የህዳሴ ግድብ ውኃ የሚተኛበት 3ኛው ዙር የደን ምንጣሮ ሥራ የክረምት ወቅት ሳይገባ እንደሚከናወን ተገለጸ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ የሚተኛበት ሥፍራ 3ኛው ዙር የደን ምንጣሮ ሥራ የክረምት ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተገለጸ።
የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የዘንድሮውን የግድቡ ውኃ የሚተኛበትን የደን ምንጣሮ ሥራ ዝግጅት በተመለከተ በአሶሳ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ፣ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በ2014 ዓ.ም የግድቡ ውኃ የሚተኛበትን 17 ሺህ ሄክታር መሬት የደን ምንጣሮ የክረምት ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የግድቡ ውኃ የሚተኛበትን አካባቢ ክረምት ከመግባቱ አስቀድሞ ማከናወን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከየካቲት 01/2014 ዓ.ም ጀምሮ የምንጣሮ ሥራውን መጀመር እንደሚገባ የገለጹት አቶ አሻድሊ፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም መናገራቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።