ዶ/ር ቴድሮስ ምን አሉ ? የአፋር እና የአማራ ክልል ባለስጣናት ምን መለሱ ?

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም 7 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት ክልል ከአንድ አመት በላይ ሙሉ በሙሉ ከበባ ውስጥ ሆኗል ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ህዝቡ ምንም አይነት የምግብ አቅርቦት፣ የህክምና ፣ ኤሌክትሪክ፣ የቴሌፎን ፣የመገናኛ እንደማያገኝ ተናግረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ፥ ” በመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው። በምግብ እጥረት ምክንያት እንደዚሁ ብዙዎች ህይወታቸውን ያጣሉ ከዚያ በላይ በየቀኑ የሚሰነዘረው የድሮን ጥቃት ሰዎችን እየገደለ ነው ” ብለዋል።

ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ድርጅታቸው ለመንቀሳቀስ ጥያቄ አቅርቦ በአማራ እና በአፋር ክልል እንዲንቀሳቀስ ወደ ትግራይ ግን እንዳይገባ መደረጉን ተናግረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ፥ ” ከዓለም ጤና ድርጅት በኩል ወደ ትግራይ እና ሌሎች በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች መድሃኒት ማስገባት እንድንችል ጥያቄ አቅርበን ለአማራ እና አፋር ሲፈቀድልን ለትግራይ ግን ተከልክለናል። የጠ/ሚ ፅ/ቤትን ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ፣ እና ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቀናል ፍቃድ ግን አላገኘንም። በተለይ ከሀምሌ ወር ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅት ምንም አይነት የህክምና ድጋፍ እንዲያደርግ አልተፈቀደለትም። ” ብለዋል።

ሁኔታውን ” በ21ኛው ክፍለዘመን መንግስት የራሱን ህዝብ መድሃኒት እና ለመኖር የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ይከለክላል ተብሎ አይታሰብም ” ሲሉ ነው የገለፁት።


የአፋር ክልል አዳአር ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ አሊ ለትግራይ ክልል የምግብ ድጋፍ ማድረስ አልተቻለም የሚባለውን ጉዳይ አጣጥለውታል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ወደትግራይ በአፋር አብአላ በኩል የምግብ እርዳታ ሲጓጓዝ ቆይተዋል ያሉ ሲሆን በቅርብ ጊዜ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ዓለም ያውቀዋል ሲሉ ገልፀዋል።

አቶ አብዶ ፥ ” መጀመሪያ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባበት አማራጭ መንገድ የለም፤ ለምን ? በአፋር አብአላ በኩል ያለውን ጦርነት እራሳቸው ከፍተው በአብአላ በኩል ጦርነት እያካሄዱ ነው እነሱ። በቆቦም በኩል ጦርነት እየተካሄደ ነው፤ እናስገባ ቢባል እንኳን ሁሉም መግቢያ በሮቹ በአፋር በኩል ነበር እስከዛሬ የሚገባላቸው እርዳታ የሚገባው በዛ በኩል እራሳቸው ጦርነት ከፍተው ወረራ አድርገው በአብዓላ ከተማ ላይ እስካሁን ድረስ በመድፍ እየደበደቡ ስለሆነ እርዳታ የሚገባበት አማራጭ የለም።

እሱ (ዶ/ር ቴድሮስ) ለህወሓት ፕሮፖጋንዳ ነው እንዲህ የሚያደርገው እንጂ የመግቢያ መንገዶቹ በሙሉ የጦርነት ቀጠና እንደሆኑ ያውቃል። ” ብለዋል።

በአደዓር በጦርነት የከፋ ጉዳት ቢደርስም የዓለም ጤና ድርጅት ያቀረበው ምንም አይነት ድጋፍ የለም ሲሉም ተናግረዋል።

” እኔ ባለሁበት አደዓር ወረዳ ካሳጊታ ግንባር አራት ቦታ በጦርነት የተፈናቀለውን ህዝብ አስፍረናል። ከWHO የመጣ እርዳታ እኔ አላየሁም አንድም ካርቶን የለም። WFP ሁለት መኪና ሶስት መኪና ምግብ አይቻለው ምግብ ማለት ነው። “

እንደውም በአካባቢው ካለው አሳሳቢ የጤና ችግር አንፃር WHO ለአካባቢው ጭራሽ ትኩረት አለመስጠቱን ተናግረዋል።

አቶ አብዶ ፥” አሁን ወረርሽኝ እየተከሰተ ነው። ህፃናት ደግሞ በየቀኑ መሬት ላይ ወድቀው በቀሩ ፈንጂዎች እየተጎዱ ነው። ስለዚህ ነገር ምንም ያለው ነገር የለም የዶ/ር ቴድሮስ ተቋም ” ሲሉ ወቅሰዋል።

በተጨማሪ ፥ ” በሚሊዮን የሚቆጠር ሜትሪክ ቶን ውድመት፣ ቁሳቁስ እና መድሃኒት ነው ህወሓት ወራር ባካሄደባቸው ቦታዎች በሙሉ ዘርፎ ወደ ትግራይ ያሸሸው። በእነ አቦይ ስብሃት የህወሓት አባላቶች በይቅርታ መፈታታቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘውን የሀገሪቱን ውሳኔ አጀንዳ ለማስቀር ነው እንጂ ስለተዘረፉት መድሃኒቶች እና ስለወደሙት ሆስፒታሎች ምንም ያልተነፈሰው ተቋም ዛሬ ላይ ትግራይ ውስጥ የመድሃኒት እጥረት አለ ብሎ መግለጫ መስጠቱ ከኃላ ምን አለ ? ብሎ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ” ተናገረዋል።


የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም ከዓለም ጤና ድርጅት የደረሰ ድጋፍ አለመኖሩን ተናግረዋል።

” 6 ወራት ጠላት በክልላችን በሚቆይበት ጊዜ ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ የትኛውም የUN ኤጀንሲ በለው ዓለም አቀፍ NGO ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገም። የምግብ ብቻ ሳይሆን የጤና አገልግሎት ተቋርጧል፣ አንድም ለህብረተሰቡ የሚያስፈልግ ለምሳሌ የHIV ህመምተኞች አሉ፣ የስኳር ፣ የደም ግፊት ችግር ያለባቸው አሉ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው መድሃኒት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠበት ሁኔታ ነው የነበረው ይህን ችግር ለመሻገር የትኛውም የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅት WHOን ጨምሮ ገብቶ ድጋፍ ያደረገበት ሁኔታ የለም።

ድጋፍ አለማመድረጉ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ እንዳልተደረገ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያነሳን ብንጠይቅም በጎ ምላሽ አላገኘንም።

ስለዚህ የተመድ ተቋማት ገለልተኛ ሆኖ እዚህ ክልል ላይ ተገቢውን ድጋፍ አልነበረም። ሁኔታውን ሲያወግዙም አልተሰሙም ” ሲሉ ነው የገለፁት።

ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም ፦ ” ቀበሌ ከምትገኝ የጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሆስፒታሎች ድረስ የሚችለውን ዘርፎ መውሰድ የማይችለውን አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎ አውድሟል። ይሄ እንግዲህ መላው የዓለም አቀፍ ተቋማት በግላጭ የሚያውቁት ነው። ይህን እንኳን ሲያወግዙ አይሰማም። በተመሳሳይ ጠላት ከወጣ በኃላ እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የመድሃኒት ችግር ፣ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል ቁመና ላይ አይደሉም ያሉት ጤና ተቋማቱ መልሶ ለማቋቋም እንኳን የዓለም ጤና ድርጅት አንድም አስተዋጽዖ እያበረከተ አይደለም ” ብለዋል።