በአሁኑ ወቅት ኹሉም የጸጥታ ሀይሎች የተሻለ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛሉ – ዐቢይ አህመድ

በአሁኑ ወቅት ኹሉም የጸጥታ ሀይሎች የተሻለ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛሉ፤ ጠላቶቻችንም ይህንን በውል ሊረዱ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግርም፤ በአሁኑ ወቅት የኹሉም ክልሎች ልዩ ሀይሎች በተሻለ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛሉ፤ የእነዚህ ሀይሎች የተሻለ ብቃትትና አቋም ላይ መሆን የኢትዮጵያን ሰላም አንድነትና ህልውና ዋስትና ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህንን ሳይረዱ ኢትዮጵያዊያን በብሄር፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት በፖለቲካ ተከፋፍለዋል በሚል የተሳሳተ ስሌት ስህተት እንዳይፈጽሙ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያሳሰቡት።

ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደምም በብሄር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋና በፖለቲካ እሳቤ የሚለያዩ ሰዎች እንደነበሯት ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልዩነቶቻቸው ግን ለኢትዮጵያ ከመዋደቅ አላገዳቸውም።

በኢትዮጵያዊነት በመሰባሰብ ነጻ አገር እንዳስረከቡ ኹሉ ዛሬም ከተለያዩ ክልሎች፣ ብሄሮች ሀይማኖቶች እና የፖለቲካ እሳቤዎች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን፤ ጠላት የኢትዮጵያን ህልውና ለመንካት ሲፈልጉ በጋራ የምንቆምና ህሊውናችንን የምናስከብር መሆናችንን ጠላቶች ትምህርት ወስደው ደጋግመው እንዲያስቡበት በመጥቀስ አሳስበዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ነበረው አውደ ውጊያ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ልዩ ሀይሎችና፣ ልዩ ልዩ መጠሪያ ያላቸውና የተለያዩ ዩኒፎርሞችን የለበሱ ሀይሎች በአንድነት ጠላትን ማሳፈርና ነጻነታችንን ማስቀጠል ችለዋልም ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በዛሬው ዕለት የተሰጠው ሽልማት የህይወት እና የደም ዋጋ ለከፈሉ እንዲሁም በገንዘብና በእውቀት ለአገራቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱት መላ ኢትዮጵያዊያን የተሰጠም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።