በሰሜን ኢትዮጵያው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸው ተሰማ

ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት በቀረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አዲሱ የተመድ ሰብአዊ መብት ሪፖርት ይፋ አደረገ ።

19 ገጾች ያሉትና የመጀመሪያ ግኝት የሆነው ይህ ሪፖርት ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች በሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ነው።

ለተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት መሰረት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ ብሏል።

ኮሚሽኑ እነዚህ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም ያምናል ብሏል።

ይህንን ሪፖርት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፣ የባለሙያዎቹ ቡድን ሲቋቋም ተቃውሞውን ማሰማቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ይህንን ሪፖርት ሲያቀርብ ለአምስት ወራት የዘለቀው የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሶ ጦርነቱ ባገረሸበትና በሕዝቡ ስቃይ ላይ መከራ መጨመር ብቻ መሆኑን ጠቅሶ ከኢትዮጵያም ድንበር ተሻግሮ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መዘዝ የማስከተሉ ስጋት ከፍተኛ በሆነበት ወቅት ነው።

የባለሙያዎቹ ቡድን ባወጣው ሪፖርት ላይ ተካተው የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ከተባሉት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

በመቀለ የተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ድብደባ

በመቀለ ከተማ በኅዳር 14/2014 ዓ.ም በአቅራቢያው ከነበሩ ተራራማ ስፍራዎች በነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በከባድ መሳሪያ ድብደባ እንደተፈጸመ የዐይን እማኞችን ዋቢ አድርጓል።

የከባድ መሳሪያ ድብደባ ከመፈጸሙ በፊት የመከላከያ ቃለ አቀባይ መቀለ ከበባ እንደሚፈጸምባትና ጥቃት እንደሚደርስ እንዲሁም ንጹሃን ዜጎች ራሳቸውን ከትግራይ ባለሥልጣናት ካላራቁ “ምህረት አይኖርም” ብለዋል።

ኮሚሽኑ ያናገራቸው የዐይን እማኞች እንዲሁም ሌሎች ታማኝ የሆኑ መረጃዎች ያረጋገጡት የትግራይ ኃይሎች የጦር መሳሪያዎችን ይዘው መቀለን ከኅዳር 14 በፊት ለቀው መውጣታቸውን ነው።

ኮሚሽኑ ድብደባው በሚፈጸምበት ወቅት የጦር መሳሪያ ወይንም አቅርቦት ስለመኖሩ እንዲሁም ወታደራዊ ኢላማዎች ስለመደረጋቸው ምንም መረጃ እንዳላገኘ ጠቅሷል።

ኮሚሸኑ በሰበሰበው መረጃም መሰረት የትግራይ ኃይሎች ለቀው ከወጡ በኋላ መከላከያ በንጹሃን ዜጎችና በሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ስለማድረሱም መደምደሚያ ላይ ደርሷል።

በከተማዋ ውስጥ ቢያንስ አስራ ሁለት አካባቢዎች የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን ጠቅሶ በርካታ የዐይን እማኞች የአጸፋ የተኩስ መልስ እንዳልነበር ተናግረዋል።

በእነዚህ ድብደባዎች በርካታ ሰዎች እንደተገደሉና እንደቆሰሉ ያመለከተው ሪፖርቱ በአይደር ሆስፒታል አንድ የጤና ባለሙያ 15 አስከሬኖች መቁጠሩንና ሆስፒታሉም 27 የሞቱ ሰዎችን መመዝገቡን ገልጿል።

በከተማዋ የተለያዩ ሰፈሮች ህፃናትን ጨምሮ በርካቶች መሞታቸውን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በእነዚህ ጥቃቶች ዘላቂ የሆነ አደጋ የደረሰባቸውንና ከጥቃት የተረፉ ግሰለሰቦችንም አናግሯል፤ ታማኝ የሆኑ መረጃዎችም ከ100 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ እስከ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የቆየ ሲሆን በነዚህም ወራት አባላቱ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በየፍተሻ ጣቢያው፣ ከቤታቸው ውጪ በአጠቃላይ በመላው ከተማው እየተኮሱ ገድለዋል።

በተጨማሪም ወታደሮቹ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች ያደረሱ ሲሆን የመከላከያ አባላት የፈጸሟቸው መደፈሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑም መጠለያዎች ተቋቁሞ ነበር።

አንድ የጤና ባለሙያን ለኮሚሽኑ እንደተናገሩት መከላከያ መቀለን ከተቆጣጠረ ከ4-5 ቀናት በኋላ የተደፈሩ ሴቶች መምጣታቸውን ነው። በጦር ሰፈሮች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የተደፈሩ በርካታ ሴቶች ከፍተኛ ጉዳትም እንደደረሰባቸው ነው ።

በተጨማሪም በርካታ የመቀለ ነዋሪዎችን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር በማዋል ከፍተኛ ድብደባም ይፈጽሙም እንደነበር አስፍሯል። የመከላከያ አባላት መጠነ ሰፊ ዝርፊያ እንደፈጸሙ ያመላከተው ሪፖርቱ በዚህም ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ የመንግሥት ቢሮዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችን ዘርፈዋል።

በተጨማሪም ከከተማዋ ሴት ነዋሪዎች ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ እንዲሁም የቤት እቃዎችን ዘርፈዋል። የአፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት እና የአይደር ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቢያንስ ከአምስት ወራት ባላነሰ ለጦር ሰፈር  መጠቀማቸውን አመላክቷል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰኔ 15/2013 ዓ.ም. ቶጎጋ ገበያ ላይ በደረሰ ጥቃት 60 ንጹሃን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን መከላከያም ንጹሃን ዜጎችን ለማዳን የደረሱ አምቡላንሶችን ለሁለት ቀናት አግዷል ብሏል።

በቆቦና ጭና ከተሞች የተፈጸሙ ግድያዎች

የትግራይ ኃይሉ ወደ አማራ ክልል ገብተው የቆቦን ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ በከተማዋና በአካባቢው የሚገኙ ወንዶችን ፍለጋ ጳጉሜ 04/2013 ዓ.ም. ጀመሩ።

ይህንን ያደረጉት ጦርነቱ ካቆመ በኋላ ሲሆን የጦር መሳሪያ ፍለጋ በሚያደርጉበትም ወቅት በርካታ ወንዶችን ከቤታቸው እንደወሰዱና አንዳንዶቹንም በቤተሰባቸው ፊት ገድለዋቸዋል ብሏል።

ከመግደል በተጨማሪ ድብደባዎች፣ መደፈርና የአማራን ብሔር የሚያንቋሽሹ ስድብ ይሳደቡ ነበር ተጠቅሷል።

የዐይን እማኞች ለኮሚሽኑ እንደተናገሩት የተገደሉት ግለሰቦች ሰላማዊ አርሶ አደሮችና የቀን ሠራተኞች መሆናቸውን ነው። ኮሚሽኑ ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦችንና ቤተሰብ ያጡ የከተማዋ ነዋሪዎችን ማናገሩን አመላክቷል።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች በየመንገዱ አስከሬኖች ተረፍርፈው እንደተመለከቱና በርካቶቹንም በጅምላ ቀብረናቸዋል ብለዋል። በርካቶቹም በአራት ቤተ ክርስቲያኖች ቢቀበሩም አስከሬናቸው በጅብ የተበሉ እንዳሉ የዐይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን አስከሬኖችንም ይዘው እንዳይሄዱም የትግራይ ኃይሎች ከልክለውናል ብለዋል።

የዐይን እማኞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ያሉ ሲሆን ኮሚሽኑ በበኩሉ የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ምርመራ ሊደረግ ይገባል ብሏል። በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ቁሶችን ማውደማቸው ተጠቅሷል።

በጭና ከተማም በተመሳሳይ መልኩ ወንዶችን ከሴትና ከቤተሰብ በመለየት መግደላቸውንና አንዳንዶቹም በቤተሰባቸው ፊት ተገድለዋል ብለዋል ። አንድ የዓይን እማኝ አምስት ቄሶች መግደላቸውንና የጠቀሱ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸውም ሰዎች መገዳላቸውን ገልጸዋል።

በጭናም ድብደባዎች እንዲሁም የ11 ዓመት ህፃንን ጨምሮ ታዳጊዎችንና ሴቶችን ደፍረዋል ብለዋል።

በእነዚህ ከተሞች በነበሩበት ወቅት የጤና ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችና ቤቶች መጠነ ሰፊ ውድመት ና ዝርፊያ ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ይህንን አስመልክቶ የትግራይ ባለሥልጣናትን የጠየቀ ሲሆን እሰኑም በመልሳቸው “ሕዝብ ተኮር፣ በሕግ የሚመራና መርህ ያለው” ኃይል እንዳላቸው መልሰዋል።

ሕጋቸውም የዘፈቀደ ግድያ፣ መድፈር፣ ስቃይ፣ ዝርፊያና ሌሎች ጥሰቶችን እንደማይፈቅድ ጠቅሰው ጥሰቶች ፈፅመዋል የተባሉ አባላቶቻቸው በጦሩ መመሪያና መርኅ መሰረት ታይቷል ብለዋል። ኮሚሽኑ እነዚህ ጥሰቶች መታየታቸውንና እንዲሁም በአምን ሁኔታ የሚለውን አላረጋገጥኩም ብሏል።

የድሮን ጥቃት በደደቢት የተፈናቃዮች መጠለያ

የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ በርካታ የትግራይ ነዋሪዎችን ከበው ከሁመራ ከቤታቸውና ከመሬታቸው በኃይል አፈናቅለዋል፤ እንዲሁም እህል ጨምሮ፣ ጌጣጌጥ እንደዘረፉ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች ከምዕራብ ትግራይ መሬታችሁ አይደለም በሚል በመኪኖች ጭነው ደደቢት መንገድ ላይ ጥለዋቸዋል ብልል። ደደቢት ህዳር አካባቢ የደረሱት እነዚህ ነዋሪዎች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በጊዜያዊነት ተጠልለው ነበር።

ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም. የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ሦስት ቦምቦችን የጣሉ ሲሆን በርካታ ህፃናትን ጨምሮ በስፍራው የነበሩ ተፈናቃዮች ተገድለዋል ብለዋል። ኮሚሽኑ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎችን ያናገረ ሲሆን የበርካታ ሰዎች አካላት ተበጣጥሶና ተቆራርጦ የሞቱ ሲሆን በዚህም 60 ሰዎች ሞተዋል፤ በጅምላም እንዲቀበሩ ሆኗል።

 በተጨማሪም ከተባበሩት መንግሥታት የተገኙ የሳተላይት ምስሎችና ፎቶዎችንም ኮሚሽኑ መርምሮ ይህንኑ ያረጋጠ ሲሆን በደደቢት ወታደራዊ ኢላማ አለመኖሩንም ተረድቻለሁ ብሏል። በማለት አስረድቷል።እነዚህ ምስሎች እንደሚያሳዩት በቱርክ የጦር መሳሪያ አምራች የተመረቱ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጾ በዚህ ጦርነት ላይ ድሮኖችን የተጠቀመው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው ብሏል።

መደፈር እና ወሲባዊ ጥቃት

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ መደፈርና ወሲባዊ ጥቃት መድረሱን ያመላከተው ሪፖርቱም ምንም እንኳን የተለያዩ ማኅበረሰቦች የዚህ ጥቃት ሰለባ ቢሆንም የትግራይ ሴቶችና ታዳጊዎች በተለየ መልኩ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ኢላማ መሆናቸውን ተመልክቷል።

ካለው ባህል ጋር ተያይዞ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ታዳጊዎች ሪፖርት የሚያደርጉት ወስን ቢሆንም በርካታ ኮሚሽኑ ያናገራቸው ሴቶች ፍትህ፣ አገልግሎትና ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በትግራይ በርካታ መደፈሮችና ወሲባዊ ጥቃቶች የደረሱት መከላከያ ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ፣ በኤርትራ መከላከያና በፋኖ ኃይሎች መሆኑም ሰፍሯል። በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ትግራይ መደፈርና ወሲባዊ ጥቃቶችም አሉ ብሏል።

ወሲባዊ ባርነትን ጨምሮ፣ በደቦ መደፈርና በተደጋጋሚ መደፈርና እንዲሁም በልጆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ፊትም የተደፈሩ አሉ ብሏል። ከመደፈሩ በተጨማሪ የማዋረድ ስራዎች፣ ድብደባዎች፣ ባዕድ ቁሶችን በብልት ውስጥ መጨመርም ነበሩ ብሏል።

ኮሚሽኑ ፕላስቲክ እያቃጠሉ ሰውነቷን የተለበለበ ሴት እንዲሁም በደቦና በቢላ የተደፈረች ሴት የደረሰባትን ጉዳት ተመልክቻለሁ ብሏል። የሴቶቹን አካላት በማበላሸት እንዲመክኑ የማድረግና በተለይም በምዕራብ ትግራይ ሰብዓዊነትን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ ከዚህ ስፍራ እናስወጣችኋለን እንዲሁም ሌሎች አጸያፊ ነገሮችን እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎችም መደፈርና ወሲባዊ ጥቃቶች በተቆጣጠሯቸው የአማራ ስፍራዎች መፈፀማቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። ታዳጊዎችና ሴቶች በቤታቸው እንዲሁም ተደብቀው እያሉ መደፈርና በደቦም መደፈራቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

በርካታዎቹም በትግራይ ለተደፈሩ ሴቶችና ታዳጊዎች በቀልም እንደሆነ የትግራይ ኃይሎች መናገራቸውን ከጥቃቱ ሰለባዎች ሰምቻለሁ ብሏል። በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች የኤርትራ ስደተኞችን መድፈራቸውን በሪፖርቱ ሰፍሯል።

በአጠቃላይ የተደፈሩት ሴቶች ኤችአይቪ፣ ያልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም አካላዊና የአዕምሮ ቁስለት መድረሱንም ተመልክቷል።

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ ፋኖ መጠነ ሰፊ መድፈርና ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ተጠቂዎችን ለማምከን ባነጣጠረ መልኩ መፈጸማቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። የትግራይ ኃይሎች መድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ቢፈፅሙም መጠኑ ትንሽ ነው ሲል ማረጋገጡን አስፍሯል።

ሰብዓዊ እርዳታዎችን ማገድ

የፌደራሉ መንግሥት መብራት፣ ኢንተርኔት፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ባንክ አገልግሎቶችን ከጥቅምት 25/2013 ዓ.ም ጀምሮ የታገዱ ሲሆን የተወሰኑትም በቀጣዮቹ ወራት ቢመለሱም እንደገና አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል እና አጋሮቻቸው መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ምግብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ አውድመዋል። ከብቶችን መግደል እንዲሁም ምግብ ማቃጠላቸው ተካቷል።

የትግራይ ኃይሎች በርካታ የትግራይ ግዛቶችን ከተቆጣጠሩ በኋላም መሰረተ ልማቶችን ከመዝጋት በተጨማሪ የመንግሥት ሰራተኞቸው ደመወዝ ማገድ፣ ገንዘብ እንዲሁም ቁሶችን ሸቀጦች እንዳይገቡ በፌደራል መንግሥቱና በአጋሮቹ ተፈፅሟል ብሏል።

በዚህም መድኃኒት፣ የግብርና ግብዓቶች፣ ውሃና ሌሎች ሁኔታዎች አጋጥመዋል ብሏል። በዚህም የትግራይ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ፣ 5.3 ሚሊዮን ህዝብ የሰብዓዊ እርዳታ ጥገኛ ሆኗል።

ኮሚሽኑ እነዚህን ጥሰቶች ለምን መረጠ?

ኮሚሽኑ በነበረበት የጊዜ እና የአቅም ገደቦች በሁለት ወራት ውስጥ ሊያጠናቅቃቸው የሚችሉ ክስተቶችን እንዲመርጥ አድርጎታል። ምንም እንኳን እነዚህ በኮሚሽኑ የተመረጡት ጥሰቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲሁም የሰብዓዊ ድንጋጎችን የሚጥሱ የተፈጸሙ ጉልህ ጥሰቶችን የሚያንጸባርቅ ቢሆንም አጠቃላይ የተፈጸሙ መጠነ ሰፊ ጥሰቶችን እንደማያሳይ አስታውሷል።

ምንም እንኳን ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተከሰቱትን ጥሰቶች እንዲያጣራ ሥልጣን ቢኖረውም ይህ ምርመራ ግን በትግራይ እና በአማራ ክልል ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጸሙ ጥሰቶች ላይ አተኩሯል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥሰቶች ሪፖርት ከመደረጋቸው አንጻር በርካቶች አሁን የተመረጡት ክስተቶች ውስንነት ብዙዎችን እንደሚያሳዝንም እረዳለሁ ብሏል።

ኮሚሽኑ ተጨማሪ ክስተተቶችንና ጥሰቶችንም እንደሚመረምርና  ትብብርም እንደሚኖረው ተስፋ አድርጓል።

ሆኖም በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎች በዚህ ሪፖርት ላይ የተካተቱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በርካታ የአማራ ተወላጆችን በምዕራብ ወለጋ ዞን የገደለ ሲሆን በተጨማሪም በርከታ ንብረት ዘርፏል እንዲሁም አውድሟል ብሏል።

ሠራዊቱ በለምለም ቀበሌ ቄለም ወለጋ ዞን ነሐሴ መጨረሻ ላይ ባደረሰው ጥቃት ከመቶ በላይ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውንና በርካቶች ቆስለዋል ብሏል። ኮሚሽኑ ሪፖርቱን በሚያጠቃልበት ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ በአማራ ሚሊሻ፣ በኦሮሞ ልዩ ኃይል በምዕራብ ኦሮሚያ በርካታ ኦሮሞዎች መገዳላቸውን አካቷል።

መረጃዎች እንዴት ተሰበሰቡ?

ኮሚሽኑ  የተባበሩት መንግሥታት ድረገፅ ላይ መረጃ እንዲሰጡት ለሕዝብ ክፍት አድርጎ ነበር። የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ጋር በጄኔቫና በአዲስ አበባ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በአዲስ አበባም ከፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ እንዲሁም ባለሙያዎች ጋር የተወያየ መሆኑን ገልጾ፤ ኮሚሽኑ ትግራይ መሄድ ባይችልም ከትግራይ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይቷል።

የኤርትራ መንግሥት የኮሚሽኑን እንወያይ ጥሪ እንዳልመለሱለትም ገልጿል። ኮሚሽኑ ነሀሴ አጋማሽ ላይ ለፌደራሉ መንግሥትና ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት የተነሱባቸውን ጥያቄዎች አስመልክቶ  ምላሽ እንዲሰጡት ጠይቆ ነበር። የትግራይ መንግሥት ጠቅለል ያለ ምላሹን ነሐሴ 27 ያስረከበ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሸ አልሰጠም።

ኮሚሽኑ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት የገለጸ ሲሆን አንደኛውም ከአዲስ አበባ እንዲወጡ አለመፈቀዱ ነው። በዚህም ከፍተኛ ኃዘን እንደተሰማው ገልጾ በርካታ ቃለ መጠይቆችንም በርቀት ለማካሄድ ተገድጃለሁ ብሏል።

በተለይም በክልሉ ካለው የስልክና ኢንተርኔት ችግር ምክንያት በርካታ ችግሮች ገጥመውኛል ብሏል። በነተጨማሪም የሱዳንና የጂቡቲ መንግሥታትም ወደ አገራቸው የገቡ ስደተኞችን እንዳናግር ፍቃድ አለመስጠታቸውን ገልጿል።

በዚህም 185 የሚሆኑ የጥቃት ሰለባዎችን፣ የዐይን እማኞችን በርቀት ቃለ መጠይቅ አድርጌያለሁ ብሏል። እነዚህም የተለያዩ ብሄርና እምነት የተውጣጡ እንደሆኑም አመልክቷል። በተጨማሪም የሳተላይት ምስሎች፣ ፎቶዎችና ድምፆችን እንደመረመረረም አስረድቷል።

በኢትዮጵያ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃዎችን ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም መደናቀፍ እንደገጠመውም አስፍሯል። ምንም እንኳን እነዚህ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም ኮሚሽኑ ያገኛቸው መረጃዎች የተባበሩት መንግሥታትን ምርመራ ድጋፍ የተከተሉ እንደሆኑ ሙሉ እምነቴ ነው ብሏል።

መንግሥት በትግራይ እየሰጠ ስላለው ምላሽ ኮሚሽኑ

የተባበሩት መንግሥታት፣ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በትግራይ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ቢያሳውቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ አያምኑም ብሏል።

በተለያዩ የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት የሚሰጡ መግለጫዎች የትግራይን ሕዝብ ሆን ብሎ ማራቆት የትግራይ ባለሥልጣናትን ለማዳከም የሚደረጉ ስትራቴጂ እንደሆነ አመላካች እንደሆነም ገልጿል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትና የአሁኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ “በትግራይ ክልል የተጣለውን ዙሪያ አቀፍ ከበባ እንደ ባያፍራ ለማድረግ” ነው ማለታቸውንም እንደ ምሳሌም በሪፖርቱ ተቀምጧል።

ኮሚሽኑ የፌደራል መንግሥቱ፣ አጋር የሆኑት የክልል መንግሥታት የትግራይ ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የሆኑ እንደ ውሃ፣ ጤና ፣ ምግብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የማራቆት ተግባር እየፈጸሙ እንደሆነም ማስረጃዎች አግኝቻለሁ ብሏል።

በአጠቃላይ በርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚ የሆኑ አካላት በተለያየ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶችንና የሰብዓዊ ድንጋጌዎቸን የሚጥሱ የጦር ወንጀሎች ተግባራትን መፈፀማቸውን ግኝቱ ይፋ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ምክረ ኃሳብ

ኮሚሽኑ ለተባበሩት የጸጥታው ምክርቤት፣ ለኢጋድና ለአፍሪካ የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሁኔታ ዋነኛ አጀንዳቸው እንዲያደርጉ ጠይቋል። በተጨማሪም ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ፣ እንደ ጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከሚቆጠሩ ጥሰቶች ተቆጠቡ ብሏል።

በተጨማሪም ለፌደራሉ መንግሥት ዘላቂና ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦትን እንዲያረጋግጥ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራትና የተቋረጡ መሰረተ ልማቶችን እንዲመልስ ጠይቋል።

በተጨማሪም ለፌደራሉ መንግሥትና ለትግራይ ኃይሎች ጦርነቱን በሰላም እንዲቋቹ ድርድሩ እንዲመለሱና የጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በዓለም አቀፉና በቀጣናው ስታንዳርድ መሰረት እንዲመረምርና ጥፋተኛ ኃይሎቹን አባላት ለፍትህ እንዲያቀርብ አስተያየቴን ሰጥቷል።

ለኤርትራ መንግሥትም ጥፋተኛ የጦር አባለቱን ለፍትህ እንዲያቀርብ የጠየቀው ኮሚሽኑ ለሌሎች ታጣቂ አካላትም እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ ከሚችሉ ጥሰቶች ተቆጠቡ ብሏል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን በተባበሩት መንግሥታት የርስ በርስ ጦርነቱ ላይ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ለማመርመር በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመ ሲሆን ኮሚሽኑ ለአንድ ዓመት የሚቆይ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም የሚችልም ነው።

የምርመራ ቡድኑ የካቲት 23/2014 ዓ.ም ሲቋቋም የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ሊቀ መንበር ሆነው ተሹመው ነበር። ፋቱ ቤንሱዳ በዩናይትድ ኪንግደም የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነርነትን ስልጣን መቀበላቸውን ተከትሎ ከኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ለቀዋል።

በሳቸውም ፈንታ በመጀመሪያ አባል ሆነው የተሰየሙት ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተወስኗል።  በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር በጦርነቱ ተፈፅመዋል ለተባሉ ዓለማቀፍ ወንጀሎች መርማሪ ቡድን አባል ሆነው መሾማቸውም ይታወሳል።