በ 3 ሳምንታት $250000 ብቻ? ከዚህ በላይ ማድረግ እንችላለን #ግርማ_ካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
ዶ/ር አብይ የአሜሪካ ጉብኝት ከማድረጋቸውና የማኪያቶን አንድ ዶላር በቀን ሐሳብ ከማቅረባቸው ሳምንታት በፊት “ከዳያስፖራው ተግባራዊ መደመር ያስፈለጋል – የዶ/ር አብይን ጉብኘት በተመለከተ” በሚል አንድ ጽሁፍ አስነብቤ ነበር። በዚህ ጽሁፍ
“አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አዉስትራሊያ፣ አዉሮፓ.. የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሚሊዮን ናቸው እንበል። እርግጠኛ ነኝ ትንሽ ደሞዝ አገኙ ቢባል በአመት 12 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው። ሁለት ስራ ከሰሩ ወደ 25 ሺህ፣ ፕሮፌሽናል ከሆኑ ከአምሳ ሺህ በላይ ነው የሚያገኙት። ለዉይይት እንዲመቸን ሁሉም ኢትዮጵያዊን ትንሹን ደሞዝ በአመት 12 ሺህ ዶላር ነው የሚያገኙት እንበል። በወር $1000 ፣ በቀን ደግሞ $34 ዶላር። በመሆኑ አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አባል የአመት ደሞዛቸውን 0.03%፣ በቀን አንድ ዶላር ቢሰጡ፣ በአመት 365 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል። ከ34 ዶላር አንድ ዶላር ማለት ነው። ያ በአንድ ጊዜ የአዲስ አበባ የመስለተኛ ባቡር ፕሮጀክትን እዳ ይዘጋል። ከአንድ ወደ $2.09 ቢያደረጉት፣ 762 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል። በሁለት አመት ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዳር ይሰበሰባል። ከወልዲያ አዋሽ ያለው የባቡር መስመር እዳ ይዘጋል።በቀን $2.09 ለሁለት አመት ተኩል ቢሰበሰብ ወደ $2.28 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይሄን ከአዲስ አበባ ፣ ጅቡቲ ያለውን የባቡር ፕሮጀክት እዳ ይዘጋል”
የሚል ሐሳብ በማቅረብ ዳያስፖራው ትልቅ አቅም እንዳለው ነበር ለማሳየት የሞከርኩት።
ይሄ ጽሁፍ ከወጣ ከሳምንታት በኋላ ዶ/ር አብይ አንድ ዶላር በቀን የማኪያቶ የሚል ሐሳብ አቀረቡ። ይሄንን የሚያንቀሳቀስ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድና ኮሚቴም አዋቀሩ። በፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም የሚመራ።
የተቋቁመውን የኢትዮጵያዉያን የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ኮሚቴ ( አንድ ዶላር በቀን) የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴውን ከጀመረ ሶስት ሳምንታት የሆኑት ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ከሶስት መቶ ሺህ ዶላር በታች ብቻ ነው የተሰበሰበው። ወደ እሩብ ሚሊዮን።፡ይሄ በጣም በጣም ትንሽ ነው።
አስታወሳለሁ በቅንጅት ወቅት በዲሲ በአንድ ቀን ብቻ አንድ መቶ አምሳ ሺህ ዶላር፣ በሲያትል ደግሞ መቶ ሺህ ዶላር ተሰብስቦ ነበር። በአንድ ቀን ብቻ በሲያትልና በዲሲ ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተብሎ የተሰበሰበዉን ያህል ነው በሶስት ሳምንታት ውስጥ ለዚህ ለዳያስፖራ ፈንድ ገንዘብ የተሰበሰበው። ይሄ በጣም ፣ በጣም ትንሽ ነው።
ወገኖች ቢያንስ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ መቻል አለበት። ይሄ የአንድ ወይንም የሁለት ግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው።
የትረስት ፈንዱ አጀማመር ዘገምተኛ የሆነበት ምክንያቱ በደንብ ታይቶ ማሻሻያዎችን በማድረግ በተቀላጠፈ መልኩ ሁላችንም ጉዳያችን አድርገነው መስራት ያለብን መሰለኝ። በኔ እይታ መሰብሰብ ከሚቻለው በጣም ያነሰ የተሰበሰበበት ምክንያቶች የምላቸው ሶስት ናቸው። እነርሱም፡
፩. የትረስት ፈንድ ኮሚቴ ገና መጀመሩ ስለሆነ ወደ ታች ወርዶ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እስከ አሁን የቻለ አልመሰለኝም። ለዚህም ኮሚቴዉን ለማገዝ ኢትዮጵያዊያን መነሳት አለብን። ለዚህ ስራ ትልቅ ድርጅታዊ መዋቅር ያስፈለጋል። አስር ሰዎች ሁሉንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ኮሚቴውም ሌሎችን ማሳተፍና ማሰራት መቻል አለበት። የትረስት ፈንዱ ኮሚቴ ይፋ ከመሆኑ በፊት በዚህ ጉዳይ ይሰሩ የነበሩትን ጨምሮ ሌሎችም በራሳቸው አነሳሽነት ለመስራት የሚፈለጉትን ማበረታታት አስፈላጊ ነው። ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነዉና !!!!!
፪. ገንዘብ አዋጡ ብቻ ማለት በራሱ በቂ አይደለም። ኮሚቴው ቢያንስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ፣ “በዚህ አመት እነዚህን ፕሮጀክቶችን ነው የምናስፈጽመው፣ ይሄን ያህል ገንዘብ ነው የሚያስፈልግን ..” ብሎ ቢቀርብ፣ በጣም ይረዳል። ለምሳሌ፣ አንደኛ – በዚህ አመት በቆቦ፣ በራያና አዘቦ ፣ በነገሌ ቦረና፣ በአፋር (ብዙ ጊዜ በድርቅ የሚጎዱ አካባቢዎች) ድርቅ ሲመጣ ለአደጋ እንዳይጋለጡ መቶ የዉሃ ጉድጓዶችን የማስቆፈር፤ ሁለተኛ – በጂንካ፣ አሰላ፣ ጂጂጋ፣ ሸዋሮቢት፣ ሽሬ ላሉ ሆስፒታሎች አንዳንድ አንድ የ MRI ማሽን የመግዛት እቅድ ነው ያለን፣ ወጭዉን ይሄን ያህል ነው” ብለው ቢገልጹ ገንዘቡ የት እንደሚዉል ሰው ስለሚያውቅ የበለጠ ይነሳሳል። እንደምሳሌ እነዚህን አቀርብኩ እንጂ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ሊሆኑ ይችላሉ።
ገንዘቡ ለምን እንደሚውል ሳይታወቅ፣ አዋጡ ማለት፣ ትንሽ ሰው በስሜት እንዳይነሳሳ ያደርገዋል። በዚህ ረገድ ኮሚቴው ሰዎች ለዚህ ታላቅ ተልእኮ እንዲነሳሱ creative በሆነ መልኩ መቅረብ ያለበት መሰለኝ።
፫. የዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ብዙዎች ጥይቄ ምልክት ማድረግ መጀመራቸውም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽኖ ነበረው፣ አለውምም። በተለይም የዘር ፖለቲካው አሁንም መቀጠሉ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀል ፣ በአዲስ አበባ ልጆች ላይ የተፈጸመው ግፍ ፣ የዶ/ር አብይ አመራርም ዝምታን መምረጡ፣ ብዙዎችን ግራ ያጋባበት ሁኔታ ነው የነበረው። ለዚህም ነው በአማራ ክልል የተቃዉሞ ሰልፎችም የተደረጉት።
የዶ/ር አብይ አስተዳደር፣ ፖለቲካው ከተበላሸ ሌሎች ነገሮችን ሊበላሹ እንደሚችሉ በመረዳት በተቻለ መጠን የሕዝብን ጥያቄ በመመለስና ፣ ለሕዝብ የተገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ ትልቅ ትኩረት ቢሰጥበት ጥሩ ነው እላለሁ። አስተዳደሩ በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ እንዲያዋጡ እየጠየቀ በሌላ በኩል የሕዝብን ገንዘብ አላስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ የሚያጠፋ ከሆነ ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም። ለምሳሌ ከዉጭ ወደ አገር ቤት ለሚሄዱ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶቭ መንግስት ሆቴላቸውን እየቻለ፣ እነርሱን የሚጠብቁ ጠባቂዎችን እየመደበ ፣ ለግሰለቦች ብሎ ከሕዝብ ካስና ገንዘብ የሚፈጅ ከሆነ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
ይሄን ብዬ ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ይሄን እላለሁ። የለማ ቲምን ( እነ ገዱን ጨምሮ) ገና ስልጣን ሳይዙ አደጋ ላይ የነበሩም ጊዜ ስደግፋቸው ነበር። አሁንም ለነርሱ ትልቅ ድጋፍ አለኝ። ሆኖም የጭፍን ደጋፊ አይደለሁም። ጠንካራ ተቃዉሞዎችና ትችቶችን ያቀረብኩባቸው ጊዚያቶች ቀላል አይደሉም። የዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ችግር የለብኝም ማለት አይደለም።
ሆኖም ግን በዚህ በትረስት ፈንዱ ዙሪያ ግን ያሉን የፖለቲካ ችግሮች ለአገራችንና ለሕዝባችን ድጋፍ እንዳንሰጥ ሊያግዱን በጭራሽ አይገባም። የዶ/ር አብይ አስተዳደር መቃወም ካለብን በምክንያት እየተቃወመን፣ መደገፍ ያለብንን ደግሞ በምክንያት መደገፍ አለብን። ይሄ የትራስት ፈንድ ጉዳይ መደገፍ ብቻ አይደለም ሌሎች እንዲደገፉት የራሳችን ጉዳይ አድርገን ነው መስራት ያለብን።
ወገኖች አንድ ዶላር በቀን፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር በአመት ነው መሆን ያለበት !!!! እንችላለን !!!!!!!!!