ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት እየያዘ በመምጣቱ ስለ አንበሳ ፋርማሲ መረጃ እንዳትሰጡ ተብያለሁ ! – የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

[addtoany]

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት እየያዘ በመምጣቱና ሁሉም በየራሱ ደብዳቤ እየጻፈ በመሆኑ መረጃ እንዳትሰጡ ተብያለሁ፡፡ ነገር ግን የአንበሳ ፋርማሲ የሚታወቀዉ በቅርስነቱ ነዉ፤የማዉቀዉም ይህን ነዉ፤በዛሬዉ እለት ስለተፈጠረዉ ነገርማ ጭራሽ የማዉቀዉ ነገር የለም ፡ በዚህ መገፋፋት ዉስጥ ቅርሱን እንዴት መታደግ ይቻላል ስንል ላነሳነዉ ጥያቄ ቢሮዉ ምንም የሚሰጠን መረጃ እንደሌለ ገልጿል፡፡

ታዋቂው የአንበሳ ፋርማሲን በተመለከተ እየሆነ ያለዉ ምንድን ነዉ?

ፋርማሲው ያለበት ህንፃ በቅርስነት የተመዘገበ ነዉ፡፡

ፋርማሲው ያለበት ይህ ታሪካዊ ህንፃ ሊፈርስ ነዉ በሚል ከፍተኛ የተቃዉሞ ድምጾች ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡

በዛሬዉ እለት ጠዋት 12፡30 አካባቢ በደረሰን ጥቆማ ማንነታቸዉን ያላወቅናቸዉ ሰዎች ህንጻውን እያፈረሱ ነዉ፤በዉስጡ ያለዉ እቃ እንዲወጣ እንኳን እድል አልሰጡንም ሲሉ ነግረዉናል፡፡

ይህን ያህል አመት ህብረተሰቡን ሲያገለግል የነበረ ፋርማሲ እና በቅርስነት የተመዘገበን የሃገር ሃብት እንዴት ሰዉ ወደ ስራ ሳይሰማራ በሌሊት እንዲፈርስ ይደረጋል? ሲሉም ጥቆማዉን ያደረሱን ሰዎች ይጠይቃሉ፡፡

ስለ ጉዳዩ የተጠየቀዉ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ይህ የሚመለከተዉ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮን ነዉ የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት እየያዘ በመምጣቱና ሁሉም በየራሱ ደብዳቤ እየጻፈ በመሆኑ መረጃ እንዳትሰጡ ተብያለሁ ብሎናል፡፡
ነገር ግን የአንበሳ ፋርማሲ የሚታወቀዉ በቅርስነቱ ነዉ፤የማዉቀዉም ይህን ነዉ፤በዛሬዉ እለት ስለተፈጠረዉ ነገርማ ጭራሽ የማዉቀዉ ነገር የለም ሲል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡

በዚህ መገፋፋት ዉስጥ ቅርሱን እንዴት መታደግ ይቻላል ስንል ላነሳነዉ ጥያቄ ቢሮዉ ምንም የሚሰጠን መረጃ እንደሌለ ገልጿል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ የሚገኘው እድሜ ጠገቡ አንበሳ መድኃኒት ቤት ለረጅም ዐመታት ከነበረበትና በቅርስነት ከተመዘገበው ቤት ዛሬ ማለዳ ዕቃዎቹ እንዲወጡ ተደረገ። የመድኃኒት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፀጋዬ ታደሰ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፦ ዛሬ ማለዳ «ከ12 ሰዓት ጀምሮ የድርጅቱ የጥበቃ ሠራተኞች የመድኃኒት ቤቱ መግቢያ በር እየተሰበረ መሆኑን እንደነገሯቸውና ቦታው ላይ ሲደርሱ በር ተሰብሮ ዕቃዎች እየተጫኑ እንዳገኟቸው» ተናግረዋል።

ይህንን ድርጊት የፈፀሙት እነማን እንደሆኑ ተጠይቀው ሲመልሱ «ማን እንደሆኑ አናውቅም፣ ከክፍለ ከተማ ታዘን ነው የሚሉ ናቸው» ብለዋል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ፖሊሶች ነበሩ የሚሉት ወይዘሮ ፀጋዬ ወደ ሥፍራው ስንደርስ «እኛም ለሰላሳ ደቂቃ እንዳንገባ ተከልክለን ቆይተን መታወቂያችን እየታየ ነው የገባነው» ብለዋል።

ዶይቼ ቬለ በሥፍራው ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ ከመድኃኒት ቤቱ ውስጥ ዕቃዎች «አይሱዙ» ተብለው በሚጠሩት የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ እየተጫኑ ተሽከርካሪዎቹም የጫኑትን እየያዙ ሽቅብ ወደ ጣይቱ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ሲጓዙ ተመልክቷል።

 

መድኃኒት ቤቱ በሚገኝበት መስመር ቁልቁል ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ የሚወስደው መንገድ እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆኖ፣ አሽከርካሪዎች በዚያ መስመር ማለፍ እንደማይችሉ በፖሊሶች እየተገለፀላቸው ሲመለሱ እንደነበርም ታዝቧል። የዜናው ዘጋቢም የመድኃኒት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብቶ ቀረፃ ለማድረግ ፈቃድ አላገኘም።

ዕቃው ወዴት እየተጫነ እየተወሰደ ነው? ያልናቸው ሥራ አስኪያጇ «የመድሃኒት ቤቱ ንብረት የሆኑ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመን በየ ዘመድ ቤት እየጫንን ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከመንግሥት በኩል የተዘጋጀ ምትክ ቤት ወይም ቦታ ስለመኖሩም ጠይቀናቸው «የለም» ብለው መልሰዋል። አክለው እንደነገሩንም የመድኃኒት ቤቱ ሠራተኞች ወደ ቤቱ ገብተው ዕቃዎችን በመጫን ሲያግዙ ውለዋል።

በጉዳዩ ላይ የተጠየቀው በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ አንክ ዶንኮህ ጉዳዩ እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልፀው «ክስተቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ እና መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በሚያደረጉ የጀርመን ባለሀብቶች ላይ ትልቅ ተፅእኖ ይሮረዋል» ብለዋል። አንበሳ መድኃኒት ቤት ላለፉት ስምንት ዐሥርት ዐመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መድኃኒት የሚያቀርብ ጥንታዊ የጀርመን ድርጅት መሆኑንም ተናግረዋል።

ፒያሳ የሚገኘዉ እና በቅርስነት የተመዘገበዉ የአንበሳ መድሐኒት ቤት ባለቤት ጀርመናዊዉ ካርል ሂልደብራንት በንጉሱ ዘመን አባታቸዉ ኩርት ሂልደብራንድት የመሰረቱትን መድሐኒት ቤት በማስቀጠል የቆየ መሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱ የመድሃኒት ሽያጭ አገልግሎት፣ የቅመማ እና የሕክምና ቁሳቁስ ማስምጣት ላይ የተሰማራ ነው።

የቤቱ ባለቤት የሆነው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ «አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ የተባሉ ድርጅቶች በኪራይ ሲገለገሉበት የነበሩበት እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ንብረት የሆኑ ቤቶች፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅርስነት ይዘታቸው ሳይቀየር፣ ባሉበት ምንም ዓይነት የቅርጽና የይዘት ለውጥ ሳይደርግባቸው በአካባቢው ከሚገነባው አዲስ ግንባታ ጋር ለአልሚው ባለሀብት እንዲተላለፉ ተደርጓል» ብሏል። በቅርሶቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስባቸው በኮርፖሬሽኑ እና በከተማ አስተዳደሩ መካከል ሥምምነት ላይ መደረሱንም ዐስታውቋል።

«ቅርሶችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ፤ ቅርስ ጥበቃ እና ልማት ሚዛኑን አስጠብቆ እንዲሔድ ማድረግ ሌላኛው ከድህነት መውጫ መንገድ ሊሆን ይገባል» ያለው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን «በእርጅና ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን እና ቤቶችን ደግሞ ለኹላችን ጥቅምና እድገት በሚያስገኝ መልኩ ማልማትም ተገቢ ነው» ብሎ እንደሚያምንም ዐስታውቆ ነበር።