የመንግስት ሆሰፒታሎች በማደንዘዣ መድሃኒቶች እጥረት ምክንያት መደበኛ የኦፕሬሽን አገልግሎት አቁመዋል፡፡

ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግስት ሆሰፒታሎች በማደንዘዣ መድሃኒቶች እጥረት ምክንያት መደበኛ የኦፕሬሽን አገልግሎት አቁመዋል፡፡ ይህ ችግር መቼ እንደሚፈታ አይታወቅም፡፡ በዚህ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች በተራዘመ የኦፕሬሽን ቀጠሮ እየተጉላሉ ይገኛሉ፡፡ ሃኪሞችም ብንሆን ስራ ፈተን ሌሎች ብሶቶቻችንን ማዳመጥ ጀምረናል፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ለጤና ተቋማቱ ገዝቶ ማቅረብ ያለበት መስሪያቤት ይህንን ችግር እስቀድሞ በመረዳት ዝግጅት በማድረግ መቅረብ ነበረበት ኣላደረገም፡፡ ለምን? ችግሩ ያለው የት ነው?
* የውጭ ምንዛሪ እጥረት፡-
ብዙ ሰው ሰበብ የሚያደርገው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ነገር ግን ለውስኪ፣ ለኮስሞቲክስ፣ እና ለዘመናዊ መኪኖች የዶላር እጥረት ገጥሞን የማያውቅ ለምን ይሆን ለመድሃኒት እና ለህክምና እቃዎች መግዣ እጥረት የሚገጥመን? በምሽት ክበቦች ብንሄድ ሰዎች እጅግ ውድ የሚባሉ ውስኪዎች ሲራጩ እንመለከታለን ፣ ትልልቅ መንግሰታዊ ስብሰባዎች ሲኖሩ በስብሰባው አዳራሽ አካባቢ የሚደረደሩ የV8 እና ሌሎች እጅግ ውድና ዘመናዊ መኪኖች ብዛት ሲታይ መሰረታዊ ፍጆታችንን ያሟላን (ምግብና መድሃኒት) እንመስላለን፡፡ (ቅናት የተቀላቀለበት አስተያየት እንደሆነ ይወሰድ)
*ሁሉ አቀፍ ግድ የለሽነት፡-
ሃኪሞች፣ የጤና ተቋማቱ ሃላፊዎች፣ በየቢሮው ያሉ ባለስልጣናት ባጠቃላይ በምንቸገረኝነት ተጠፍንገን ዝም ብለናል፡፡ ይህ ችግር የተከሰተው በእንድ አዳር አይደለም፡፡ ለወራት ምናልባትም ለአመት ያህል ሲንከባለል የመጣ ችግር ነው፡፡
በየሆስፒታሉ ያለን ሃኪሞች በበቂ ሁኔታ አልጮህንም፣ ችግሩ ቀጥታ የሚመለከታቸው የየሆስፒታሎቹ ሃላፊዎች አለቆቻቸውን ላለማስቀየም ጸጥ ብለዋል፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ጉዳዩን የሚሰሙ የጤና ባለ ስልጣናትም ባላየ ባልሰማ ዝም ብለዋል፡፡ መድሃኒቱን ማቅረብ ያለበት መስሪያ ቤትም ቢጠየቅ አሳማኝ የሚመስል ምክንያት አዘጋጅቶ ቁጭ ብሏል፡፡
በኛ አገር በማንኛውም መስክ ሰዎች የሚጠየቁት ሲሰሩ በሚያጠፉ ዜጎች ላይ እንጂ ባልተሰራ ጉዳይ በሚመጣ ቀውስ አይደለም፡፡ አንድ ቀዶ ሃኪም ካቅም በላይ በሆነ ችግር ህይወት ለማዳን ብሎ ግዜው ባለፈበት መድሃኒት ቢጠቀምና ታካሚው ችግር ቢደርስበት ሁሉም በዛ ምስኪን ሃኪም ላይ ጣቱን ይቀስራል፡፡ ይህ ሃኪም ወይም ሰመመን ሰጪ ባለሞያ ለዚህ ሁኔታ እንዴት ተዳረገ ብሎ የሚጠይቅ ማህበረሰብም ሆነ ስርአት የለንም፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች “ባለመስራት አለመጠየቅን” እንደመፍትሄ ቆጠረውታል፡፡
* የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ፖሊሲያችን፡-
በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም እውቀትም ባይኖረንም የምንመለከተው ነገር መንግስት የውጭ ምንዛሬን ወደራሱ ለመሳብ የሚጠቀማቸወው ዘዴዎች ሁሉ እየሰሩ አይመስሉም፡፡ ከጊዜ ወደግዜ ዜጎችም የሚያገኙትን ዶላር ከመንግስት እያራቁ ነው የሚገኘው ለምን? ስግብገብ ስለሆኑ? ስግብግብ ነጋዴ ያለው እኛ አገር ብቻ አይመስለንም፡፡ በየአገሩ አሉ፡፡
የመፍትሄ ሀሳቦች
ተጠያቂነት፡- የዜጎች ተጠያቂነት ሊኖር የሚገባው በስራ ላይ ለተፈጠረ ስህተት ብቻ ሳይሆን ሃላፊነትን ባለመወጣት ለተፈጠሩ ቀውሶችም መሆን አለበት፡፡ አገሪቱን እና ዜጎችን ከግዜ ወደግዜ ትልቅ ችገር ውስጥ እየከተተ የሚገኘውን ሌብነትንና ሙስናን መንግስት ሳይውል ሳያድር በመግለጫ ሳይሆን በተግባር መዋጋት መጀመር አለበት፡፡ አንዱ የችግሩ ምንጭ ሙስና ስለሆነ፡፡ ኮሚሽን የማይገኝበት ግዢ መፈጸም ወይም አገልግሎት መስጠት በዚህ ዘመን ብርቅ እየሆነ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎቻችንን መፈተሽ፡- ይህ ጉዳይ በሹመኞች ሳይሆን በሙያው ሊቆች ሊወሰን ይሚገባው ጉዳይ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ለግዜው ግን መንግስት ይህንን ግዢ ለሚፈጽመው መስሪያ ቤት በአስቸኳይ ገንዘብ መድቦ ግዢውን እንዲፈጽም ቢያደርግ ወይም ግዢው በቀላሉ ሊከወን የሚችልበትን መንገድ ቢፈጥር፤ በንዝህላልነት የተፈጠረ ችግር ከሆነ መጠየቅ ያለበትን አካል ተጠያቂ ማድረግ፡፡ ለግል መድሃኒትና የህክምና አስመጪ ተቋማትም በቂ የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙ ቢደረግ፤ ያገኙትን ገንዘብ ለሌላ ነገሮች ግዢ አለማዋላቸውን በጥብቅ መቆጣጠር፤ በውጭ አካውንት ያላቸው ዜጎች ውጭ ያላቸውን ገንዘብ መድሃኒት እና የህክምና እቃዎችን እንዲያመጡበትን እና የሚበረታቱበትን አሰራሮችን መፍጠር፡፡
ይህ የመድሃኒት ችግሮቻችንን በከፊል የሚቀንስልን ሲሆን በተጨማሪም ካገር ውስጥ ተመልሶ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ሊቀንስ እና ለሌላ ጉዳይ ሊዉል ይችላል፡፡
በውጭምንዛሬ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ የተሰጠው አስተያየት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን እንዳንድ ተራ ዜጋ (lay man) በስሜት የተሰጠ አስተያት ተደርጎ ይወሰድ፡፡
መቋጠሪያ፡- አብዛኛው ሆስፒታሎች የኦፕሬሽን አገልግሎት አቁመው ዜጎች እየተጉላሉም ጤናቸውም አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ሰለዚህ የማደንዘዣ መድሃኒቶች የምናገኝበት መንገድ ባስቸኳይ ይፈለግ፡
– ዶ/ር መዝገብ ገደፌ – ዩሮሎጂስት
via ሀኪም