መሳይ መኮንን
ሁለተኛው ዙር ጦርነት በተጠናቀቀ ሰሞን ነው። እኔም ስለጦርነቱ ዘገባ ለመስራት ሀገር ቤት ነበርኩ። በነበረኝ ቀረቤታ ከወታደራዊውም ሆነ ከፖለቲካው ከፍተኛ አመራሮች ጋር የመገናኘትና አንዳንድ ስስ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ሀሳብ የመለዋወጡ እድል አጋጥሞኛል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አንድ ቀን ሙሉ አብሬ የዋልኩበትም አጋጣሚ ነበር። ምናልባት ”አንድ ቀን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር” የምትል ዘለግ ያለች ጽሁፍ በቅርቡ ይዤ እመጣለሁ ብዬ አስባለሁ። ያቺ ቀን በስልጣን ላይ ስላለው መንግስት የራሴን ውሳኔ እንድወስን ያደረገች በመሆኗ በተለየ ሁኔታ አስታውሳታለሁ። ስለጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ያለኝን ዕይታ የቀየረች፡ ስለኢትዮጵያ አብዝቼ እንድጨነቅ ያደረገች፡ ባልጠበኩት የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ራሴን ያገኘሁባት፡ በመጨረሻም ከእሳቸው ተለይቼ ወደማደሪያዬ ምሽት ላይ ስገባ ”ኢትዮጵያ ሆይ! በዚህ ሰው እጅ ላይ ነሽና ፈጣሪ ይሁንሽ!” ብዬ አንጋጥጬ ጸሎት በማድረስ አልጋዬ ላይ የወጣሁባት ቀና ናት። በቅርቡ እመለስበታለሁ።
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልግባ። እናም ያን ሰሞን ከአንድ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዥ ጋር እየተጨዋወትን ነው። በመሀል አንድ ርዕሰ ጉዳይ ተነሳ። ስለአማራ ተወላጅ ባለሀብቶች። አዛዡ ‘የኢትዮጵያ የወቅቱ ችግር ምንጭ የአማራ ባለሀብቶችና ምሁራን ናቸው’ የሚል ግልብ ሀሳብ ዱብ አደረጉብኝ። እውነት ለመናገር ደንግጬአለሁ። በእሳቸው ደረጃ እንዳዚያ ዓይነት ቦልድ አቋም አልጠበኩም ነበር። ዝም ብዬ ማዳመጤን ቀጠልኩ። ‘ስታር ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል የአማራዎች ድርጅት ካወክ ዋና ስራቸው ይሄን መንግስት ለመገልበጥ የሚደረግን እንቅስቃሴ ከጀርባ መደገፍ ነው። በደንብ ደርሰንበታል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባለሀብቶችም ከማን ጀርባ እንዳሉ እናውቃለን። ከመንግስት የሚመጣውን ትዕዛዝ እየጠበቅን ነው እንጂ ልክ እናስገባቸዋለን’ እያሉ ቀጠሉ። አይኔ መርገብገቡን አቆመ። ቀዝቀዝ ያለ ላብ በጀርባዬ ሲንቆረቆር ተሰማኝ።
በምጥ አንድ ጥያቄ ሰነዘርኩኝ፥ ‘ጦርነቱን መንግስት በአሸናፊነት እንዲያጠናቅቅ የአማራ ባለሀብቶች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እኮ ነው። ለአብነትም…’ ብዬ እነበላይነህ ክንዴንና ወርቁ አይተነውን ጠቀስኩላቸው። በእርግጥም ሁለቱ ባለሀብቶች ሌሎችም አሉ፥ ሚናቸው ከፍተኛ ነበር። ፊት ለፊቴ የተቀመጡት አዛዥ ግን ሀሳቤ የጣማቸው አይመስሉም። የፊታቸው ገጽታ በአነጋገሬ የተደሰቱ እንዳልሆኑ የሚያሳብቅ ነው። ‘ተዋቸው። እነሱም ቢሆኑ አጥር ላይ የተንጠለጠሉ እንጂ ወዴየትኛው እንደተሰለፉ እርግጠኛ አይደለንም።’ በእውነቱ ግራ ገባኝ። ምን እየተደረገ ነው? ወዴት እየሄድን ነው? በየቴሌቪዥኑ መስኮትና በየመድረኩ የሚስተጋባው ፕሮፖጋናዳ ሌላ ነው። ሰዎቹ በውስጣቸው የሚንተከተከው ግን ከወዲህ ነው። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙም የዘለቀ ቆይታ አልነበረንም። በሌላ ጉዳይ ተተካ። እኔ ግን ውስጤ ተረበሸ። የሆነ ነገር ወደፊት ሊኖር እንደሚችል ተሰማኝ።
ዛሬ የሰማሁት መረጃ በእርግጥም ያልጠበኩት አይደለም። እነእስታር ቢዝነስ ግሩፕ ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ ተጠንቶበት የተካሄደ፡ አንድን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ለማላሸቅና የራስን ወገን ጡንቻ ለማፈርጠም የሚደረግ የፖለቲካ ውስልትና መሆኑ ግልጽ ነው። ያን ጊዜ ወታደራዊ አዛዡ የተናገሩትን አሁን በሚገባ ተረዳሁት። ባለፈው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ መንግስት የጥፋት ሰይፉን የመዘዘ ጊዜ እንደአብሪ ጥይት የመንግስትን እርምጃ አስቀድመው የሚነግሩን የኦሮሞ ሚዲያዎች እነስታር ቢዝነስ ግሩፕን ጠቅሰው እርምጃ እንዲወስድባቸው ሲቀሰቅሱ ነበር። የተናገሯት ከመሬት ጠብ አላለችም። የሚዲያው ክንፍ አስቀድሞ ይናገራል፥ የፖለቲካው ክንፍ እርምጃውን ወስዶ ይፋ ያደርጋል። የሆነው ይኸው ነው። ጥያቄው በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ውስልትና ምን ዓይነት ዘላቂ ሰላም ይመጣ ይሆን? አንድን ህዝብ በእንዲህ መልኩ ገፍትሮ በመጣል የሚጸና መንግስት አለን? የሚል ነው። መልሱን ለ’ጊዜ’ ልተወው።
Source – መሳይ መኮንን