መንግሥት የሕግ የበላይነትን ያክብር! እናት ፓርቲ

  • መንግሥት የሕግ የበላይነትን ያክብር! እናት ፓርቲ
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
May be an image of textየሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነዉ ሕገ መንግሥት እጅግ ብዙ የማያስማሙ ጉዳዮች እንዳሉበት የምንሞግተውና ለመሻሻሉ ሌት ተቀን የምንተጋ ቢሆንም አግባብነት ባለው መንገድ ማሻሻያ/ለዉጥ እስኪደረግ ድረስ በግንባር ቀደምነት መንግሥት እንዲሁም ዜጎች ህገ መንግስቱን የማክበር ግዴታ አለባቸው። መንግሥትም ህገ መንግስቱን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት በጽኑ እናምናለን፡፡ ይህ ሊሆን ካልቻለ ለግለሰባዊ፣ ቡድናዊና መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነት ምቹ መደላድል ይፈጠራል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ ፫ በግልጽ እንደሚደነግገዉ “ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም”፡፡ የሕገ መንግሥቱ ግልጽ ድንጋጌ በዚህ መልኩ ቢቀመጥም ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ይህ አንቀጽ ሲተገበር አልታየም፡፡ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ሲገባ ኖሯል፤ እየገባም ይገኛል፡፡ የቅርብ ጊዜና ወቅታዊዉ የዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ መጣስ ማሳያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት መንግሥት አገርን ባዋቀረበት የጎሳ መስመር ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል ከጥር ወር ፳፻፲፭ ዓ.ም ጀምሮ እየሠራ ያለዉ ግልጽ እና ስዉር (የዉስጥ ለዉስጥ አሠራር) እንቅስቃሴ ነዉ፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ችግሩ በመንግሥት እንደተጠነሰሰና እንደተሠራ ሁሉ መፍትሄ የተበጀለትም በመንግሥት መመሪያ እና ትዕዛዝ እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነዉ፡፡
መንግስት የቤተክርስቲያኒቷ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተቀመጠበት በዚህ ወቅት ህገ መንግስቱን በመጣስ እና ረጅም እጁን በመስደድ የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት በሚያናጋ ተግባር ላይ ተሰማርቷል፡፡ ይህ አካሄድ ደጋግመን እንደምንለዉ የአገሪቱን የሕጎች ሁሉ የበላይ ህግ የሆዉን ሕገ መንግሥት በግልጽ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ መንግስት እያደረገ የሚገኘው ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት በእምነቱ፣ በእምነቱ ተከታዮች፣ በራሱ በመንግሥት እና በአገር ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በተከታታይ ጊዜያት የተያያዘዉን የጋዜጠኞች እስርና አፈና አድማስ በማስፋት በዚሁ በሃይማኖት ጉዳይ ሽፋን የብዙሃን መገናኛ ተቋምን እስከማገድ የደረሰ እርምጃ መዉሰዱን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ፓርቲያችን ዕምነት ለኅብረተሰቡ መረጃ የሚተላለፍበትን የብዙኃን መገናኛ ተቋም አሳማኝ ባልሆነ አመክንዮ ማገድ ተገቢ አይደለም፡፡ በተግባር የሆነዉንና እየተፈፀመ ያለዉን እውነታ መቼም ቢሆን አይደብቀውም ያልተፈጸመም አያደርገውም፡፡ ስለሆነም:-
፩) መንግሥት በአብያተ እምነት ሥራዎች ውስጥ እያደረገ ካለዉ ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ በመታቀብ እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በቤተክርስቲያኒቱ ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት እንዲከናወን በመተዉ፤ ከተያያዘዉ የእምነት ተቋም ማፍረስና መከፋፈል ተልዕኮ በአስቸኳይ እጁን እንዲሰበስብ እናሳስባለን።
፪) በህግ ሽፋን በጊዜያዊነት እንዲዘጋ ዉሳኔ የተላለፈበት የማህበረ ቅዱሳን መገናኛ ብዙኃን ተቋም የሠራዉ ጥፋት ካለ በግልጽ ቀንና ሰዓቱ ተጠቅሶ ሕዝቡ እንዲያዉቀዉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ባልሆነበት ሀኔታ መገናኛ ብዙሃን ድርጅቱን በተለመደው አይነት ጥቅል ፍረጃና ካለ ተጨባጭ አሳማኝ ማስረጃ ማገድ ተገቢ አይደለም፡፡ ህዝባችንም መረጃዎችን በነጻነት የማግኘት መብቱን ሊነጠቅ አይገባም፡፡ በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው እያሳሰብን፤ የማህበረ ቅዱሳን መገናኛ ብዙሃን ተቋም ኅብረተሰቡን የማገልገል መብቱ ተጠብቆለት የእግድ ትዕዛዙ በአስቸኳይ እንዲነሳለት እንጠይቃለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.