ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ ላይ ያልተገባ አሉባልታ መንዛት በአገር ህልውና ላይ አደጋ ለማጣል መሞከር ነው ሲሉ አስፈራሩ/ አስጠነቀቁ

በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሰራዊቱ አባላት የተሰጠው የማዕረግ እድገትና ሽልማት በደጀንነት የተሰለፈው ህዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ጭምር መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የአገር ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያልተገባ አሉባልታ የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ነው ያስጠነቀቁት።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ አኩሪ ገድል መፈጸሙን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ የተገነባበት ህዝባዊ መሰረትና ያለው ጠንካራ የአመራር ትስስር ሰራዊቱ ላስመዘገበው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው ያነሱት።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ መነሳቱ በሰራዊቱና ደጀን በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ በተካሄደው ውጊያ በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሰራዊቱ አባላት የተበረከተው የማዕረግ እድገት እና ሽልማት በቀጣይ ለአገራቸው ፊት ለፊት የሚቆሙ ጀግኖችን በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሽልማቱ የሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን ከሰራዊቱ ጎን የተሰለፉ የክልል የጸጥታ ኃይሎችና ደጀኑ ህዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሰራዊቱ ራሱን ይበልጥ በማደራጀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅሙን በመገንባት የትኛውንም የህልውና አደጋ መቀልበስ በሚያስችል ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

ሰራዊቱ ከሌሎች ጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አሸባሪው ህወሃት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ያስወጣበትን ብቃት የሰራዊቱ ዝግጁነት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ከወረራቸው አካባቢዎች የወጣው በሰራዊቱ ተቀጥቅጦና ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ገጥሞት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የሽብር ቡድኑ ሽንፈቱን በመሸፋፈን የትግራይ ህዝብንና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል አጅግ አሰልቺና የተለመደ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የትግራይ ህዝብን አፍኖ ከፍተኛ በደል እያደረሰበትና እያሰቃየው መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ “ማሸነፍ የምችለው በህዝብ ማእበል ነው” በሚል የተሳሳተ አካሄድ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን በግድ ወደ ጦርነት በመማገድ ማስጨረሱ ደግሞ የቡድኑን ጭካኔ ያሳያል ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ ቆምኩለት ለሚለው የትግራይ ህዝብ ግድ እንደሌለው በተደጋጋሚ ማሳየቱንም ነው ያነሱት።

የመከላከያ ሰራዊቱ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብራክ ክፋይና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻው ምሽግ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በዚህም ሰራዊቱን መደገፍ የአገርን ህልውና ማጽናት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ሰራዊቱ ላይ ያልተገባ አሉባልታ መንዛት ግን በአገር ህልውና ላይ አደጋ ለማጣል መሞከር መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም ሰራዊት ላይ ያልተገባ አሉባልታ የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ነው ያስጠነቀቁት።