ወንድሜን፣ መሪዬን ዶ/ር አብይን የ2018 የአመቱ ሰው ብዬዋለሁ #ግርማ_ካሳ

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ወደ 2019 አዲስ አመት እየተሻገርን ነው። ባለፈው አመት በአገራችን ኢትዮጵያ ሕወሃት የተወገደበት አመት ነው። የድል አመት። ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀበት አመት።

ይህ ባለፈው አመት ያየነው ለውጥ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። በሂደት ላይ ያለ ነው እንጂ ገና ሙሉ አይደለም። ብዙ ፈተናዎች አሉት። ምንም እንኳን ህወሃት ይሄን ለውጥ ሊቀለብሰው የሚችልበት ሁኔታ ጠባብ ቢሆንም፣ በፖለቲካ አስተሳሰብና ርዪት አለም ከሕወሃት ጋር ተመሳሳይነት ባላቸው አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ግን ለውጡ የመጨናገፍ እድሉ የጠበበ አይደለም። እነዚህ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ኦነግ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ያሉት፣ ገዢው ፓርቲ ኦህዴድ/ኦዴፓ ውስጥ በብዛት ተሰግስገው እንዳሉ ለማወቅ በኦሮሞ በክልል መስተዳደር ታችኛዉና መካከለኛ መዋቅር ያሉ አመራሮች እየፈጸሙት ያለውን መመልክት ብቻ በቂ ነው።

ይህን ለውጥ እየመራ ያለው ሚሊዮኖች “አብያችን” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ነው። ጀነራል አሳምነው ጽጌ የኢትዮጵያ ሙሴ ያለው ዶ/ር አብይ፣ በስልጣን ላይ በቆየ በሰባት ወራት ውስጥ ከትግል አጋሮቹ አቶ ገዱ፣ አቶ ደመቀ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ከመሳሰሉት ጋር በመሆን በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛና መሰረታዊ ለውጦች በአገሪቷ አምጥቷል፤ እያመጣም ነው።

እንደ ጦማሪና አክቲቪስት በክልል ደረጃ በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉትን ጸረ-ዲሞክራሲያዊ፣ ኢሰብአዊ፣ ዘር ተኮር ግጭቶችን፣ መፈናቅሎችን፣ ግድያዎችና ሽብሮችን መቆጣጠርና ሕግን ማስከበር ባለመቻሉ፣ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ተቃዉሞና ትችትን አቅርቢያለሁ። በተለይም በኦሮሞ ክልል ውስጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት ኦህዴድ/ኦዴፓ ፓርቲ ውስጥ ያሉ የታችኛውና መካከለኛ፣ው አመራር አባላት፣ በወረዳዎች፣ በቀበሌዎችና በከተሞች ኦሮሞ ባልሆኑ ማህበረሰባት ላይ እየፈጸሙት ያለውን በደልና፣ ግፍ፣ መድልዎና ዘረኝነት ፣ ለብዙዎች መፈናቀል፣ መሞት ከልክ በላይ እየሆነ ነው።

ይሄንን ለማሳየት እጅግ በጣም ብዙ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይችላል። ሆኖም በዚህ ጽሁፍ አራቱን ብቻ አቀርባለሁ፡

በቡሌ ሆራ ዪኒቨሪስቲ ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎች መማር አልቻሉም። ሕግና ስርዓት ማስጠበቅ ስላልተቻለ ተማሪዎች ለሳምንታት ሜዳ ላይ አድረው መፍትሄ ስላላገኙ፣ ወደ መጡበት ተመልሰዋል። በፈንታሌ ወረዳ፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አማራ ናችሁ ተብለው ኦሮሞ ያልሆኑ ገበሬዎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል። በአሰላ የኦህዴድ አመራሮች የአሰላ ነዋሪዎች ተደራጅተው በኦሮሞ ስም ያልተደራጁ አገር አቀፍ ድርጅቶች በመጋበዝ ስብሰባ ለማድረግ ሲሞክሩ የመሰብሰብ መብታቸው ተረገጠ። በቡራዩ በዋናነት ጋሞዎች ላይ እልቂትና መፈናቀል ሲፈጸም የአካባቢው የኦህዴድ ሃላፊዎች ለተጎጂዎች ጥበቃ ማድረግ አልቻሉም። በአጠቅላይ ኦህዴድ/ኦዴፓ በሚያስተዳድረው የኦሮሞ ክልል ከኦሮሞ ድርጅቶች ውጭ ማንም ሌላ ድርጅት ሆነ ቡድን ምንም አይነት እንቅስቅቃሴ ማድረግ አይቻልም፤ ኦሮምኛ የማይናገሩ ማህበርሰባትን አንገታቸው ደፍተው፣ ፈርተውና እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው ነው የሚኖሩት።

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ፣ በይፋ የፍቅር፣ የመደመርና የአንድነት የኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካና መርህ በሚመራው ድርጅት በኦህዴድ/ኦዴፓ ውስጥ እንዲተገበር ባለማድረጉ እጅግ በጣም ትልቅ ቅሬታ አለኝ። የተቃዉሞዬም፣፣ የትችቴም ምንጭ ይኸው በኦህዴድ ውስጥ ያሉ፣ ያልተደመሩ አሁንም ዘረኛና ኦነጋዊ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ቡድኖች አፍራሻና ጎጂ ተግባራት ናቸው።

ዶ/ር አብይን በዚህ ጉዳይ መተቸቴን፣ መቃወሜን እቀጥላለሁ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ የሚመራውን ድርጅት ኦህዴድ/ኦዴፓ እንዲያጠራና ድርጅታዊ ዲሲፕሊን እንዲዘረጋ መጠየቄን ፣ የኦህዴድ/ኦዴፓ አባላት በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጸሙትን ግፍ ማጋለጤን እቀጥላለሁ። ይሄንንም የማደርገው፣ ዶር አብይን ለማዳከማ አይደለም። አንደኛ ዶ/ር አብይን ለማጠናከር ነው። ለዉጡን ለመደገፍ ነው። ሁለተኛ ፖለቲካዬ፣ አጀንዳዬ ድምጽ ለሌላችው ድምጽ መሆን፣ ለተጎዱት መጮህ በመሆኑ ነው።

ሆኖም ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዪች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “F” ብሰጠም፤ ሌሎች ዶ/ር አብይ የፈጸማባቸው ፣ በኔ ዘንድ A+ የሚያሰጡት፣ አኩሪ፣ አስደሳች፣ ለትዉልድ የሚተርፍና ታሪካዊ ተግባራት እንዳሉት በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ እወዳለሁ። እጅግ በጣም ብዙ ዋው የሚያሰኙ ተግባራት።

ለምሳሌ በፌዴራል ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል። የሕሊና እስረኞች በትግራይ ውስጥ ካሉት በስተቀር ተፈተዋል። ጋዜጦች፣ ራዲዮዎች ቴሌቭዥኖች በዝተዋል። ፍርድ ቤቱና ምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ባላቸው በባለሞያዎች እንዲመራ ተደርጓል። በወጣቱ፣ በሕዝቡ ዘንድ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ በፊት የነደደ ነበር፣ አሁን ደግሞ በነ ዶር አብይ የበለጠ ተቀጣጥሏል። ሽብርተኛ ተብለው የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ገብተዋል። ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ሸንጎ..ሁሉንም መደርደር ይቻላል። ታግዶ አሁን በዉጭ ወይንም በጫካ ያለ ቡድን አለ ብዬ አላምንም። ሁሉም ጥሩም ይሁኑ መጥፎ በወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል። በዉጭ የታሰሩ እስረኞችን አስፈትተው ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ተደርጓል። የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንዱቋቋም በአምድረግ ዳያስፒራዉን በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሰማራ ምሪት ሰጥቷል።፡ሌሎች ሌሎችንም ድንቅ ተግባራት መዘርዝር ይችላል።

ከሁሉም በላይ ግን የዶ/ር አብይ እጅግ በጣም ትልቁና እንቁ የምለው ክንዋኔ ከኤርትራ ወንደሞቻችንን ጋር እንዳንገናኝ ሲያደርግ የነበረዉን የጥል ግድግዳ በአምላክ ቸርነት ማፈራረሱ ነው። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ የአዉሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት፣ አሉ የተባሉ ስመጥር ዲፕሎማቶች ደክመዋል ፤ ለፍተዋል። ግን ሰላምና እርቅ ማምጣት አልቻሉም።

ዶር አብይ በሳምንታት ውስጥ፣ አለም እስኪደነቅ ድረስ፣ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ጠበብት ቲዮሪን ገለባብጦ ፣ የጥላቻ፣ የጦርነትም የደም መፋሰስም ድባብን መንፈስ እንዲገፈፍ ያደረገ ነው። ዶ/ር አብይ አስመራ ሲገባ፣ የአስመራ እናቶች በአደባባይ እየዘመሩ ሲቀበሉት ሳይ ፣ እንደዚያ ቀን ውስጤ በደስታ ተናውጦ አያውቅም።

ከሶስት ሳምንታት በፊት ከዉጭ አገር ዜጎች ጋር በአንድ መድረክ ተገናኝቼ ነበር። ከፓኪስታን፣ ከበርማ፣ ከኮንጎ…የመጡ ሰዎች ነበሩ። በዚያ የተገኘው አንድ የኮንጎ ሰው፣ በውይይት መካከል፣ ከኢትዮጵያ ነኝ ስል፣ እኔ እንኳን ሳልናገር፣ ስለ ጠ/ሚኒስተር አብይ መናገር ጀመረ። “በጣም እደለኞች ናችሁ፣ እናንተ ለአፍሪካማ ተስፋ ናችሁ” ነው ያለኝ።

እንግዲህ አብያችን ይሄ ነው። ምንም እንኳን ትችትና ቅረታ ቢኖረኝ፣ መልካም ስራዎቹ በእጅጉ ሚዛን ስለደፉ፣እንደ ኢትዮጵያዊ በአለም አቀፍ መድረክ አንገቴን ቀና እንድል ስላደረገኝ፣ ስላኮራኝ፣ ቅር የተሰኘሁበትንም ያሻሽላል ከሚል እምነት፣ የጂማው ልጅ፣ ወንድሜን፣ መሪዬን፣ ዶ/ር አብይ አህመድ የግርማ ካሳ የ 2018 የአመቱ ሰው ብዬዋለሁ።