አቶ ለማ ትኩረታቸው ከኦሮሞ ድርጅቶች አንስተው ሕዝቡ ላይ ቢያደርጉ ጥሩ ነው #ግርማካሳ

 
ከአስር በላይ የሆኑ የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ አክቲቭስቶች እና ታዋቂ ሰዎችን ያካተተ የጋራ ምክክር መድረክ በአንድ እና ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማቋቋም መወሰናቸውን ሰምተናል።
 
ስብስቡ እዉን እንዲሆን ትልቅ ሚና የተጫወቱት አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። አቶ ለማ ያለ ማጋነን ላለፉት አመት የኦሮሞ ድርጅቶች ከጽንፈኛ አስተሳሰቦቻቸው ተመልሰው ወደ መሐል እንዲመጡ ለማግባባት ፣ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ለማድረግ በጣም ሲሰሩ የነበሩ ሰው ናቸው። እጅግ በጣም ደክመዋል።
ሆኖም ግን ኦሮሞ ከመሆናቸውና ከዘራቸው በቀር በነ አቶ ለማ መገርሳና በሌሎች የኦሮሞ ድርጅት መሪዎችና አክቲቪስቶች መካከል፣ ትላልቅ የአጀንዳ፣ የአስተሳሰብ፣ የፖለቲካ አመላካከት ልዩነቶች አሉ። ከዚህም የተነሳ የሄ ስብስብ ሆነ መድረክ ስብስብና መድረክ ከመሆን ዉጭ ለኦሮሞ ማህበረሰብ ሆነ ለሌላው ኦሮሞ ላልሆነ ኢትዮጵያዊ የሚፈይደው ይኖራል ብዬ አላስብም።
 
በኦሮሞ ክልል ያለው ትልቁ ችግር የኦሮሞ ብሄረተኞች የመስፋፋት ፖሊሲ፣ የኦሮሞ ብቻና የኦሮሞ አንደኛ ፖለቲካ የፈጠረው ችግር ነው። ላለፉት ሃያ ስምንት አመት የነበረው ፖሊቲካና የጎሳ አወቃቀር ፣ ኦሮሞው፣ ከሶማሌው፣ ከጉሙዙ፣ ከሃረሬው፣ ከአማራው ከጌዴዎ፣ ከጉራጌ፥ ከአዲስ አበቤዉና ኢትዮጵያ ብሄረትኛው…..ከሁሉም ጋር እንዲጋጭና ፣ እንዳይተማመን አድርጓል። በተለይም ከአማራውና ከአማርኛ ተናጋሪዎች ጋር ትልቅ መቃቃርና ክፍተት ተፈጥሯል።
 
እነ አቶ ለማ ያንን ክፍተት ለመሙላት፣ በኦሮሞውና በሌላው መካከል መቀራረብ መያያዝ እንዲኖር፣ አብሮነት ፣ አንድነት፣ መደመር፣ ፍቅር፣ የጋራ እሴት የሆኑትን ኢትዮጵያዊነት እንዲጠናከር ለመስራት ቢሞክሩም፣ ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ግን በተግባር ትልቅ መሰናክል ሲሆኑባቸው ነው ያየነው። (በነገራችን ላይ እነ አቶ ለማ ስል ኦህዴድ/ኦዴፓ ማለቴ አይደለም። ለምን ኦህዴድ/ኦዴፓ ውስጥ አብዛኞቹ ኦነጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ያልተደመሩ ናቸውና። ግን በኦህዴድ/ኦዴፓ ውስጥ ያሉትን ሞደሬት አመራሮች ማለቴ እንጂ)
 
በኔ እይታ ፣ አቶ ለማ ብዙ ጊዜያቸውን የኦሮሞ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ላይ ማተኮር ሳይሆን የሕዝቡ መሰረታዊ የፍትህ፣ የሰላም የመብት፣ የልማት ጥያቄዎች በመመለሱ ላይ ቢያጠፉ የተሻለ ይሆናል ባያ ነኝ። ለዚህም ምክንያቶች አሉኝ።
 
– አብዛኞቹ የኦሮሞ ድርጅቶች የሕዝብን ጥቅም ያልተረዱ፣ ተረድተውም ከሆነ ሆን ብለው የተረዱትን የሕዝብ ጥቅም ያላስቀደሙ፣ የተወሰኑትም በጥላቻና በዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እነርሱን ለማግባባት መሞከር ዉሃ በድንጋይ ላይ እንደማፈሰስ ነው።
 
– ድርጅትቶቹ፣ አንዳንዶቹ በግብጾች ገንዘብ የሚደገፍ ሜዲያ ስላላቸው፣ ሌሎችም ከድሮም የሚታወቁ ፖለቲከኞች በመሆናቸው ሕዝብ የሚደግፋቸው ይመስላል እንጂ ስር የሰደደ ሕዝባዊ ድፍ የላቸውም። የተወሰኑ ድጋፍ አላቸውም ቢባልም በኦሮሞ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች በተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ነው ድጋፍ ሊኖራቸው የሚችለው። በብዙ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች የአቶ ለማና የዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊነትና የመደመር ፖለቲካ ነው ድጋፍ ያለው።
 
– ድርጅቶቹ በሚያራመዱት አንዳንድ እንቅስቅሴዎች እነ አቶ ለማ መገርሳ የገነቡትን ሲያፈርሱ ነው የምናየው።
 
እነ አቶ ለማ መገርሳ፣ በኔ እይታ ፣ እነዚህ ድርጅቶች ሕዝብን የማይወክሉ፣ ህዝባዊ መሰረተ እንደሚያወሩት የሌላቸው መሆናቸውን ተረድተው፣ እነርሱን ከመለማመጥ ትኩረታቸውን ሕዝብ ላይ ማድረግ ነው ያለባቸው። ሶስት መሰረታዊ ተግባራትን ቢፈጸሙ በትክክል እንወክለዋለን የሚሉትን ክልል ህዝብ መጥቀምና ማገለግል ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡
 
አንደኛ- ሕዝብ የተራባውና የተጠማው ሰላምና መረጋጋት ነው። ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን፣ አቶ ለማ መገርሳ በሁሉም የኦሮሞ ክልል ሕግና ስርዓት ማስጠበቁ ላይ ትልቅ ጊዜና ጉልበት ማጥፋት አለባቸው። ከሕግ ውጭ የሆኑ፣ ቄሮዎችና አክራሪ ኦነጎች ሕዝብን እንዲያሸብር መፍቀድ የለባቸውም። በተለይም ወለጋና ሃረርጌ እየሆነ ያለው ሽብር መቆም አለበት።
 
ሁለተኛ- ሕዝብ የሚፈልው በተለይም ወጣቱ ስራን ነው። የስራ እድል እንዲኖር ደግሞ በክልሉ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስተመንት መኖር አለበት። ኢንቨስትመንት እንዲኖር ክልሉ አግላይ ሳይሆን አቃፊ፣ ዘረኛና አፓርታይዳዊ ሳይሆን የሰለጠና ዘመናዊ፣ አንዱን ጎሳ የበላይ ሌላውን ሁለተኛ ዜጋ የሚያደርግ ሳይሆን ሁሉም እኩል የሚያይ መስተዳደር መሆን አለበት። በመሆኑም በክልሉ ያሉ አፋኝና አፓርታይዳዊ አሰራሮች ተሻሽለው፣ መስተዳደሩ በተጨባጭ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ማህበረሰባት አባላትን መብት ማከር መጀመር አለበት።
 
ሌላው ኢትዮጵያዊ ወለጋ፣ አርሲ፣ ባሌ …..ሲሄድ እንደ መጤ የሚታይ ከሆነ፣ አድልዎ የሚፈጸምብት ከሆነ፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለመዝናናት፣ ኦንቨስት ለማድረግ አይመጣም።
 
ሶስተኛ – ሕዝብ የሚፈልገው መልካም አስተዳደርን ነው። ኦሮሞ ክልል በጣም ትልቅ ክልል ነው። አንድ አቶ ለማ መገርሳ ያንን ሁሉ ክልል ማስተዳደር አይችሉም። በፌዴራል ደረጃ የኦሮሞ ክልል አነስ ወዳለ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል መስተዳደሮች መቀየር እንዳለበት የማቀርበው መከራከሪያ እንደተጠበቀ፣ ያ እስኪሆን፣ ቢያንስ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልልን ለአስተዳደር አመች በሆኑ ስድስት ንኡስ መስተዳድሮች በማዋቀር፣ የርሳቸው እንዳራሴ አድርገው፣ ሙሉ ስልጣን ያላቸው ስድስት ጠንካራ ምክትል ርእስ መስተዳደሮች ቢያስቀምጡ ጥሩ ነው።
 
ለምሳሌ
 
– የኦሮሚያ የሸዋ ዞኖችን ሸዋ በሚል፣ ዋና ከተማው አዳማ የሆነ ንኡስ መስተዳደር
– የሃረርጌ ዞኖችን ምስራቅ ኦሮሚያ በሚል ንኡስ ስመስተዳደር
– የአርሲ ዞኖች አርሲ በሚል ንኡስ ስመስተዳደር
– የጉጂ፣ ባሌና ቦረና ዞኖችም ደቡብ ኦሮሚያ በሚል ንኡስ ስመስተዳደር
– የወለጋና ኢሊባቡር ዞኖⶭን ምእራብ ኦሮሚያ በሚል ንኡስ ስመስተዳደር
– የጂማ ዞኖችን ጂማ በሚል ንኡስ ስመስተዳደር