የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደረጀት ውሳኔን ተከትሎ ትጥቅ እንዲፈታ በደብዳቤ ከታዘዘው የአማራ ልዩ ኃይል እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ከአደረጃጀት መውጣቱን ክልሉ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ግርማ የሽጥላ በጉዳዩ ላይ ትናንት ምሽት ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ፤ የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ የሚያዝ ደብዳቤ ከክልሉ ልዩ ኃይል ቢሮ መውጣቱ ለልዩ ኃይሉ ከአደረጃጀት ለመውጣቱ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ግርማ ጉዳዩን ሲያብራሩ፤ “ከሥራው ፈጻሚዎች መካከል “ትጥቅ እንዲያወርድ” የሚል ደብዳቤ፤ የፖለቲካ መሪዎች ባላወቅነው መንገድ ሾልኮ ይልቁንም ሰራዊቱ ሳያውቀው ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ተመለከትን” ሲሉ ስለሁኔታው ጠቁመዋል፡፡
ልዩ ኃይሉ የበላይ አመራሩ የፈረመበትና ማኅተም ያረፈበት የውሳኔ ደብዳቤ በመመለከቱ ምክንያት፤ የክልሉ ልዩ ኃይል መደናገጡን ግርማ ጠቁመዋል፡፡ በደብዳቤ የተላለፈው ውሳኔ የሰራዊቱንም የሕዝቡንም ክብር የሚነካ መሆኑን የጠቆሙት ግርማ፤ በዚሁ ደብዳቤ ምክንያት ልዩ ኃይሉ “ሳልወያይ” በሚል ቁጭት መቆጣቱን ገልጸዋል፡፡
የልዩ ኃይሉ መቆጣት ትክክል መሆኑን ያመኑት ግርማ፤ በልዩ ኃይል አመራሮችና በፖለቲካ መሪዎች ደረጃ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የልዩ ኃይል አባላትን ለማወያየት ከታሰበበት ቀን ዋዜማ ልዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ የሚያዝ ውሳኔ በደብዳቤ መታላለፉን ሲሰማ በድንጋጤ ከአደረጃጀት የመውጣት ሁኔታዎች መፈጠሩን ግርማ አምነዋል፡፡
በዚህም፤ በክልሉ ካለው አጠቃላይ ልዩ ኃይል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከእነ ሙሉ አደረጃጀቱ ባለበት ካምፕ ላይ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በውሳኔው የተደናገጡ ወይም ቅር የተሰኘው የልዩ ኃይል፤ እንደ ግርማ ገለጻ ከሆነ እሰከ 30 በመቶ የሚደርሰው ልዩ ኃይል ከአደረጃጀቱ ወጥቶ ተበትኗል ብለዋል፡፡
የክልሉን ልዩ ኃይል ደንጋጤ ውስጥ ከቷል የተባለውና በክልሉ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ደብዳቤ፤ በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ሎጂስቲክስ ተወካይ በሆኑት ረዳት ኮሚሽነር መኮንን ደርብ ተፈርሞ የወጣ ነው፡፡ በደብዳቤው ላይ ለልዩ ኃይል አደረጃጀት መምሪያዎች የተላለፈው መመሪያ፤ “በየዘርፋችሁ እና በየመመምሪያችሁ ያሉ አባላት የታጠቁትን መሳሪያ እና ተተኳሽ ወደ ኦርዲናንስ ግምጃ ጽ/ቤት ገቢ እንድታደርጉ” የሚል መሆኑን አዲስ ማለዳ ከደብዳቤው ተመልክታለች፡፡
መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን፣ በፌደራል የጸጥታ ተቋማትና በክልል ፖሊስ ለማደራጀት የወሰነው ውሳኔ፣ በአማራ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሶ ሰንብቷል፡፡ ተቋውሞውም እንደ ራያ ቆቦ፣ ደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ ባሉ ከተሞች ላይ ግጭት ተቀስቅሶ ለሰዎች ሞትና አካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል፡፡
አዲስ ማለዳ