተካትተውበት ነበር።

እአአ 1868 በተደረገው ጦርነት የእንግሊዝ ጦር ድል አደረገ። አጼ ቴዎድሮስ እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸውን አጠፉ።

በምናብ የተሳለ የመቅደላ አምባ
የምስሉ መግለጫ, በመቅደላው ጦርነት በምናብ የተሳለ የመቅደላ አምባ

ሕይወት በባዕድ አገር

ከመቅደላ ጦርነት በኋላ እንግሊዛውያኑ ቅርስ ዘረፉ። ቁስ ብቻ አልበቃቸውም። የንጉሡን ልጅ ልዑል አለማየሁን እና እናቱን እቴጌ ጥሩወርቅን ይዘው ወደ ብሪታኒያ ጉዞ ጀመሩ።

በጉዞ ላይ ሳሉ ግን እቴጌ ጥሩወርቅ ሕመም ጠንቶባቸው ከመንገድ ቀሩ፤ ሕይወታቸው አለፈ።

የልዑል አለማየሁ የወላጅ አልባነት፤ የሐዘን ሕይወት የሚጀምረው ከዚህ ነው። ልዑል አለማየሁ እግሩ የእንግሊዝ ምድርን ሲረግጥ ገና የሰባት ዓመት ታዳጊ ነበር።

ያለ ፍላጎቱ እንደ ጦር ምርኮኛ የተወሰደው ልዑሉ፣ እንግሊዝ ሲደርስ እንደ ንጉሥ ልጅ እውቅና እንደተሰጠው እና ከወቅቱ የብሪታኒያ ንግሥት ቪክቶሪያ ፊት ከቀረበ በኋላ የንግሥቲቱን ቀልብ መግዛት ችሎ እንደነበረ አሉላ ፓንክረስት ይናገራሉ።

ንግሥቲቱ አሳዳጊ ተንከባካቢ እንዲቀጠርለት፤ የትምህርት እና የቀለብ ወጪ ተቆራጭ እንዲደረግለት ወሰኑ።

ልዑሉ ከመቅደላ ይዘውት ከአገር ከወጡት ካፒቴን ስፒዲ ከተባሉ የጦር መኮንን ጋር አብሮ መኖር ጀመረ። ከአሳዳጊው ካፒቴን ስፒዲ ጋርም ጥሩ ግንኙነት ፈጥሮ ነበር። አለማየሁ ከካፒቴኑ ጋር ወደ ሕንድ እና ወደ ቀድሞዋ ብሪቲሽ ማላያ ድረስ ተጉዟል።

ገና በትንሽ ዕድሜው እንደ ስሙ ዓለምን ያየው አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ እንዲለይ መደረጉ እና አዳሪ ትምህር ቤት መግባቱ ከባድ ሆኖበት ነበር ይላሉ አሉላ ፓንክረስት።

ልዑል አለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አለማየሁ

አንድሪው ሄቨንስ የተባለ ፀሐፊ በቅርቡ ባሳተመው “ዘ ፕሪንስ ኤንድ ዘ ፕላንደር” በተሰኘ መጽሐፉ፣ እንግሊዛውያን ልዑሉን እና እናቱን የወሰዷቸው በመቅደላ ዙሪያ የነበሩ የአጼ ቴዎድሮስ ጠላቶች ይዘው ይገድሏቸዋል ብለው በመስጋታቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ ነው ይላል።

ሄቨንስ በዚሁ መጽሐፉ ልዑል አለማየሁ ብሪታንያ ከደረሰ በኋላ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ ውጪ ወጥቶ መጫወትን ይመርጥ እንደነበር፣ ለፈረስ እና ለፈረስ ግልቢያ ልዩ ፍቅር እንደነበረው አስፍሯል።

አለማየሁ ቁርስ ለመመገብ ሲቀርብ “Me ride today” ? [ዛሬ ፈረስ እጋልባሁ?] የሚለው የዘወትር ጥያቄው ነበር።

ከእኩዮቹ ጋር ‘ብላይንድ ማንስ በፍ’ የተባለ ጨዋታን መጫወት ያዝወትር ነበር። ይህ ጨዋታ እንደ አባሮሽ ነው።

የጨዋታው ሕግ ዐይኑን የታሰረ ተጫዋች በዙሪያው የሚሯሯጡ ልጆችን መያዝ ነው። ዓሳ ማጥመድም አለማየሁን በልጅነቱ የሚያስደስተው ተግባር ነበር።

የአለማየሁ አሳዳጊ የነበረው ካፒቴን ስፒዲ የልጁን እድገት በተመለከተ በየጊዜው ሪፖርት ያቀርብ ነበር። አለማየሁ በጥሩ ጤንነት እንደሚገኝ፣ ንቁ አእምሮ እንዳለው እና የእንግሊዝኛ ቋንቋን በፍጥነት እየተማረ እንደሆነ ጽፎ ነበር።

ሄቨንስ በመጽሐፉ አለማየሁ በአንድ ወቅት ለጓደኛው የጻፈው ደብዳቤ በአካባቢው የሚታተሙ ጋዜጦች ይዘውት ወጥተው እንደነበረ አመልክቷል።

ልዑል አለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አለማየሁ

ሕልፈተ ሕይወት

ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ደስተኛ ያልሆነ ሕይወት ማሳለፉን ከታሪክ ማኅደሮች መገንዘብ ይቻላል።

ልዑሉ ከአሳዳጊው ካፒቴን ስፒዲ ከተለየ በኋላ፤ በሐዘን እና በጥርጣሬ ነበር ሕይወቱን የገፋው።

ልዑል አለማየሁ ጤናው ተቃውሶ ለሕልፈቱ በተቃረበበት ወቅት ‘ተመርዣለሁ’ ብሎ በማሰቡ ምክንያት ምግብ እና መጠጥ ለመውሰድ ፍላጎት አልነበረውም።

ሄቨንስ በመጽሐፉ ለልዑል አለማየሁ ክትትል ሲያደርጉ ከነበሩት መካከል አንዱ፤ “ተመርዣሁ ብሎ ስለፈራ ምግብን እና መጠጥ እምቢኝ ብሏል” ሲሉ ለንግሥት ቪክቶሪያ የቴሌግራም መልዕክት ልከው እንደነበረ ጽፏል።

ልዑል አለማየሁ ወደ ባዕድ አገር ከተወሰደ ከ10 ዓመታት ገደማ በኋላ በ18 ዓመቱ ከመተንፈሻ አካሉ ጋር በተያያዘ ሕመም እአአ ኖቬምበር 14/1879 ሕይወቱ አለፈ።

ለአለማየሁ “ርህራሄ” የነበራቸው ንግሥት ቪክቶሪያም በልዑሉ ሕልፈት ሐዘን ገብቷቸው ነበር። ንግሥቲቱ በግል ማስታወሻቸው ላይ የልዑሉን ሞት ከሰሙ በኋላ እንደሚከተው አስፍረው ነበር፤

“ዛሬ ጠዋት መልካም የሆነው አለማየሁ ሕይወቱ ማለፉን ስሰማ ከባድ ሐዘን እና ድንጋጤ ተሰምቶኛል። በባዕድ አገር ብቻውን፤ አንድም ዘመድ ይሁን የቅርብ ሰው ሳያይ…ደስተኛ ሕይወት አልነበረውም። ሁሉም አይነት ፈተና ተጋርጦበት ነበር…ሰዎች ትክ ብለው ሲመለከቱት በቆዳ ቀለሙ ይመስለው ነበር። …ሁሉም በጣም አዝኗል።”

“ንግሥቲቱ ለእርሱ ርህራሄ ነበራቸው። ከሞተ በኋላ ቁንዳለውን ጠይቀው ነበር። ንጉሣውያኑ ለፀጉር ትልቅ ትርጉም ይሰጣሉ። ንግሥቲቱ በሞት ያጡትን የባለቤታቸው ፀጉር ነበራቸው” የሚሉት አሉላ፤ ልዑል አለማየሁ በቤተመንግሥት እንዲቀበር የተደረገው በንግሥቲቱ ትዕዛዝ መሆኑን ይናገራሉ።

መቅደላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“አጽሙ ቢመለስ እርሱ ራሱ በሕይወት እንደተመለስ ነው የምቆጥረው”

ልዑል አለማየሁ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ እንግሊዛውያን ነገሥታት ከሚቀበሩበት የዊንዘር ቤተ መንግሥት የቀብር ስፍራ እንዲያርፍ ተደርጎ ይገኛል።

በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ እና አባታቸው ንጉሥ ጆርጅ ስደስተኛን ጨምሮ በርካታ የእንግሊዝ ነገሥታት በዊንዘር ቤተ መንግሥት ተቀብረው ይገኛሉ።

ኢትዮጵያውያን ግን የልዑሉ አጽም ወደ አገሩ አንዲመለስ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

እኤአ በ2007 የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለንግሥት ኤልዛቤጥ ይፋዊ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም።

በጎንደር ያሉት የልዑሉ ቤተሰቦች ግን አጭር እድሜውን በሰው አገር በብቸኝነት አሳልፎ በሐዘን ሕይወቱ ያለፈው ልዑል፣ ከእንግሊዝ ነገሥታት ጎን መቀበሩ ብቻ “ለነፍሱ እረፍት አይሰጥም” ይላሉ።

ልዑል አለማየሁ በዊንዘር ቤተ መንግሥት ከተቀረበ 143 ዓመታት ቢያልፉም፤ አጽሙ ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ እንዲያርፍ ለንጉሥውያን ቤተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።

በጎንደር የሚገኙ የአጼ ቴድሮስ ሦስተኛ እና አራተኛ ትውልድ ቤተሰብም ልዑሉ “የዘላለም እረፍት” ያገኝ ዘንድ አጽሙ ወደ ትውልድ አገሩ መመለስ አለበት ሲሉ ለባኪንግሃም ፓላስ ይፋዊ ጥያቄ አቅርበዋል።

መኖሪያቸውን ከጎንደር በቅርብ ርቀት በምትገኘው እንፍራንዝ ከተማ ያደረጉት የአጼ ቴድሮስ የሦስተኛ ትውልድ ቤተሰብ የሆኑት ወ/ሮ አበበች ካሳ ልዑል አለማየሁ “እንደ ከፋው ሞቶ፤ እንደ ከፈው እዚያው መቅረት የለበትም” ይላሉ።

“አጼ ቴዎድሮስ፤ መሸሻ ቴዎድሮስን ወለዱ። መሸሻ ደግሞ ደጃዝማች ካሳን ወለዱ። እኔ አበበች ካሳ የደጃዝማች ካሳ ልጅ ነኝ” በማለት ከልዑሉ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚያስረዱት ወ/ሮ አበበች፤ “አለማየሁ ሥጋችን ነው። አጽሙ እንዲመለስ እንፈልጋለን። በባዕድ አገር እንዲቀር አንፈልግም። አይደለም እርሱን የተዘረፉ ዕቃዎች እንዲመለሱ እየተጠየቁ እኮ ነው” ይላሉ።

አጤ ቴዎድሮስ በአንበሶች ተከብበው የሚያሳይ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአጼ ቴድሮስ አራተኛ ትውልድ ቤተሰብ የሆነው ወጣቱ ፋሲል ሚናስም በተመሳሳይ ልዑል አለማየሁ መቀበር ያለበት እትብቱ በተቀበረበት ነው ይላል። ፋሲል “ልዑሉ የኖረው አጭር ሕይወት በሐዘን የተሞላ መሆኑ ለሕልፈቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል” ይላል።

“እናቱን እና አባቱን አጥቶ በጠላት እጅ በባዕድ አገር መኖር ያውም በጨቅላ ዕድሜ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በጣም ብቸኛ ነበር። የብቸኝነት ስሜት ከባድ ነው።”

ፋሲል የአባቱ ቁንዳላ በቅርቡ በተመለሰበት ወቅት ከፍተኛ ደስታ ቤtሰቡ እንደተሰው አስታውሶ፤ የልዑል አለማየሁ አጽሙ ቢመለስ ደግሞ “ደስታችን ወደር አይኖረውም” ብሏል።

ወ/ሮ አበበች የልዑሉ አጽም እንዲመለስ ለንጉሥ ቻርለስ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ “ተንከባክባችሁታል እናመሰግናለን። ግን ደስተኛ አልነበረም። ከአገሩ በጣም ርቆ ነው የተቀበረው። ነፍሱ አታርፍም። ቢያንስ ነፍሱ እንድታርፍ ፍቀዱለት” በማለት ከአዲሱ ንጉሥ ቻርልስ አዎንታዊ መልስ እንደሚያገኙ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የልዑሉን አጽም ለማስመለስ ለረዥም ዓመታት ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም እስካሁን ፍሬ አለማፍራታቸውን የሚናገሩት ደግሞ በዩናትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ በየነ ገ/መስቀል ናቸው።

“ጥያቄ ማቅረብ ከጀመርን ረዥም ጊዜ ሆኖናል። መሪዎች ተቀያይረዋል። እስካሁን ግን እንሰጣለን የሚል መልስ የለም” ይላሉ።

እንግሊዛውያኑ የመቅደላ ቅርሶችን ለመመለስ ፍላጎት ቢያሳዩም የልዑልን አጽም ለመመለስ ግን ፍላጎት አለማሳየታቸውን አቶ በየነ ገ/መስቀል ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የልዑሉን አጽም ለማስመለስ የሚያደርገውን ጥረት እንደማያቆም በኤምባሲው ምክትል ሚሲዮን መሪው ይናገራሉ።

“ከመቅደላ የተወሰዱ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት እያደረግን እንዳለነው ሁሉ ይህንም ለማስመለስ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።”

ለአሁኑ ግን ልዑል አለማየሁ በቀዝቃዛው የአውሮፓ ምድር፤ ከአገሩ ርቆ እና ‘ነፍሱ ሳትርፍ’ በባዕድ አገር መቆየቱ የሚቀር አይመስልም።

ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ጋር

ልዑል አለማየሁ በለጋነቱ ሞት ባይቀድመው ኖሮ ምን አይነት ሕይወት ይኖረው ነበር?

እንደ አለመታደል ሆኖ ልዑሉ ገና በለጋ ዕድሜው ሞት ቀደመው እንጂ በሕይወት ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ምን አይነት ሕይወት ያሳልፍ ነበር? በጎንደር ያሉ ቤተሰቦች ዘወትር እራሳቸውን የሚጠይቁት ጥያቄ ነው።

በዚህም ምክንያት ልዑሉ በለጋ እድሜው ባያልፍ ምን ሊሆን ይችል ነበር ብለው ሲያስቡ ይበከነከናሉ።

“አለማየሁ የአጼ ቴዎድሮስ ‘ተመራጭ’ ልጅ እንደሆነ ስንሰማ ነው ያደግነው። ልክ እንደተቀሩት የአጼ ቴዎድሮስ ልጆቹ ሁሉ አገሩን እያገለገለ የተሻለ ሕይወት ይኖረው ነበር። የእርሱ ወንድሞች እና የወንድሞቹ የልጅ ልጆች አገር እየገዙ ቆይተዋል። አባቴም አገር አስተዳዳሪ ነበሩ። አለማየሁ አግብቶ ወልዶ ከብዶ ሊኖር ይችል ነበር” የሚሉት ወ/ሮ አበበች ናቸው።

አሉላ ፓንክረስት ደግሞ የአለማየሁ ዕጣ ሞት ባይሆን ኖሮ ሐኪም ወርቅነህ ወደ አገር ቤት ተመልሰው አገራቸውን እንዳገለገሉት ሁሉ፣ ልዑል አለማየሁም ወደ አገሩ ቢመለስ ኖሮ አሁን የሚነገረው ታሪክ ምን ሊሆን ይችል እንደነበር እርግጠኛ አይደሉም።

ባህሩ ዘውዴ፤ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው ልዑል አለማየሁ በተወሰደበት ተመሳሳይ ወቅት ከአገር የወጡት ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ከሦስት አርሥት ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው የአጼ ሚኒሊክ የግል ሃኪም ከመሆናቸው በላይ ኢትዮጵያን በምዕራባውያን አገራት ወክለው አገራቸውን ማገልገላቸውን ጽፈዋል።

“አለማየሁ ወደ አገሩ ቢመለስ ኖሮ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ለውጥ እንመለከት ነበር?” ሲሉ አሉላ ይጠይቃሉ።